ፑቲን የሌሉባት ሩሲያን የሚያልሙት ቢልየነሮች

ቭላድሚር ፑቲን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን በወረሩ ማግሥት የሩሲያን የናጠጡ ባለ ሃብቶች ሰብስበዋል። ወቅቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተስፋፋበት ነበር።

በክሬምሊን፣ ዬካትሪኒንስኪ አዳራሽ የተሰበሰቡት ከ30 በላይ የሚሆኑ ባለ ሃብቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለብሰዋል።

አንድ የሩሲያ ጋዜጣ የስብሰባውን ታዳሚዎች "እንቅልፍ አጥተው፣ ገርጥተው" ነበር ሲል ገልጿቸዋል።

ፑቲን ወደ አዳራሹ ገብተው ከባለ ሃብቶቹ በተቃራኒው አቅጣጫ ተቀመጡ። እንደተለመደው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አላደረጉም።

ባለ ሃብቶቹ ጦርነቱን ይደግፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ፕሬዝዳንቱ ተናገሩ።

"ምን እየተከናወነ እንደሆነ እንድታውቁ እና ከዚህ መንግሥት ጋር እንድትሠሩ እፈልጋለሁ። ይህም ምርታችንን፣ ኢኮኖሚያችንን እና የሥራ ዘርፋችንን ለመደገፍ መንገድ በመቀየስ ነው።"

ክሬምሊን በለቀቀው ቪድዮ ላይ እንደሚታየው ሁሉም ቢልየነሮች ንግግር አላደረጉም።

ዝምታ የሩሲያ ቢልየነሮች መገለጫ ከሆነ ሰነባብቷል።

የሩሲያ ባለ ሃብቶች ድምጽን ማሰማት ዋጋ እንደሚያስከፍል ያውቃሉ።

በአውሮፓውያኑ 2003 የሩሲያ ቁጥር አንድ ባለ ሃብት የነበረው ነዳጅ አምራች ሚካሂል ኮዶርኮቭስኪ ለተቃዋሚዎች ድጋፍ ይሰጥ ነበር።

ፑቲንን በሙስና የወነጀለው ባለ ሃብት በግብር ስወራ፣ በማጭበርብር እና በሃብት ምዝበራ ተከስሶ የ10 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

ለሌሎች ባለ ሃብቶች የተላለፈው መልዕክት በሩሲያ ትችት እንደማይፈቀድ ነው።

ባለ ሃብቶቹ የዩክሬንን ጦርነት ቢቃወሙም አቋማቸውን በአደባባይ አያሳዩም።

በዝምታው ውስጥ ግን ሹክሹክታዎች ይሰማሉ። ቱጃሮቹ ፑቲን ከሥልጣን ሲወርዱ ሩሲያ ምን ልትመስል እንደምትችል ማሰብ ጀምረዋል።

ፑቲን ቢሞቱ ወይም ከሥልጣን ቢወርዱ ሩሲያ ወደ 1990ዎቹ ገጽታዋ ትመለስ ይሆናል ብለው ያስባሉ።

ጤናማ የፖለቲካ ዐውድ የሚኖር ከሆነ ባለ ሃብቶች ቅንጡ ሕይወታቸውን ያጣጥማሉ።

ዘ ኢኮኖሚስት ጋዜጣ ላይ ስለ ክሬምሊን የሚጽፈው ጋዜጠኛ አርካዲ ኦስትሮቭስኪ የአገሪቱን ባለ ሃብቶች ለሰዓታት አነጋግሯል።

ቱጃሮች የአገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ በሚያዩበት መንገድ ላይ "ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ እየመጣ ነው" ይላል።

ፑቲን ወደ አዳራሹ ገብተው ከባለ ሃብቶቹ በተቃራኒው አቅጣጫ ተቀመጡ
የምስሉ መግለጫ, ፑቲን ወደ አዳራሹ ገብተው ከባለ ሃብቶቹ በተቃራኒው አቅጣጫ ተቀመጡ

ሶቪየት ኅብረት በ1991 ሲከስም አዲስ ዓለም ተፈጥሯል። የኮምኒዝምን ማክተም ተጠቅመው የናጠጡ ሃብታም የሆኑም ብዙዎች ናቸው።

ባለ ሃብቶቹ ፖለቲከኞችን ለመቆጣጠር ሞክረዋል። በእንግሊዘኛው 'ኦሊጋክስ' ይባላሉ። ሃብታቸው ፖለቲካዊ ጫና ማሳደሪያም ጭምር ነው።

1990ዎቹ "አዳዲስ ሩሲያውያን" ወደ አደባባይ የወጡበት ነው። መንግሥት ሃብት ንብረት መውረስ ሲጀምር ለባለሥልጣናት ቅርብ የሆኑ ሰዎች በአንድ ጀንበር ሚልየነር እና ቢልየነርም መሆን ችለዋል።

ዘመኑ ሙስና የተንሰራፋበት፣ ቅጥረኛ ገዳዮች በስፋት የተሰማሩበትም ነበር።

ፑቲን በ2000 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመረጡ ባለ ሃብቶች ላይ ገደብ ጣሉ። በፖለቲካው ውስጥ ማንም ጣልቃ እንዲገባ አልፈለጉም።

የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ስላገገመ ቢልየነሮችን እንዳሻቸው ማድረግ ቻሉ። ማዕከላዊ መንግሥቱም ተጠናከረ።

በሩሲያ የከፍተኛው የውጭ ኢንቨስትመንት ባለቤት ቢል ባውደር ሙስናን በመቃወሙ ከአገሪቱ የተባረረው በ2005 ነበር።

በዓለም አቀፉ የዳቮስ የምጣኔ ሃብት ጉባዔ ላይ ሳይቀር ባለ ሃብቶች ያሳዩትን ባህሪ ነቅፏል።

"ጉባዔው የእነሱ ንብረት ይመስል ነበር። በጣም በትዕቢት የተሞሉ ሰዎች ናቸው። ፑቲን ሲመጣ ግን እንደ ተማሪ ይሽቆጠቆጣሉ።"

የሩሲያ ባለ ሃብቶች የሚታወቁበትን አለባበስ የሚያሳየው አርቲስት
የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ ባለ ሃብቶች የሚታወቁበትን አለባበስ የሚያሳየው አርቲስት
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩክሬን ጦርነት ከተነሳ በኋላ ክሬምሊን የሩሲያ ባለ ሃብቶች ላይ ቁጥጥሩን አጥብቋል።

ጦርነቱን የሚተቹ ሃብታቸው ላይ ማዕቀብ ይጣልባቸዋል። የፑቲን ታማኝ ወዳጆች ደግሞ ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ የሥራ ኮንትራቶች ይሰጣቸዋል።

አሁን ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሩሲያውያን ቢልየነሮች ተበራክተዋል። ፎርብስ እንደሚለው ቁጥራቸው 115 ደርሷል። ሃብታቸው ሲደመር 700 ቢልዮን ዶላር ይደርሳል።

ታማኝ የሆኑት ባለ ሃብቶች በገንዘብ ብቻ ደስተኛ አይመስሉም። በአገር ውስጥ ፖለቲካ ጫና ማሳደር አልቻሉም።

ከሩሲያ የተሰደደው ፖለቲከኛ እና ተንታኝ ዲሚትሪ ኔክርሶቭ "ሃብታም የሆኑት በፑቲን ምክንያት ነው፤ ስለዚህ ሌላ የአቅም ምንጭ የላቸውም" ይላል።

ባለ ሃብቶቹ ከሩሲያ ውጭም አቅም አልባ ናቸው። በሞስኮ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች አላላውስ ብለዋቸዋል።

ቢል ባውደር "እንደ ተራ ወንጀለኛ ነው የሚታዩት። በግል ጄት መጓዝ አይችሉም፣ መርከባቸውን በአውሮፓ ባሕር ዳርቻዎች ማቆም አይችሉም። ይሄም በጣም የሚያዋርዳቸው ድርጊት ነው" ይላል።

ለባለ ሃብቶቹ ቅርብ የሆኑ የቢቢሲ ምንጭ እንደሚሉት፤ ቱጃሮቹ ስለ ድኅረ-ፑቲን ሩሲያ ማሰብ ጀምረዋል።

በእርግጥ ፑቲን ጥሩ ጤና ላይ ናቸው፤ ከሥልጣን በቅርቡ እንደሚወርዱ የሚጠቁም ነገርም የለም።

የ74 ዓመቱ ፑቲን ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ ቆይተዋል። አምና ለሮይተርስ የዜና ወኪል እስከ 2036 ለመምራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

ፑቲንም "ስለ ጤናችን የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው" ብለዋል።

ፑቲን ከሞቱ ወይም ሥልጣን ከለቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚካሂል ሚሹስቲን ይተካሉ። እስካሁን ግን ፕሬዝዳንት የመሆን ፍላጎት አላሳዩም።

ይህም የሥልጣን ክፍተት ሊፈጥር ይችላል። ምዕራባውያን እና ሩሲያውያንም በድኅረ-ፑቲን ዘመን ዴሞክራሲ ይሰፍናል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

ሥልጣን በባለ ሃብቶች ቁጥጥር ሥር ሳይሆን የሕዝብ ይሁንታን ይከተላል ተብሎ ቢታሰብም ይሄ የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው።

ፑቲን በሩሲያ የቀሩትን ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አክስመዋል።

ከአገሪቱ የተሰደደችው ጋዜጠኛ እና ተንታኝ አሌክሳንድራ ፕሮኮፔንኮ "ሩሲያ ቀውስን ተላምዳለች፤ ከዴሞክራሲ የራቀ ሕይወት መደበኛው አካሄድ ሆኗል" ትላለች።

ከፑቲን በኋላ ሌላ አምባገነን አገሪቱን ሊመራም ይችላል።

ሌላ አምባገነን እስከሚመጣ ድረስ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አሌክሳንድራ ትናገራለች። የፑቲን ምትክ አቅመ ደካማ ሊሆንም ይችላል።

ሌላው አማራጭ ባለ ሃብቶች አገሪቱን የሚቆጣጠሩበት ዘመን መምጣቱ ነው። ይህም የ1990ዎቹ ዓይነት ሁኔታ ይፈጥራል።

አሁን በስደት የሚኖረው የቀድሞው የክሬምሊን አማካሪ እና ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ዲሚትሪ ኔክራሶቭ እንደሚለው ምናልባትም አገሪቱ በጥቂት ኃያላን ትተዳደራለች። እነዚህ ኃያላን ግባቸው በቢዝነስ ተጠቃሚ መሆን ነው።

በአውሮፓውያኑ 2003 የሩሲያ ቁጥር አንድ ባለ ሃብት የነበረው ሚካሂል ኮዶርኮቭስኪ
የምስሉ መግለጫ, በአውሮፓውያኑ 2003 የሩሲያ ቁጥር አንድ ባለ ሃብት የነበረው ሚካሂል ኮዶርኮቭስኪ

የመጨረሻው አማራጭ ለባለ ሃብቶቹ የተሻለው መንገድ ነው። ይህ አማራጭ ተደማጭነት የሚያገኙበት፣ ሃብታቸው የማይወረስበት እና ነገሮች በእነርሱ ዙርያ የሚያጠነጥኑበት ይሆናል።

ዲሚትሪ እንደሚለው፤ ከ1990ዎቹ ወዲህ ባለ ሃብቶቹ ያላቸው ተደማጭነት እየቀነሰ ቢመጣም የፖለቲካ ጫና ለማሳደር መሞከራቸውን ይቀጥላሉ።

አንዳንድ ባለ ሃብቶች "የፀጥታ ባልደረቦችን ከመሰሉ ከትክክለኛዎቹ ሰዎች ጋር" ወዳጅነት ለመመሥረት መሞከራቸውን እንደ ማሳያ ይጠቅሳል።

ባለ ሃብቶች በፑቲን መስመር ከተጓዙ ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ ከፕሬዝዳንቱ ከተቃረኑ ደግሞ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ሃብት ንብረታቸውን በጥሬ ገንዘብ ያስቀመጡ ቱጃሮች ከሌሎች በተሻለ ነጻነት ሊኖራቸው እንደሚችል ዲሚትሪ ይገምታል።

በድኅረ-ፑቲን ዘመን የተሻለ መንቀሳቀስ የሚችሉትም እነዚህ ናቸው።

በአንጻሩ ሃብታቸው ከመንግሥት ጋር የተሳሰረ ቱጃሮች በድኅረ-ፑቲን ዘመን ፈተና ይበዛባቸዋል።

ባለ ሃብቶች ስለ ፑቲን የሚያወሩበት መንገድ እየተለወጠ መምጣቱን አሌክሳንድራ ትገልጻለች።

'አለቃ' ሲሉ ፕሬዝዳንቱን ያሞካሹ ነበር። የቭላድሚር ፑቲንን ስም መነሻ ቃል አጣምረው በሩስያኛ 'ፐርቪ' ሲሉም ይጠሯቸዋል። 'ፐርቪ' አንደኛ እንደማለት ነው።

አሁን ላይ ግን ቅያሜያቸውን በሚያሳይ ሁኔታ 'አስቀያሚ' ሲሉ ፑቲንን መጥራት ጀምረዋል።

ቭላድሚር ፑቲን

አንዳንድ ባለ ሃብቶች አፈና ያልበዛበት፣ የንግግር ነጻነት የሰፈነበት እና በፖለቲከኞች እንዲሁም ፓርቲዎች መካከል ጤናማ ፉክክር የሚስተዋልበት ሩሲያን ማየት እንደሚፈልጉ ታስረዳለች።

አሌክሳንድራ ከአንድ ባለ ሃብት ጋር ቃል ምልልስ ስታደርግ ስልኩ ይጠለፋል ብለው በመፍራት ድምጹን ለማፈን በሚል ስልኩ ላይ ተቀምጠው እንዳነጋገሯት ታስታውሳለች።

"እንዲህ ያለ ፍርሃት ምክንያታዊ አይደለም ብዬ አስቤ ነበር" ትላለች።

ድኅረ-ፑቲን ሩሲያ ምን እንደምትመስል ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በዓለም የማዳበሪያ ንግድ ቁጥር አንድ የሆነው እና የሩሲያ ስምንተኛ ቱጃር አንድሪ ሜላንቼንኮ ነው።

ከሩሲያዊ ሃብታሞች በማይጠበቅ ሁኔታ ለ 'ዘ ኢኮኖሚስት' ቃለ ምልልስ ሰጥቷል። በተለይም የክሬምሊን ወዳጅ ላልሆኑ መገናኛ ብዙኃን ቃል ምልልስ መስጠት እምብዛም አልተለመደም።

ባለ ሃብቱ ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ዩክሬን የሩሲያ እና ምዕራባውያን የውጊያ አውድማ መሆኗን ተናግሯል። ምዕራባውያን የሩሲያን የደኅንነት ስጋት እና ሉዓላዊነት ችላ እንዳሉም ገልጿል።

ሆኖም ግን ፑቲን ከሥልጣን መውረድ አለባቸው ሲል አልተደመጠም።

በሩሲያ የአንድ ሰው አገዛዝ መለወጥ እንዳለበት እና አገሪቱ ከዓለም ጋር መቀራረብ እንደሚገባት ጠቅሷል።

አሌክሳንድራ እንደምትለው ባለ ሃብቱ ለሕዝብ ውይይት በር ለመክፈት ሞክሯል። "እንደሱ ያሉ ቱጃሮች በአደባባይ መናገር እንዲጀምሩ ለማድረግ ነው" ትላለች።

ቃለ ምልልሱን ያደረገለት አርካዲ ኦስትሮቭስኪ እንደሚለው ከባለ ሃብቱ ጋር "ጥልቅ ክርክሮች" አድርገዋል።

ለጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው አሰላስሎ እንጂ ለፖለቲካ ግብዓት ብሎ አለመሆኑን ይናገራል።

ከሩሲያ ባለ ሃብቶች ጋር በሚደረጉ ቃለ ምልልሶች በግልጽ ለፑቲን ድጋፍ ሲያሳዩ አይስተዋልም።

አንዳንዶቹ ባለ ሃብቶች ድኅረ-ፑቲን ሩሲያ ወደ 1990ቹ የመመለስ ዓይነት ገጽታ እንደሚኖራት ያምናሉ።

ጋዜጠኛው አርካዲ እንደሚለው አሁን ላይ ቱጃሮች "ከግድግዳ ጋር የመላተም" ስሜት ይታይባቸዋል።

ስለ ሩሲያ የወደፊት እጣ ፈንታ ቢያስቡም እንኳን በቅርቡ አንዳች እርምጃ የመውሰድ ዕድላቸው ጠባብ ነው።

ባለ ሃብቶቹ በፑቲን ደስተኛ ባይሆኑም ፕሬዝዳንቱ በሕይወት እስካሉ ድረስ ሴራ ሊወጥኑ የሚችሉበት ዕድል ውስን እንደሆነ ቢል ያስረዳል።

"ፑቲንን ቢገዳደሩ እንደሚገድላቸው ያውቃሉ፤ ፑቲን ደግሞ በቀላሉ የሚደናገጥ ሰው ነው" ይላል።

በሩሲያ ሰፊ ኢንቨስትመንት የነበረው አሜሪካዊ ማይክ ካልቪም በዚህ ይስማማል።

"እስር ቤት ሊገቡ እና ሃብታቸውን ሊያጡ ይችላሉ" ሲል ያስረዳል።

በቀደመው ዘመን የሩሲያ ቱጃሮች የፖለቲካ ኃያላን ላይ ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል። በድኅረ-ፑቲን ዘመንም ይሄንን ለመመለስ መሞከራቸው አይቀርም።

አሁን ያለው መንግሥት ቅሪት ባለ ሃብቶቹ ወደ ቀደመው ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው እንዲመለሱ ይፈቅድላቸው ይሆን?