የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በሩሲያ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ተገናኝተው ሊወያዩ ነው

ስቲቭ ዊትኮፍ በጠባቂዎቻቸው ተከብበው
የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ በኦስሎ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ለዓመታት እያካሄደች ያለውን ጦረነት ለማስቆም በሚቻልባቸው ሀሳቦች ላይ ለመወያየት ረቡዕ ዕለት በሴንት ፒተርስበርግ ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚገናኙ ተገለጸ።

ይህ ዜና የተሰማው ዊትኮፍ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር በኦስሎ ከተገናኙ አንድ ቀን በኋላ ሲሆን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ውይይቱን "ገንቢ" ሲሉ ገልጸውታል።

ኪየቭ ቀደም ሲል አሜሪካ ቁልፍ መረጃዎችን መስጠት አቁማለች ስትል ከስሳለች።

ዋሽንግተን ግን ክሱን "አሳፋሪ" በማለት ውድቅ አድርጋለች። ዜሌንስኪ ማክሰኞ ዕለት በሩሲያ የሚሳኤል ጥቃቶች ላይ ከአሜሪካ ጋር የደህንነት መረጃ ልውውጥ "አሁን እየተደረገ ነው" ብለዋል።

ዜሌንስኪ እና የአውሮፓ አጋሮቻቸው ዊትኮፍ ረቡዕ ዕለት ከፑቲን ጋር ሲገናኙ በኦስሎ ለተስማሙባቸው ሀሳቦች ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት የሩሲያ ነው ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የፊንላንድ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስቱብ ሰላምን ለማስፈን በሚቀርቡ ሀሳቦች ላይ "እውነተኛ ለውጥ" ታይቷል ብለዋል። ምንም ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ትዕግስት እንደሚያስፈልግ አስጠንቅቀዋል።

ዊትኮፍ ማክሰኞ ዕለት በኖርዌይ ዋና ከተማ ከተካሄደው ውይይት በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አልተገኙም። ሌላኛው የልዩ መልዕክተኛው አባል የሆኑት የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር በቪዲዮ በስብሰባው ላይ ተሳትፈዋል።

አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን በኋላ ላይ ውይይቱን "በጣም ውጤታማ እና ገንቢ" ሲሉ ገልጸውታል።

"በቀጣይ እርምጃዎች" ላይ በአሜሪካ፣ በዩክሬን እና በአውሮፓ መካከል "ገና እየዳበረ ያለ ጠንካራ ቅንጅት" እንዳለ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ዊትኮፍ ረቡዕ በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን አግኝተው በቀረቡ ሀሳቦች ላይ ለመወያየት ቀጠሮ እንዳላቸው እና ኩሽነር ይህንንም ስብሰባ በቪዲዮ እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል።

ፑቲን በቅርብ ጊዜ ስለተደረጉ ውይይቶች እና ድርድር ጥረቶች እስካሁን ድረስ በይፋ አስተያየት አልሰጡም። ነገር ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ ቀደም ብለው ክሪሜሊን ዊትኮፍ የሚያቀርቡትን ሃሳብ እንደሚያዳምጡ እና "ምንም አይነት የፖለቲካ ስምምነት" እንደማያደርጉ ተናግረዋል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በዩክሬን እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት እየተበላሸ በመምጣቱ ትራምፕ ዩክሬን አዲስ ፕሬዝዳንት የምትሾምበት ጊዜ አሁን ነው" በማለት "በቅርቡ ሌላ ሰው ዩክሬንን ወክሎ እንዲደራደር" ጠይቀዋል።

ትራምፕ ዩክሬን በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያዎች ላይ የፈጸመችውን ጥቃት አሜሪካ በኢራን ላይ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እየጨመረ ለመጣውን የነዳጅ ዋጋ ተጠያቂ በማድረግ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ በኦስሎ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ትራምፕ በዋይት ሐውስ ለተገኙ ጋዜጠኞች ኪየቭ "ስምምነት ላይ እንድትደርስ" እንደሚፈልጉ በድጋሚ ተናግረዋል። ሩሲያ "ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች" ካሉ በኋላ "ዩክሬን ይህንን ጦርነት የምታቆምበት ጊዜ ደርሷል" ብለዋል።

ፑቲን በ2022 ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ በመውረር በአሁኑ ጊዜ 20 በመቶ የሚሆነውን ግዛቷን ተቆጣጥረዋል።