በአላማጣ እና አካባቢው በነበረው ውጊያ ነዋሪዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ምን እናውቃለን?

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ አላማጣ ከተማ ሲገቡ የሚያሳይ ምስል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በአላማጣ እና አካባቢው ደረሰ በተባለ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ባለፉት ሦስት ቀናት ብቻ ቢያንስ ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪ እና አንድ የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ በአላማጣ እና አካባቢው ከመስከረም 16 እስከ 19፣ 2019 ዓ.ም. ድረስ ከባድ ውጊያ መካሄዱን ጨምረው ገልጸዋል።

ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ ማወቅ አለመቻላቸውን የተናገሩት እነዚህ ነዋሪዎች፣ በከተማዋ እና በአካባቢው በተፈጸሙ ጥቃቶች የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ50 በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ቢቢሲ በከተማዋ ደረሱ ስለተባሉት ጉዳቶች ከገለልተኛ ምንጮች ማረጋገጥ አልቻለም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአላማጣ ከተማ ነዋሪ "በእነዚህ አራት አምስት ቀን [ከአርብ እስከ ሰኞ] በነበረው ውጊያ 65 የሚጠጉ ንፁኃን ሰዎች የሞቱ ሲሆን የቆሰሉት ግን ምን ያህል እንደሆኑ አላውቅም" ብለዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ጦር እና የትግራይ ኃይሎች በአካባቢው ያደረጉት ውጊያ "አካባቢውን የጦርነት ቀጣና " አድርጎት እንደነበር የተናገሩት እኚህ ነዋሪ "በድሮን ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች አለመጎዳታቸውን" ተናግረዋል።

"ጉዳቱ የደረሰው በከባድ መሣሪያ" በተፈጸመ ጥቃት ነው ያሉት እኚህ ነዋሪ፣ በገበያ ሥፍራ፣ ከአላማጣ ወደ ኮረም በሚወስደው መንገድ እንዲሁም ወርቅነሽ በመባል በሚታወቀው ሆቴል አካባቢ መሆኑንም ጨምረው አስረድተዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እንደ አዲስ ጦርነት ያገረሸው የህወሓት ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ ሦስት የአውሮፕላን ማረፊያዎችን መቆጣጠራቸው ከተሰማ በኋላ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጦርነቱ በአማራ እና አፋር ክልል አዋሳኝ ቦታዎች እየተካሄደ ሲሆን ህወሓት "ከፌዴራል ኃይሎች ተፈፀመብኝ" ያለውን ጥቃት ለመከላከል ግጭት ውስጥ መግባቱን አስታውቋል።

የፌደራል መንግሥቱም ከህወሓት ለተከፈተበት ጥቃት የመከላከያ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።

ጦርነቱ በይፋ የተጀመረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች " የፌደራል መንግሥቱን ከሥልጣን ለማውረድ" ጥምረት መፍጠራቸውን ባስታወቁ ማግስት ነው።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከመስከረም 12 እስከ መስከረም 15/2019 ዓ. ም. ድረስ ብቻ በኮረም እና አላማጣ ሆስፒታሎች የገቡ ታካሚዎች ቁጥር በ48 ሰዓታት ውስጥ ከ180 ወደ 420 ከፍ ማለቱን ገልጿል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ጥቃቱ ከዋና መንገዱ ገባ ባሉ አካባቢዎችም መፈጸሙን ተናግረው "የካቶሊክ ሚሽን የሚገኝበት አካባቢ፣ ከዋጃ ወደ አላማጣ መግቢያው ላይ ባለው ድልድይ አቅራቢያ፣ መስጊድ አካባቢ ከባድ መሳሪያ ወድቆ ሰዎች ተጎድተዋል።" ሲሉ ተናግረዋል።

ከግራ ካሱ አቅጣጫ ተተኩሶ የቤተሰብ አባላት መጎዳታቸውን እንዲሁም ከከተማው ወጣ ብሎ ባለ የገጠር አካባቢ በሚገኙ ትንንሽ አካባቢዎችም የተጎዱ መኖራቸውን እንዲሁም የሟቾች ቀብር መፈጸሙን ጨምረው ገልጸዋል።

ሌላው ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይገለጽ የጠየቁ የሆስፒታል ምንጭ ባለፉት ሦስት ቀናት ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ የ52 ሰዎች ሕይወት በከባድ መሣሪያ ጥቃት መጥፋቱን ተናግረዋል።

የሆስፒታል ምንጩ ከሟቾቹ መካከል ለተወሰኑት የሕክምና እርዳታ ማድረጋቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

ከሟቾቹ መካከል የሦስት ቀን ጨቅላ ሕጻንን ጨምሮ በተለያየ የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች እንደሚገኙበት ምንጩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መስከረም 18፣ 2019 ዓ.ም. ወደ አላማጣ ከተማ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መግባቱን እና ሙሉ በሙሉ አካባቢውን መቆጣጠሩንም ምንጩ አክለዋል።

በአላማጣ ከመስከረም 16 እስከ 19 2019 ዓ.ም. ድረስ ከባድ ውጊያ መካሄዱን የተናገሩት ምንጩ "ታኦ፣ ጉባጋላ፣ መረዋ፣ ራያ መንደር፣ ደራይታ፣ በርተኽላይ በሚባሉ ሥፍራዎች ከባድ ውጊያ ተካሂዷል" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።

ከአላማጣ ከ18 እስከ 20 ኪሎሜትር በሚርቁ አካባቢዎች እስከ ትናንት ማክሰኞ ድረስ ከባድ ውጊያ መካሄዱንም ጨምረው ተናግረዋል።

"የዛሬውን ሳይጨምር [ማክሰኞ] እስከ ትናንት ድረስ የሦስት ቀን ሕጻንን ጨምሮ እስከ 68 ዓመት አዛውንት ድረስ 52 ንጹኃን ሞተዋል" ያሉት የሆስፒታል ምንጩ፣ ከ52 ሟቾች መካከል 12ቱ የተገደሉት በአላማጣ ገበያ ላይ በደረሰ ጥቃት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በርካታ ከባድ እና ቀላል ቁስለኞች ወደ ሕክምና ተቋማት መምጣታቸውን የሚናገሩት ባለሙያው "ከ52 ሰዎች ዘጠኙ ብቻ የሕክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው ሳለ ሞተዋል" ብለዋል።

የሕክምና ባለሙያው ተጎጂዎችን ወደ አላማጣ ሆስፒታል፣ ብሩህ ተስፋ መለስተኛ ሆስፒታል እንዲሁም አሰፋ ሻረው ከፍተኛ ክሊኒክ መወሰዳቸውንም ገልጸዋል።

ከ52 ሟቾች መካከል አምስቱ ከከተማዋ ወጣ ብሎ በሚገኝ የገጠር ቀበሌ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የተገደሉ መሆናቸውን የተናገሩት ባለሙያው፣ ሌላው በከተማዋ በደረሰ የከባድ መሣሪያ ፍንዳታ የተነሳ መገደላቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ከአላማጣ ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች የከባድ መሣሪያ ተኩስ እስከ ትናንት ማክሰኞ አመሻሽ ድረስ እንደሚሰማ የሚናገሩት ባለሙያው "ሕዝቡ በጣም ሰላም ናፍቆታል" ይላሉ።

ነፍሰ ጡሮች፣ ሕጻናት፣ እናቶች፣ አዛውንቶች ጦርነቱን ሽሽት ወደ ከተማ ተፈናቅለው "የአንድ ሰዓት እና የሁለት ሰዓት መንገድ እየተጓዙ" እየመጡ መሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ሰኞ መስከረም 18/2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ በጦርነት ተጎድተው በትግራይ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች የሄዱ ታካሚዎችን ቁጥር ይፋ አድርጓል።

በተቋሙ ድጋፍ መስከረም 15፣ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ሽረ ወደሚገኘው ስኹል ሆስፒታል የገቡ በጦርነት የተጎዱ ታካሚዎች ከ300 በላይ እንደሚሆኑ ገልጿል።

ቡድኑ አክሎም "አሁን ባለው ሁኔታ ምክንያት በአላማጣ ሆስፒታል ያለው እንቅስቃሴ ተቋርጧል" ሲልም ኤምኤስኤፍ አስታውቋል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ "በጣም አስጊ" ሲል ገልጾታል።

ነዋሪዎች ከግጭት እየሸሹ መሆናቸውን በመግለጫው ላይ የጠቀሰው ቡድኑ፣ የተፈናቃዮችን ሁኔታ እየተከታተለ እንደሆነ ጠቁሟል።

በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች "የተፈናቃዮችን ፍላጎት ለማሟላት" ዝግጅት እያደረገ እንደሆነም በመግለጫው ላይ ገልጿል።

ግጭቱ እየተባባሰ ከመምጣቱ አንጻር የንጹኃን ዜጎች ደኅንነት እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት "እንዳሰጋው" ጠቅሷል።

በ2012 ዓ.ም. ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመት ያህል የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከአራት ዓመት በፊት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት ከቆመ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ያለው ቁርሾ እየተካረረ መጥቶ ባለፈው ሳምንት በይፋ ዳግም ግጭት ውስጥ ገብተዋል።

በትግራይ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ሲቋረጥ፣ በአማራ ክልል ታሪካዊ ቅርስ መገኛ በሆነችው ላሊበላም በረራ መቆሙን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ህወሓት በአጎራባች ክልሎች እና በደቡብ ትግራይ ተፈፀመ ያሉትን ጥቃት እና በትግራይ ክልል ያሉ አየር ማረፊያዎችን መቆጣጠሩን አውግዘው የግጭቱ መባባስ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በትግራይ ለሁለት ዓመት በተካሄደው እና በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት በተቋጨው ጦርነት ከ600,000 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይገመታል።