የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሸን ሊቀ መንበር የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በአፋጣኝ እንዲቆም ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ውጥረት እና ወታደራዊ መካረር "እጅግ እንዳሳሰባቸው" ገለጹ። ግጭቱ "በአፋጣኝ እንዲቆምም" አሳስበዋል።
ዛሬ ረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ማምሻውን ባወጡት መግለጫ፤ የመቀለ፣ የአክሱም እና ሽረ አውሮፕላን ማረፊያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው፣ ህወሓት የፌደራል መንግሥት ሠራተኞችን መያዙ እና የሕዝብ አገልግሎት መስጫዎች መቋረጣቸው እንዳሰጋቸው አስታውቀዋል።
ረቡዕ ማለዳ ላይ የትግራይ ኃይሎች መቀለ የሚገኘውን አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠራቸው ከተገለጸ በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር ጦርነት መቀስቀሱ ተሰምቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ እና የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የህወሓት ኃይሎች "ጦርነት መክፈታቸውን" ገልጸዋል።
ትግራይን የሚያስተዳድሩት የህወሓት መሪዎች ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "ተከፈተብን" ያሉትን ጥቃት ለመከላከል ኃይሎቻቸው "እርምጃ እንዲወስዱ" መታዘዛቸውን ገልጸዋል።
የአፋር ክልል ኮምንኬሽን ቢሮ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ ህወሓት "ከዛሬ ሌሊት ጀምሮ በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን በአብአላ፣ በመጋሌ፣ በወሰማና በሌሎች አካባቢዎች" ላይ ጦርነት "መክፈቱን" ገልጿል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር፤ በደቡብ ትግራይ እና በአፋር ክልል ግጭት እየተባባሰ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።
አያይዘውም በቅርቡ በታጣቂ ኃይሎች የተፈጠረው ጥምረት "አለመረጋጋቱን እንደሚያባብስ" ገልጸዋል።
"ጥይትን ዝም በማሰኘት የተገኘውን ውጤት የሚቀለብስ" ሲሉም ጥምረቱ እንደሚያሰጋቸው በመግለጫው አስታውቀዋል።
ህወሓት፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን (ኦነሠ) ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የመሠረቱት 'የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና' የተባለው ይህ ጥምረት ዛሬ ባወጣው መግለጫ በፌደራል መንግሥቱ "በአየር እና በምድር መጠነ ሰፊ ጥቃቶች" እንደተከፈቱ ገልጿል።
በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል "ግጭትን በማቆም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት" ያለውን ሚና ሊቀ መንበሩ ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ ጠቅሰዋል።
ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተገታ በኋላ የስምምነቱ ተፈጻሚነት ላይ የፌደራል መንግሥቱም የትግራይ አመራሮችም ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል። ለተፈጠሩ ክፍተቶች አንዳቸው ሌላቸውን ሲወቅሱም ነበር።
ሊቀ መንበሩ በበኩላቸው ስምምነቱ "በኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና ሰላም የማዕዘን ድንጋይ ነው" ብለዋል።
በትግራይ ያሉ አውሮፕላን ማረፊያዎች መያዛቸው ከፕሪቶሪያ ስምምነት ኃላፊነቶች እና ግዴታዎች ጋር "እንደሚጣረስ" ጠቅሰዋል።
"ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የተደረገውን ከባድ ጥረት" የሚቀለብስ እንደሆነ በመግለጫቸው አክለዋል።
ይህንን መግለጫን ተከትሎ የህወሓት ከፍተኛ አመራር እና የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ በቀረበው ወቀሳ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
አቶ አማኑኤል፤ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በትግራይ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ የአየር ጥቃቶች ሲፈጸሙ በዝምታ ቆይተው አሁን የሰነዘሩት ወቀሳ "ፍትሐዊ አይደለም" ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የህወሓት ኃይሎች በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ቦታዎች በኩል ሙሉ ጥቃት መክፈታቸውን በመግለጽ ጦርነት መቀስቀሱ "እጅግ የሚያሳዝን" ክስተት ነው ብለዋል።
የህወሓት መሪዎች በበኩላቸው ኃይሎቻቸው ወደ መከላከል ውጊያ እርምጃ መግባታቸውን ገልጸው፤ ውሳኔው የተላለፈው የመንግሥት ኃይሎች ቀደም ብለው ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው ሲሉ ከስሰዋል።
የአፋር ክልል ኮምንኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ ጦርነት የተከፈተው በኪልበቲ ረሱ ዞን በአብአላ፣ በመጋሌ፣ በወሰማና በሌሎች አካባቢዎች መሆኑን አስታውቋል።
'የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና' በበኩሉ የጥምረቱ አባል ድርጅቶች "በተለይ በሰሜን ወሎ፣ በዋግሕምራ፣ በአፋር ክልል ሰሜናዊ ቀጠናዎች" ላይ "ፀረ ማጥቃት" እያደረጉ እንደሆነ ጠቅሷል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ በአፋጣኝ ግጭቱ እንዲቆም አሳስበዋል።
"ግጭቱን የበለጠ ሊያባብሱ የሚችሉ ሁሉም ድርጊቶች በአፋጣኝ እንዲገቱ" ጠይቀዋል።
በፕሪቶርያ ስምምነት መሠረት "ሳይዘገይ ወደ ቀጥተኛ ንግግር" መመለስ እንደሚያስፈልግ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ አጎራባች አገራት ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። አክለውም "ግጭቱ እንዲቆም እና ንግግር እንዲደረግ" ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት አሸማጋይ የሆኑት የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፤ ዲፕሎማሲያዊ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መጠየቃቸውን ሊቀ መንበሩ ገልጸዋል።
































