በኦሮሚያ ክልል ሁለት ወረዳዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ስድስት ሰዎች መገደላቸው እና ቢያንስ አምስት ሰዎች መታገታቸው ተገለጸ

ታጣቂዎች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በኦሮሚያ ክልል ሽርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ በሚባሉ ወረዳዎች ባለፈው ሳምንት ከጥቅምት 2 እስከ 7/2019 ዓ.ም. ድረስ በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የቢቢሲ ምንጮች ተናገሩ።

ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪ እና የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንደተናገሩት፤ ጥቅምት 2፣ ሰንጎ ያያ ቀበሌ አንድ ሰው ሲገደል፤ ጥቅምት 7 ለ 8 አጥቢያ እሄላ ዘንባባ ቀበሌ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

"ጥቅምት 2 የተገለደው ሰው አዝመራ ላይ ነበር። ጥቅምት 7 ለ 8 አጥቢያ የተገደሉት አንድ ሴት እና አንድ ወንድ ቤታቸው ነበሩ" ሲሉ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንዳሉት ጥቅምት 2 ግድያው ከተፈጸመ በኋላ የሟቹን ከብቶች ጨምሮ ወደ "50 የሚደርሱ" የተለያዩ ነዋሪዎች ከብቶችም ተወስደዋል።

ሁለተኛው ጥቃት በተፈጸመበት ዕለት አምስት ሰዎች ታግተው መወሰዳቸውን አክለዋል።

"አንድ ቄስም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ሽርካ ሆስፒታል እየታከሙ ነው" ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ ነዋሪ ሐሙስ ዕለት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ ላይ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሦስቱ የላሎ ቀበሌ ነዋሪዎች የተገደሉት እርሻ ላይ እያሉ መሆኑን ገልፀዋል። በማግሥቱ በላሎ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቀብራቸውን መፈጸሙን አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ጥቅምት 5 በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ ሦስት መገደላቸውን አስታውቋል።

ከጥቅምት 2 አንስቶ የተገደሉ እና የታገቱ ነዋሪዎች እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸውን ካህን ስም ዝርዝርም አውጥቷል።

ቢቢሲ ግድያውን እና እገታውን በተመለከተ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ከኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስተያየት ለማግኘት የተደረገው ስልክ ጥሪ እና በፅሁፍ የቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

በቀድሞው የክልሉ ዞኖች አወቃቃር አርሲ ውስጥ በሚገኙት ወረዳዎች ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አምና ግንቦት ላይ በአርሲ ዞን ሦስት ወረዳዎች ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ 13 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደተፈናቀሉ ተዘግቧል።

በተጨማሪም አንድ ቤተ ክርስቲያን በእሳት የወደመ መሆኑን እና ሌላ ቤተ ክርስቲያን ላይ ዘረፋ እንዲሁም ጉዳት መድረሱን የአካባቢው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ በአርሲ ዞን በምዕመናን እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት መቀጠሉ "እስከ መቼ" የሚል ሐዘን ፈጥሯል ብለዋል።

አቡነ ማትያስ በአርሲ ሀገረ ስብከት በአሰኮ፣ በሽርካ፣ በሆንቆሎ፣ በዋቤ እና በሙኔሳ ወረዳዎች በተፈጸሙት ጥቃቶች "በመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ጥቃት የሰማነው በተሰበረ ልብ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንደገለጹት፤ ባለፉት ወራት ግድያዎች "ጋብ ቢሉም" እገታዎች ሲፈጸሙ ነበር።

"ገዳዮቹ ለምን ጋብ እንዳደረጉት አይታወቅም ነበር። አሁን ተመልሰው ጀመሩ" ብለዋል።

"ስላልተሰማ ነው እንጂ መሀል ላይ አንድ ሁለት እየተባለ የሚፈጸም [ጥቃት] ነበር። ግድያ ቆም ብሎ ነበር" ሲሉም አክለዋል።

ነዋሪዎች እየታገቱ "ሚዲያ ጋር ሳይደርስ በፊት" ክፍያ ሲፈጽሙ ቶሎ ይለቀቁ እንደነበርም አክለዋል።

ጥቅምት 2 የተገደለው ነዋሪ አዝመራው ላይ እንደነበርም ገልጸዋል።

"አዝመራው ላይ ሰውየውን ገድለው ከብቶቹን ወስደዋል። ከብቶቹን ለማሸሽ ሲሞክር ነው የገለዱት። ቀን 6 ሰዓት አካባቢ ነው የተገለደለው። ቢጮህም ማንም አልደረሰም።"

በአካባቢው የፀጥታ አካላት ቢኖሩም "የተደረገ ፍለጋም ክትትልም የለም" ብለዋል።

ባለፉት ቀናት ስለተፈጸሙት ግድያዎች እና እገታዎች ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ጥቅምት 5 የተገደሉት ሦስት ሰዎች መሆናቸውን አስታውቋል።

"ምዕመናን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገደሉ፣ ከቀያቸው እና ከንብረታቸው እየተፈናቀሉ እንዲሁም ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ የሚገኙ በመሆኑ፣ የሚመለከተው አካል እነዚህን ችግሮች አጣርቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ" አሳስቧል።

በተጨማሪም ከቀያቸው እና ከንብረታቸው ለተፈናቀሉ "አስፈላጊው ጥበቃ እና ክትትል" ተደርጎ እንዲመለሱ እንዲሁም ለተቀሩት የአካባቢው ነዋሪዎች "አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግ" ጠይቋል።

የቢቢሲ ምንጭ እንደገለጹት ጥቅምት 7 ለ 8 አጥቢያ ሌሊት ግድያ የተፈጸመባቸው ሰዎች "ቤታቸው" ውስጥ ነበሩ።

"የታገቱትም ከቤታቸው ነው የተወሰዱት። የተገደሉትንም ከየቤታቸው ነው" ብለዋል።

በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ቢኖሩም እንኳን "ከስጋት ነጻ" ሆነው እንደማያውቁ ገልጸዋል።

"አካባቢው ከችግር ከጻ ሆኖ አያውቅም፤ የስጋት ቀጣና ነው። በስጋት የሚወጣበት በስጋት የሚገባበት አካባቢ ነው።"

ከ2017 ዓ. ም. አንስቶ በሽርካ ወረዳ አራት ቤተ ክርስቲያኖች "አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን" አክለዋል።

"ቤተ ክርስቲያናቱ አጥራቸው ፈርሶ ተወስደዋል፣ ተሸጠዋል። ታቦታት ተነስተዋል። የ400 ክርሰቲያኖች ቤት ፈርሷል። ከስጋት በመነጨ በርካታ መሬት አልታረሰም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ሐምሌ 19/2018 ዓ. ም. ባወጣው በአርሲ ዞን ውስጥ በአራት ዓመታት በተፈጸሙ ጥቃቶች "458 ሰዎች" ሲገደሉ፤ "38 ነዋሪዎች ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም" ብሏል።

ከ2014 እስከ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. በዞኑ "የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን" የዳሰሰበት ሪፖርት "በአካባቢው የሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች የአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ሃይማኖትን መሠረት ባደረገ መልኩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ላይ" ጉዳት ማድረሳቸውን ያትታል።

የኢሰመጉ ባለሙያዎች ምርመራ ካካሄዱባቸው ዘጠኝ ወረዳዎች መካከል ሽርካ፣ መርቲ፣ ሆንቆሎ ዋቤ እና አሰኮ ይገኙበታል።

ያለፈው ዓመት ብሔራዊ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር "ንጹኃንን እና የሃይማኖት ተቋማትን ዒላማ በማድረግ የተፈጸሙ ጥቃቶች ዓላማቸው አገሪቱ እንዳትረጋጋ እና ምርጫውን ለማደናቀፍ የተደረገ ዕቅድ ተከታይ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ለጥቃቶቹ ተጠያቂ አድርገዋል። ታጣቂ ቡድኑ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ግድያዎች፣ እገታዎች፣ ማፈናቀሎች እና የንብረት ውድመቶች ቢወነጀልም ክሶቹን ያስተባብላል።

ተቃዋሚው የፖለቲካ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሰሞነኛዎቹን ጥቃቶቹን በተመለከተ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ በኦርቶዶክስ አማኞች እና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ይፈጸማሉ ያላቸውን ተደጋጋሚ "ግድያዎች፣ አፈናዎችና የግዳጅ ማፈናቀሎች በጽኑ" አውግዟል።

"በአርሲና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች" የሚፈጸሙት እነዚህ ድርጊቶች "ባስቸኳይ እንዲቆሙ" የጠየቀው ፓርቲው፣ የታገቱ ሰዎች "ያሉበት ቦታ በአስቸኳይ እንዲጣራ" እና "ያለምንም ጉዳት በአስቸኳይ እንዲለቀቁ" ጠይቋል።

መንግሥት "እስከዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ማንነትን እና ሀይማኖትን መሰረት በማድረግ ስለተፈጸሙ ድርጊቶች ኃላፊነቱን በመውሰድ" ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቧል። ጥቃቶቹ "በዓለም አቀፍ ገለልተኛ አካል በጥልቀት እንዲመረመሩ" ብሏል።

"የጥቃቶቹ ፈጻሚዎችና ከጀርባቸው ያሉ አካላት ማንነት በነፃ ምርመራ መጋለጥ አለበት" ሲልም አሳስቧል።

በአርሲ ዞን ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዩች በተጨማሪ ሙስሊሞች ላይም ጥቃቶች መድረሳቸው ከዚህ በፊት ተሰምቷል።

ቢቢሲ በተለያየ ጊዜ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጥቃቶች "የሃይማኖት እና የብሔር" መልክ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከሰሞኑ ከተፈጸሙ ግድያዎች እና እገታዎች ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ፤ ጥቃቶቹ "ሃይማኖት ተኮር" መሆናቸውን ያምናሉ።

እየሞተ፣ እየተገደለ፣ እየተሰደደ ያለውን ውጤቱን ስናይ ነው። [ሃይማኖት ተኮር] ባይሆን ኖሮ ሰው ተፈልጎ፣ ሰው ተመርጦ፣ ትኩረት ተደርጎ ይፈጸም ነበር? ሌላው ሰው በሰላም እየኖረ ነው። ክርስቲያን ተፈልጎ ነው እየተገደለ፣ እየተፈናቀለ፣ ቤቱ እየፈረሰ ያለው።"