የእስራኤል ጦር ከሚቆጣጠረው የጋዛ ክፍል አልፎ ወታደራዊ ዘመቻ ከፈተ

የተፈናቀሉ ቤተሰቦች እየሸሹ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእስራኤል ምድር ጦር፣ "የሽብር ዋሻዎችን" ለማፍረስ በሚል ባልተለመደ ሁኔታ ከቁጥጥሩ ውጭ በሆነው የማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ አካባቢ ወታደራዊ ዘመቻ ከፈተ።

በከባድ መሣሪያ ድብደባ ሽፋን የተደረገላቸው የጦሩ ታንኮች፣ ከኑሴይራት የስደተኞች ካምፕ በስተምሥራቅ በኩል በመገስገስ ከሰሜን ወደ ደቡብ ወደሚወስደው የግዛቱ ዋና መንገድ መግባታቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

እስራኤል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው የጋዛ ግዛት በቁጥጥሯ ሥር ያደረገች ሲሆን፣ ይህንን ስፍራም "ቢጫ ክልል" በሚል ለይታዋለች። የአሁኑ ወታደራዊ ዘመቻ የተደረገው ከዚህ መስመር አልፎ በሚገኝ የጋዛ ክፍል ላይ ነው።

የእስራኤል ጦር የዚህ ዘመቻው ዓላማ "ቢጫው መስመር" ተብሎ ከሚጠራው የግዛቱ ክፍል በስተምዕራብ የሚገኝን "የሽብር ዋሻ" ማፍረስ ነው ብሏል።

ከቢጫው መስመር ውጪ ያለውን የጋዛ ክፍል የሚቆጣጠረው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ በበኩሉ፣ እስራኤል ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ "ግልጽ ጥሰት" ፈጽማለች ሲል ከስሷል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በነበሩት ያለፉት 13 ወራት እስራኤል በየዕለቱ በሚባል ደረጃ ጋዛ ውስጥ ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች። በግዛቱ የሚኖሩ 2.1 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን የኑሮ ሁኔታም እጅግ አስከፊ እንደሆነ ቀጥሏል።

ትናንት ረቡዕ፣ የእስራኤል ወታደራዊ ክፍል የሆነው 'ኮጋት' የአረብኛ ቋንቋ ቃል አቀባይ፣ የምድር ጦር ዘመቻ መጀመሩን አስታውቀዋል። ከኑሴይራት እና ቡሬጅ የስደተኞች ካምፖች በስተሰሜን በሚገኝ አካባቢ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ለራሳቸው ደኅንነት ሲሉ ከአካባቢው እንዲርቁ አስጠንቅቀዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው የሚያልፈው እና ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚወስደው የሳላህ አል-ዲን መንገድ ዝግ እንደሚሆን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቀጥሎም የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አገሪቱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ከሆነው ሺን ቤት ጋር በመተባበር "ከቢጫው መስመር በስተምዕራብ የሚገኝ እንዲሁም በእስራኤል ሠራዊት ላይ ቀጥተኛ እና አፋጣኝ ስጋት የደቀነ የሽብር ዋሻ ለማፍረስ" የጋራ ዘመቻ መጀመሩን አስታውቋል።

"በደቡብ ዕዝ ሥር ያሉ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት በአካባቢው ተሰማርተዋል" ብሏል።

"ማንኛውንም አፋጣኝ ስጋት ለማስወገድ እና የሐማስ አሸባሪ ድርጅት በእስራኤል ሲቪሎች ወይም በሠራዊቱ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚያደርገውን ሙከራ ለማክሸፍ ወይም ስምምነቱን እንዳይጥስ ለመከላከል መንቀሳቀስ ይቀጥላሉ" ሲልም አክሏል።

ሐማስ ባወጣው መግለጫ የእስራኤል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ከቢጫው መስመር አልፈው መግባታቸው እና ነዋሪዎችን ማፈናቀላቸው "አደገኛ ክስተት እና ግልጽ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት ነው" በማለት አስጠንቅቋል።

ከእስራኤል ጦር ማስጠንቀቂያ በኋላ፣ ነዋሪዎች በኑሴይራት ካምፕ አቅራቢያ ከሚገኙ አካባቢዎች ሲሸሹ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ወጥተዋል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ባረጋገጠው አንድ ቪዲዮ ላይ፣ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ድምፅ የሰማ አንድ ሰው አጎንብሶ ሲሮጥ ይታያል። ግለሰቡ "በአሁኑ ሰዓት የእስራኤል ወራሪ ኃይል በሰዎች ቤቶች እና ድንኳኖች አቅራቢያ በዘፈቀደ እየተኮሰ ነው" ሲል ይሰማል።

በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ረቡዕ ዕለት እስራኤል በፈጸመቻቸው ሦስት የተለያዩ የድሮን ጥቃቶች ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች መቁሰላቸውን አስታውቋል።

ከዘመቻው ተከስቷል ስለተባለው የሰዎች ሞት ጥያቄ የቀረበለት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ስለ ዘመቻው ጠቅለል ያለ መግለጫ ልኳል።

የእስራኤል ጦር "በርካታ ወታደራዊ ታጣቂዎችን መምታቱን" ለቢቢሲ ገልጿል።

ባለፈው ዓመት የእስራኤል እና ሐማስ ተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተጀመረ ወዲህ እስራኤል በጋዛ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ቢያንስ 1,658 ሰዎች መገደላቸውን በተባበሩት መንግሥታ ተዓማኒ መረጃ ተደርጎ የሚቆጠረው በሐማስ በሚተዳደረው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ በዚህ ጊዜ ውስጥ ስድስት ወታደሮቹ መገደላቸውን ገልጿል።