ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዲሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ የሕክምና ሙከራ ተጀመረ
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ዝርያን የሚያክም የሕክምና ሙከራ መጀመሩን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።
የመጀመሪያው ታካሚ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሕክምና መጀመሩን የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገልፀዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ 1,400 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ 438 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።
እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ ለሆነው 'ቡንዲቡግዮ' ለተባለው የኢቦላ ዝርያ የተፈቀደ ክትባት ወይንም ሕክምና የለም።
በዓለም የጤና ድርጅት የተደገፈው የአሁኑ ሕክምና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ባዮሜዲካል ኢንስትቲዩት፣ በቤልጂየም ትሮፒካል ሕክምና ኢንስቲትዩት እና በዩናይትድ ኪንግደሙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች በጋራ የሚሰጥ ነው።
በዓለም የጤና ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ጄኔቫ መግለጫ የሰጡት ዶ/ር ቴድሮስ፤ "በሁለት የሕክምና አይነቶች የክሊኒካል ሙከራ ተጀምሯል፤ የመጀመሪያው ታካሚም ገብቷል" ብለዋል።
"ባልተፈቀደ ሕክምና እንኳ ሰዎች ከበሽታው እያገገሙ ነው። ነገር ግን ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ ሕክምና ቢኖረን በእርግጥም ከዚህ በላይ ሕይወቶችን መታደግ እንችላለን" ብለዋል።
የኢቦላ ቫይረስ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በኡጋንዳ የተቀሰቀሰው ባለፈው መጋቢት ነበር። ከዚያም በዓለም ጤና ድርጅት የሕብረተሰብ የጤና ስጋት ተብሎ ታውጇል።
እስከ ሰኔ 23/2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የተጠናቀረ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 1,406 የተረጋገጡ የኢቦላ ኬዞች ተገኝተዋል። 438 ሰዎች ደግሞ በበሽታው የሞቱ ሲሆን በቫይረሱ እንደተያዙ የተጠረጠረ ተጨማሪ 301 ሰዎች አሉ።
20 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በተረጋገጠባት ዩጋንዳ ደግሞ በቫይረሱ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል። በፈረንሳይም አንድ ሰው በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል።
በሽታው በቫይረስ የሚከሰት ሲሆን፤ ቫይረሱ የአካል ክፍሎችን እና በሽታ የመከላከል ስርዓትን ያጠቃል።
ኢቦላ በተለምዶ እንስሳትን በተለይም የሌሊት ወፎችን የሚያጠቃ ሲሆን፤ አንዳንዴ ከተጠቁ እንስሳት ጋር በሚኖር ንክኪ በሰዎች ላይ ቫይረሱ ይሰራጫል።
ሰዎች በአብዛኛው የሚያዙት ተላላፊ የሆኑ ምልክቶችን ካሳዩ በኋላ ነው። ምልክቶችም ለመታየት ከሁለት እስከ 21 ቀናት ይወስዳል።
ምልክቶቹ በድንገት የሚከሰቱ እና እንደ ጉንፋን ወይም ወባ በሽታ የሙቀት መጨመር፣ ራስ ምታት እና ከባድ ድካም ይጀምራል።
ቫይረሱን ለመከላከል ስድስት ለሆኑት ለእያንዳንዱ የኢቦላ ዝርያዎች ክትባቶች መሰራት አለበት። ነገር ግን እስካሁን ሦስቱ ብቻ የበሽታ መነሻ እንደሆኑ ነው የሚታወቀው።