ቀጥታ , የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የሳይበር ደኅንነት ክስተት” እንዳጋጠመው አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የሳይበር ደኅንነት ክስተት” እንዳጋጠመው እና የመረጃ ጥሰቱን የተፅዕኖ መጠን ለማወቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ለደንበኞቹ አሳወቀ። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ በክስተቱ የደንበኞች የፋይናንስ መረጃ ለሌላ አካል ስለመድረሱ የሚያመለክት ማስረጃ እንዳልተገኘ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 9/2019 ዓ.ም. ለ‘ሼባ ማይልስ’ ተጠቃሚዎች በላከው የኢሜይል መልዕክት ገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አሜሪካ የኢራንን ደሴት መደብደቧን ተከትሎ ኩዌት ከሁለት ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት ተሰነዘረባት

    ኩዌት
    የምስሉ መግለጫ, ኩዌት ትናንት በኢራን የድሮን ጥቃት የደረሰባት ከሁለት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    የኢራን እና አሜሪካ ፍጥጫ መካረሩን ተከትሎ፣ ኩዌት እና ባህሬን ማክሰኞ ሌሊት ከቴህራን የተሰነዘሩባቸውን የአየር ጥቃቶችን መመከታቸውን አስታወቁ።

    ኩዌት በኢራን የድሮን ጥቃት የደረሰባት ከሁለት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    ሁለቱ አገራት ጥቃት የተፈጸመባቸው፣ የአሜሪካ የጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚገኘው የቀሽም ደሴት ላይ ያከን የኢራን ሚሳዔል ማስወንጨፊያ ከደበደበ በኋላ እንደሆነ የአሜሪካ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    የኢራን ጦር በበኩሉ የአሜሪካ ኃይሎች የሚገኙበትን አሊ አል ሳሌም የአየር ኃይል ጦር ሠፈር ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል። የኩዌት ባለሥልጣናት ግን ጉዳት ስለመድረሱ አልገለጹም።

    የኩዌት ጦር ማክሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ የተሰነዘሩትን “የድሮን ስጋቶችን” መመከቱን እና በሰዎች ላይም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።

    የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ጥቃቱን አውግዟል። ጥቃቱ “የኩዌትን ሉዓላዊነት በግልጽ የጣሰ፣ ደኅንነቷን እና መረጋጋቷን በቀጥታ አደጋ ላይ የጣለ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግን በከፍተኛ ሁኔታ የጣሰ ነው” ብሏል።

    የባህሬን ጦር ደግሞ ረቡዕ ዕለት የአገሪቱ አየር መከላከያ ስርዓቶች “በርካታ የኢራን የአየር ጥቃቶችን በአየር ላይ እንደጠለፉ እና እንዳወደሙ” አስታውቋል።

    የአሜሪካ ባሕር ኃይል 5ኛ ፍሊት የሚገኝባት ባህሬን፣ ከሁለት ወራት ፋታ በኋላ ባለፉት ስድስት ቀናት ውስጥ አራት ጥቃቶች እንደተፈጸሙባት ገልጻለች።

    በሌላ በኩል፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥት ንብረት የሆነው የነዳጅ ኩባንያ ማክሰኞ ዕለት በባሕረ ሰላጤው ሲጓዝ በነበረ አንድ የነዳጅ ጫኝ መርከቡ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመበት አስታውቋል። በዚህ ጥቃት አንድ የመርከብ ሠራተኛ የደረሰበት አለመታወቁን ጠቅሷል።

    ኢራን እና አሜሪካ የጥቃት ልውውጥ ውስጥ መግባታቸው እንዲሁም በሚያደገጉት ድርድር ላይ ለውጥ አለመታየቱ፣ ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት ወደ ከፋ ደረጃ ሊያድግ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

    ጦርነቱ የተጀመረው አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው የካቲት መጨረሻ ላይ ኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው።

    በሁለቱ አገራት የተደበደበችው ኢራን፣ እስራኤል ላይ እንዲሁም የአሜሪካ ወታደራዊ ንብረቶችን እና ሠራተኞችን በሚያስተናግዱ የባሕረ ሰላጤው አረብ ሀገራት ላይ የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች።

  2. የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የሳይበር ደኅንነት ክስተት” እንዳጋጠመው አስታወቀ

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ “የሳይበር ደኅንነት ክስተት” እንዳጋጠመው እና የመረጃ ጥሰቱን የተፅዕኖ መጠን ለማወቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ለደንበኞቹ አሳወቀ።

    ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ በክስተቱ የደንበኞች የፋይናንስ መረጃ ለሌላ አካል ስለመድረሱ የሚያመለክት ማስረጃ እንዳልተገኘ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 9/2019 ዓ.ም. ለ‘ሼባ ማይልስ’ ተጠቃሚዎች በላከው የኢሜይል መልዕክት ገልጿል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታማኝ ደንበኞች አገልግሎት የሚያገኙበት ‘ሼባ ማይልስ’ ከ5.4 ሚሊዮን ገደማ ደንበኞች እንዳሉት ባለፈው ዓመት የወጣ መረጃ ያመለክታል።

    “የመረጃ ጥሰት የሕዝብ ማስታወቂያ” በሚል ርዕስ የተላከው ኢሜይል ክስተቱ ያጋጠመው የሼባ ማይልስ ሥርዓት ላይ ብቻ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።

    ለሼባ ማይልስ ደንበኞች የተላከው መልዕክት፣ በአየር መንገዱ “በሲስተሞቻች ላይ ውስን አድማስ” ያለው “የሳይበር ደኅንነት ክስተት” ማጋጠሙን አስረድቷል። “ክስተቱ የተወሰኑ ደንበኞችን መረጃዎች ነክቶ ሊሆን ይችላል” ብሏል።

    የአየር መንገዱ መልዕክት፣ ክስተቱ ያጋጠመው “በቅርቡ” እንደሆነ ቢገልጽም ትክክለኛውን ቀን አላስቀመጠም።

    በዚህ ጥሰት ምን ያህል ደንበኞች እንደተነኩ፣ ምን ዓይነት መረጃ ጥሰት እንደደረሰበት ወይም ክስተቱ እንዴት እንደተደረሰበት በግልፅ አላሳወቀም።

    ቢቢሲ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።

    ጉዳዩ “በከፍተኛ ትኩረት እና ጥንቃቄ” መያዙን የገለጸው አየር መንገዱ፣ “ክስተቱን ለመመርመር እና ሙሉ ተፅዕኖውን ለመገምገም ከሳይበር ደኅንነት አጋሮቻችን እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው” ብሏል።

    አየር መንገዱ ጉዳዩን ለመፍታት “ሙሉ ትኩረት እና ሀብቱን” ማዋሉንም አክሏል። “ተጨማሪ መረጃዎች ሲገኙ” ለደንበኞቹ እንደሚያሳውቁም ቃል ገብቷል።

    ደንበኞች ራሳቸውን ከሚደርሳቸው “ከማንኛውንም አጠራጣሪ ወይም አስፈላጊ ያልሆነ ግንኙት” እንዲጠብቁ አየር መንገዱ አሳስቧል።

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህ ዓይነት የበይነ መረብ (ሳይበር) ደኅንነት ክስተት እንዳጋጠመው ያስታወቀው፣ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ከፍተኛ የአገልግሎ መስተጓጎሎች ባጋጠሙበት ወቅት ነው። ባለፈው ሳምንት ግዙፉ ማይክሮሶፍት ባጋጠመው መስተጓጎል አገልግሎቶቹ ተቋርጠው ነበር።

    በአሜሪካ ደግሞ በአገሪቱ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ባጋጠመ ክስተት ምክንያት በ25 ዓመት ውስጥ ረጅም ለተባለ ጊዜ በረራዎች ተቋርጠዋል።

    የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅነንት ተቋም በበኩሉ ማክሰኞ ዕለት የመሥሪያ ቤቱ የውስጥ ግንኙነት ሥርዓት ተቋርጦ እንደነበር አሳውቋል። የአገሪቱ ባንኮችም ተመሳሳይ መስተጓጎል አስተናግደዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ ደግሞ በፈረንሳይ ሱፐርማርኬቶች ማቀዝቀዣ ፍሪጅ መቆጣጠሪ ሥርዓት ላይ በተፈጸመ የሳይበር ጥቃት ምክንያት ምግቦች ተበላሽተዋል። ቀጥሎም በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ተመሳሳይ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል።

    ፈረንሳይ፣ የሱፐርማርኬቶች ማቀዝቀዣ የሙቀት መጠናቸው እንዲጨምር ላደረገው የሳይበር ጥቃት ተጠያቂ ያደረገችው ኢራንን ነው። ኢራን ግን ክሱን ውድቅ አድርጋለች።

  3. ትራምፕ፣ ፑቲን እና ዢ ጂንፒንግ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ በአካል ተገናኝተው ተጨባበጡ

    ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ፣ ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን ሲጨባበጡ

    በቻይና ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ለሚያደጉት ታሪካዊ ውይይት እየተዘጋጁ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን ከአንድ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገናኙ።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በእስያ ፓስፊክ መሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሼንዘን ከተማ ደርሰው ከአውሮፕላን ሲወርዱ በቻይናው መሪ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ጉባኤው የሚጠናቀቀው ዓለም በትኩረት እየተጠባበቀው ያለው የሁለቱ መሪዎች እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ስብሰባ ከተደረገ በኋላ ነው።

    ትራምፕ ከአውሮፕላን ከወረዱ በኋላ ከቻይና ፕሬዝዳንት ጋር በጥንቃቄ በተቀናጀ አኳኋን ሲጨባበጡ እና ሲተቃቀፉ ታይተዋል። ቀጥሎ ደግሞ የአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ከመጀመቱ በፊት ለፑቲን ሰላምታ ሰሲጡ እና አጭር ቃላትን ሲለዋወጡ ተስተውሏል።

    ትራምፕ እና ፑቲን ነገ ሐሙስ ከጉባኤው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። የዩክሬን ግጭት ከንግግር አጀንዳዎቻቸው አንዱ ሊሆን ይችላል።

    ይሁን እንጂ የእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር መድረክ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል የሆነው ሐሙስ ዕለት የሚካሄደው የአሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ የሦስትዮሽ ውይይት ነው።

    ሦስቱ መሪዎች አንድ ላይ በአካል ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

    የስብሰባው ሙሉ አጀንዳ ይፋ ባይደረግም፣ ስለ ዩክሬን እና ኢራን ግጭቶችን፣ ስለ ኒውክሌር መሣሪያዎች መስፋፋትን፣ ስለ ንግድ ውጥረቶችን እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ዘርፍ ስለተመዘገቡ እድገቶች ሊወያዩ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል።

    ትራምፕ እና ፑቲን ለብቻቸው የሚያደርጉ ውይይት ምን ዓይነት ቅርጽ እንደሚኖረው እስካሁን ግልጽ አይደለም። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ግን ብዙ ልዑካን የማይገኙበት፣ አጭር እና መደበኛ ያልሆነ ንግግር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የኪየቭ ወይም የአውሮፓ ተወካዮች ባልተገኙበት ጦርነቱን ለማስቆም ስለሚዘጋጅ ዕቅድ ሊወያዩ ይችላሉ የሚል ስጋት አንስተዋል።

    ትራምፕ እና ፑቲን ከነሐሴ 2017 ዓ.ም. በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገናኝተው የተጨባበጡት ዛሬ ረቡዕ ነው። በወቅቱ የሩሲያው መሪ ስለ ዩክሬን ጦርነት ለመነጋገር ወደ አላስካ ተጉዘው የነበረ ቢሆንም ውይይቱ ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።

  4. የናይጄሪያ 36 ግዛቶች የየራሳቸውን ፖሊስ እንዲያደራጁ እና እንዲያሰማሩ ሊፈቀድ ነው

    የናይጄሪያ ፖሊስ አርማ

    ከናይጄሪያ የፌደራል ኃይሎች ጎን ለጎን ግዛቶች የየራሳቸውን ፖሊስ እንዲያደራጁ እና እንዲያሰማሩ ሊፈቀድ ነው።

    የአገሪቱ 36 ግዛቶች ለቀረበው ረቂቅ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል።

    ረቂቁ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚያስፈልገው ሲሆን፤ ሕግ ሆኖ እንዲተገበር ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ፊርማቸውን ማኖርም ይጠበቅባቸዋል።

    ግዛቶች ፖሊስ እንዲያሰማሩ በፌደራል እና በግዛቶች ደረጃ ሕጉ መተግበር እንዳለበት ተገልጿል።

    ረቂቁ የቀረበው ናይጄሪያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሰላም ማጣት እየተፈተነች ባለችበት ወቅት ነው።

    የፌደራል ኃይሉ የጅምላ እገታ፣ በማኅበረሰቦች መካከል የሚፈጠር ግጭት እና ዝርፊያን ለመቆጣጠር እየሞከረ ይገኛል።

    የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የፖሊስ ኃይል እጥረት ክፍተት ፈጥሯል። ፖሊሶች በአግባቡ ሥልጠና እንደማይሰጣቸው እና በቂ መሣሪያ እንደሌላቸውም ተመልክቷል።

    አሁን ላይ ተግባራዊ እየሆነ ያለው አሠራር በ1999 በወጣው ሕገ መንግሥት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ፖሊሶች የሚሰማሩት በማዕከላዊ መንግሥቱ ሥር ነው።

    ግዛቶች የየራሳቸውን ፖሊስ አደራጅተው እንዲያሰማሩ መፍቀድ አለመረጋጋት ሲከሰት በፍጥነት ምላሽ እንዲሰጡ እንደሚረዳ ይታመናል። ፖሊሶቹ ማኅበረሰባቸውን በተሻለ ሁኔታ እንደሚገነዘቡ በማንሳትም ሐሳቡን የሚደግፉ አሉ።

  5. ጋና የገዛችው የ60 ሚሊዮን ዶላር ፕሬዚደንታዊ ጄት ቁጣ ቀሰቀሰ

    በ60 ሚሊዮን ዶላር የተገዛው ፕሬዚደንታዊ ጄት
    የምስሉ መግለጫ, ፈረንሳይ ሰራሹ ፋልኮን 6ኤክስ እያረጀ ያለውን የፕሬዚደንቱን ጄት እንደሚተካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል

    የጋና መንግሥት አዲስ የገዛው የ60 ሚሊዮን ዶላር ፕሬዚደንታዊ ጄት ሕዝባዊ ቁጣ ቀሰቀሰ።

    መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበትን ፕሬዚደንታዊ ጄት የገዛው በርካታ ዜጎች በኑሮ ውድነት እየተፈተኑ ባለበት ወቅት ነው።

    60 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት ፈረንሳይ ሰራሹ 'ፋልኮን 6ኤክስ' ፖለቲካዊ ውዝግቦችን ያስከተለ ሲሆን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም "ቅድሚያ ለሚሰጠው ነገር ቅድሚያ ባለመስጠት" የፕሬዚደንት ጆን ማሃማን አስተዳደር ከስሰዋል።

    ሆኖም መንግሥት እያደገ የመጣው የአገሪቷ ኢኮኖሚ እየተሻሻለ በመምጣቱ የጄቱ ዋጋ ተመጣጠኝ መሆኑን እና እያረጀ የመጣውን የፕሬዚደንቱን ጄት ለመተካት በማስፈለጉ ግዥው በምክንያት የተፈፀመ መሆኑን አስረድቷል።

    ውዝግቡ የተከሰተው የማሃማ አስተዳደር ጋና ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም እርዳታ እንድትጠይቅ ያስገደዳትን እና ለዓመታት ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲያገግም ለማድረግ እየጣረ ባለበት ወቅት ነው።

    የጋና አየር ኃይል፣ የፈረንሳይ ኤርስፔስ ኩባንያ በሆነው ዳሶልት አቪየሽን የተመረተውን እና 60 ሚሊዮን ዶላር የወጣበትን አውሮፕላን ሰኞ ዕለት ተረክቧል።

    ፕሬዚደንታዊ አውሮፕላኑ የተገዛው ባለፈው ታኅሳስ ወር ምክር ቤቱ የአገሪቷን የጦር አውሮፕላኖች የማዘመን ሰፊ ፕሮግራም አካል አድርጎ ግዥውን ካፀደቀው በኋላ ነው። ይህም ከኤርባስ የተገዙ አራት ሄሊኮፕተሮችን ያካትታል።

    ጋና ጄቱን ሰኞ እለት የተረከበች ቢሆንም የተገዛበት ወቅት እና ዋጋን በተመለከተ በኦንላይን እና በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ዘንድ ትችትን አስከትሏል።

    አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ለአውሮፕላኑ የወጣው ገንዘብ በሌሎች ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ነገሮች ላይ መዋል ነበረበት ብለዋል።

    አንድ የኤክስ ተጠቃሚ “ገንዘቡ ከ100 ሺህ በላይ ነርሶችን እና 200 ሺህ መምህራንን መቅጠር ይችላል” ብሏል።

    መንግሥት በበኩሉ የጋና የኢኮኖሚ ሁኔታ ጥሩ መሻሻል አሳይቷል ሲል ትችቱን ውድቅ አድርጓል።

    • ተያያዥ ዜና፡
  6. በሱዳን ጦርነት በዚህ ዓመት ብቻ 2 ሺህ 230 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል - ተመድ

    የድሮን ጥቃት እንደደረሰበት የተገለጸው የገበያ ሥፍራ
    የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ጥቅምት ወር በአቢዬ ግዛት በገበያ ሥፍራ የድሮን ጥቃት መድረሱ ከተገለፀ በኋላ የአካባቢ ባለሥልጣናት አካባቢውን ጎብኝተዋል

    በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት በዚህ ዓመት ብቻ 2 ሺህ 230 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንዳረጋጋጠ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታወቀ።

    ከእነዚህ መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት የተገደሉት በድሮን ጥቃቶች መሆኑን ገልጿል። ይህም “የግጭቱ መገለጫ ባህሪ እየሆነ መጥቷል” ብሏል።

    የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ተርክ “ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የጦርነት ሕጎችን ችላ ማለታቸውን” አውግዘው፤ ይህም የጦር ወንጀል ሆኖ ሊቆጠር እንደሚችል ተናግረዋል።

    በሱዳን መንግሥት ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ከሦስት ዓመት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን እልባት ያላገኘ ሲሆን በዓለም አስከፊ ከሆኑ ሰብዓዊ ቀውሶችን አንዱን አስከትሏል።

    እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ከቅርብ ወራት ወዲህ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የድሮን ጥቃቶችን ፈፅመዋል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ከባለፈው ዓመት ጥር እስከ ሰኔ ወር ያሉትን ጊዜያት በሚሸፍነው ሪፖርቱ “በሱዳን እየጨመሩ የመጡት የድሮን ጥቃቶች የግጭቱን ገፅታዎች የሚያሳዩ ናቸው፤ ተፋላሚዎቹ ከጦር ግንባሮች እና በቁጥጥራቸው ሥር ካሉ ቦታዎች ርቀው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል” ብሏል ።

    ድርጅቱ ከሪፖርቱ ጋር አብሮ ባወጣው መግለጫውም በጦርነቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 2 ሺህ 230 ከፍ ማለቱን እና ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 630ዎቹ የተገደሉት በድሮን ጥቃቶች መሆኑን ማረጋገጡን ገልጿል። ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም አመልክቷል።

    በግጭቱ በቀጥታ ከተገደሉት በተጨማሪ የኃይል እና የውሃ መሠረተ ልማቶች የድሮን ጥቃቶች ዒላማ መሆናቸው እየጨመረ መምጣቱንም ሪፖርቱ አክሏል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  7. የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከስክሶ 19 ሰዎች ሞቱ

    አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ያለውን ቅጽበት የሚያሳዩ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ይገኛሉ
    የምስሉ መግለጫ, አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ያለውን ቅጽበት የሚያሳዩ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ይገኛሉ

    የሩሲያ ወታደራዊ የመጓጓዣ አውሮፕላን በሳይቤርያ ተከስክሶ ሁሉም 19 ተሳፋሪዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያ ዘገበ።

    የሩሲያ መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ኤኤን-12 የተባለው ወታደራዊ አውሮፕላን በኬሜሮቮ ግዛት “ሰዎች በማይኖሩበት አካባቢ የታቀደ በረራ” ሲያካሂድ አደጋው ተከስቷል።

    አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ሲሆን፤ ትክክለኛውን መንስዔ ለማወቅ የሩሲያ አቪዬሽን ባለሥልጣን ምርመራ ከፍቷል።

    የአካባቢው አገረ ገዢ ኢላያ ሴርዴዩክ የድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞች ተሰማርተው “በፍጥነት እሳቱን እንዳጠፉ” ተናግረዋል።

    አደጋው የተከሰተው ያጉኖቮ በተባለ መንደር ሲሆን ፖሊስ በአካባቢው እንቅስቃሴን እንዳይደረግ አግዷል።

    አገረ ገዢው እንዳሉት አሁን ላይ ዋነኛው ሥራ ለሚካሄደው ምርመራ ድጋፍ መስጠት ነው።

    የእሳት አደጋ ሠራተኞች ሥራቸውን ሲያከናውኑ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችንም አጋርተዋል።

    አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ያለውን ቅጽበት የሚያሳዩ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ይገኛሉ።

  8. በዌስት ባንክ የ72 ዓመት ፍልስጤማዊት በእስራኤል ሰፋሪዎች መገደሏ ተገለጸ

    የሚያለቅሱ ሴቶች
    የምስሉ መግለጫ, የፋዳ አል ፋሂዳ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማክሰኞ ዕለት በአከል ዱዩክ አል ታህታ መንደር ተፈጽሟል

    በእስራኤል በኃይል በተያዘው እና በቅርቡ የእስራኤል ሰፋሪዎች በገቡበት የዌስት ባንክ መንደር ውስጥ በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ አንዲት ሴት መገደሏን እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ክስተቱን በተመለከተ ከሁለቱም ወገን የሚወጡ መረጃዎች የተለያዩ ናቸው።

    በአካባቢው የሚኖሩ ፍልስጤማውያን፣ በፍልስጤም ባለሥልጣናት ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ጀሪቾ አቅራቢያ በሚገኘው አል ዱዩክ አልታህታ ሰፋሪዎቹ ጥቃት መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር በበኩሉ የፍልስጤም መኪና የእስራኤል ተሽከርካሪን በመግጨት ጥቃት መፈፀሙን ገልጿል።

    ከዚያም በምላሹ ተኩስ በከፈተው እስራኤላዊ ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን አስረድቷል። ሆኖም ጦሩ ተተኩሶባቸው የተገደሉትን ሴት በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

    በአካባቢው የሚኖሩ ፍልስጤማውያን እንዳሉት ግን ሰኞ ምሽት የተፈፀመው ጥቃት የደረሰው እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በጀመሩት ትንኮሳ ነው።

    ፍልስጤማውያን ሕፃናት ድንጋይ መወርወር ጀመሩ ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ከዚያም ሰፋሪዎቹ ተኩስ መክፈታቸውን እና በቤታቸው ደጅ ላይ የነበሩ ፋዳ አል ፋሂዳ የተባሉ የ72 ዓመት ሴት መገደላቸውን ተናግረዋል።

    የሟች የልጃቸው ሚስት የሆነችው ኔማ አል ፋሂዳ፣ ፋዳ ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመትተው መሞታቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

    በቅርቡ በዌስት ባንክ በሚገኝ አዲስ አካባቢ እስራኤላውያን መስፈራቸውን ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።

    ሰፋሪዎቹ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት "ምስጢራዊ" ባሉት ዘመቻ በመንደሯ የሚገኙ ስምንት ቤቶችን ገዝተው ገብተዋል።

    መኖሪያ ቤቶቹ የእስራኤል ኃይሎች ሙሉ ቁጥጥር በሚያደርጉበት አካባቢ የሚገኙ ናቸው።

    በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እስራኤል የምታካሂደው ሁሉም ሰፈራ ሕገ ወጥ ነው።

    • ተያያዥ ዜናዎች፡
  9. ለትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ የአሜሪካ አምባሳደር ገለጹ

    ማሲንጋ

    በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ፣ አሜሪካ በትግራይ ክልል ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ እና በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ የወደፊት ግንባታን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

    አምባሳደር ማሲንጋ፣ ከሌሎች አምባሳደሮች እና ከተባበሩት መንግስታት ልዕኡካን እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሰኞ ኅዳር 8/ 2019 ዓ.ም. በመቀለ ባደረጉት የጋራ ጉብኝት ከክልሉ አመራሮች እና ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

    የኤምባሲው ድረ ገጽ ላይ ውይይቱን በተመለከተ በወጣው መግለጫ፣ በውይይቱ ወቅት አምባሳደሩ “መረጋጋት፣ አካታችነት እና ጠንካራ ተቋማት ለሁሉም የትግራይ ሕዝብ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይሎች ናቸው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

    እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ለክልሉ ነዋሪዎች የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለማስፋት እና ሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍሎች ከዕድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስፈላጊ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።

    አምባሳደር ማሲንጋ በተለይም በቀጣይነት በክልሉ በሚታየው ድርቅ የተጎዱ ማኅበረሰቦች ሕይወት አድን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማረጋገጥ አሜሪካ ያላትን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

    አምባሳደሩ አክለውም አሜሪካ ከትግራይ ሕዝብ፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ትግራይ እና መላው ሰሜን ኢትዮጵያ ወደ መረጋጋት እና እድገት እንዲሸጋገሩ ለመደገፍ እንደምትሠራ ገልጸዋል።

    በተለይም ክልሉ ከገጠሙት ችግሮች በማገገም ወደ ልማት እንዲመለስ “ከክልሉ ሕዝብ፣ ከፌዴራል መንግሥቱ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ ነን” በማለት የአሜሪካ መንግሥትን አቋም አስታውቀዋል።

    የፌዴራል መንግሥት መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከተማዋ በገባው በዚህ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ውስጥ፣ ከአሜሪካ አምባሳደር በተጨማሪ ከስምንት ሀገራት የተውጣጡ አምባሳደሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካተታቸው ተዘግቧል።

    የጉዞው ዋና ዓላማ በትግራይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በአካል ለመመልከትና በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ነው ተብሏል።

    በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ጦርነት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ የአሜሪካ ኤምባሲ ሁለቱ ኃይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡ ሲያሳስብ የቆየ ሲሆን፣ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋም በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፣ የህወሓት መሪዎች “መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመክፈት ባሳለፉት ደካማ ውሳኔ ማዘናቸውን” ገልጸው ነበር።

    አክለውም “ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ጦርነት ውስጥ ባለመግባት ብልህ እንዲሆኑ” በመምከር፣ አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደተሳሳተ መንገድ ለመምራት የሚሞክሩ ተጨማሪ አመራሮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል አማራጩ እንዳላት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

  10. ትራምፕ ቻይና ከመግባታቸው አስቀድሞ ፑቲን እና ዢ ውይይት ጀመሩ

    ዢ ጂንፒንግ፣ ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን
    የምስሉ መግለጫ, ዢ ጂንፒንግ፣ ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቻይና የሚካሄደውን የእስያ ጉባዔ ለመታደም ሸንዘን ገብተዋል።

    በጉባዔው ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግም ይገኛሉ።

    የኒውክሌር መሣሪያ ትጥቅ መቀነስን በተመለከተ የሦስትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

    ትራምፕ ቻይና ከመግባታቸው አስቀድሞ ፑቲን እና ዢ ውይይት ማድረግ ጀምረዋል።

    ሰኞ ዕለት ወደ ቻይና የሚያደርጉትን ጉዞ የጀመሩት ትራምፕ እግረ መንገዳቸውን ትናንት ፊሊፒንስ ገብተው ሌላ ጉባዔ እየታደሙ የሚገኙ ሲሆን ዛሬ ቻይና ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ትራምፕ በፊሊፒንሱ ጉባዔ ላይ ከሕንድ እና አውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር ተገናኝተዋል።

    የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁንየር የእስያ አገራት መሪዎች ለትራምፕ ተምሳሌታዊ “ድል” እንዳቀዳጁ ተናግረዋል።

    የአሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ መሪዎች የሦስዮሽ ውይይት ሲያደርጉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።

    ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ውይይት እንዲደረግ መጠየቃቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር የኒውክሌር መሣሪያ ትጥቅን ለመቀነስ የሦስትዮሽ ውይይትን እንደሚደግፉ ጠቁመዋል።

    “ስለ ብዙ ጉዳዮች” እንደሚወያዩ የተናገሩት ትራምፕ “የኢራንን ጦርነት ለማስቆም እየሞከርን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

    መሪዎቹ የኢራን እና የዩክሬንን ጦርነት ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩም ዋይት ሃውስ ቀደም ብሎ አስታውቋል።

    በቻይና በኩል ስለ ውይይቱ አጀንዳዎች ዝርዝር መረጃዎች አልወጡም።

  11. የኅዳር 9 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የማክሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።