ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጃፓን የወሊድ እረፍት የወጡት ከንቲባ መነጋገሪያ ሆኑ
በምዕራብ ጃፓን የአንዲት አነስተኛ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሻኮ ካዋታ፤ የወሊድ እረፍት እንደሚወስዱ ሲያሳውቁ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ጉዳዩን በመገረም እንደሚመለከቱት ጠብቀው ነበር።
ይሁን እንጂ ዜናው ከጠበቁት በላይ አከራካሪ ሆኗል። የወሊድ እረፍቱ ከንቲባ ሻኮ ካዋታ ከገመቱት በላይ ማኅበረሰቡን የከፋፈለ ሁኔታ ፈጥሯል።
የወሊድ ምጣኔ ባሽቆለቆለባት ጃፓን ውስጥ ከንቲባ የሆኑት የ35 ዓመቷ ሴት፤ የሕዝብ ተመራጮች ለወሊድ እረፍት መውሰድ አለባቸው ወይ በሚል ርዕስ ብሔራዊ መከራከሪያ ሆነዋል።
"በጣም ተገርሚያለሁ፤ ምክንያቱም ምላሹ በጣም ትልቅ ነበር" ብለዋል ለቢቢሲ።
በአሁኑ ወቅት የአካባቢ ተመራጮች ልጆች ሲወልዱ እረፍትን የሚፈቅድ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ከንቲባዋ በይፋ የወሊድ እረፍት መውጣት አይችሉም። በአንፃሩ ከምክትሎቻቸው ውስጥ ለአንዱ በጊዜያዊነት ኃላፊነታቸውን ያስረክባሉ።
እቅዳቸውን ባለፈው መጋቢት በሰጡት መግለጫ ዘርዝረው ያሳወቁት ከንቲባዋ፤ ከወሊዳቸው በፊት ሁለት ወራት፤ ከወለዱ በኋላ ደግሞ ሁለት ወራት እረፍት ላይ እንደሚሆኑ አሳውቀዋል።
ይህ እርምጃቸውም በጃፓን የወሊድ እረፍት የወሰዱ የመጀመሪያዋ ከንቲባ በመሆን ታሪክ ሰርተዋል።
አማካኝ የሠራተኞች እድሜ 39 በሆነበት ቢሯቸው ሁሉም እንደደገፋቸው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በማኅበረሰቡ በኩል ግን ይህን ድጋፍ አላገኙም። በሺዎች በሚቆጠሩ የኤክስ ልጥፎች እና የዩቲዩብ ቪዲዮዎች ላይ የተለያዩ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል።
ልጅ መውለድ ከባድ እንደሆነ የሚያነሱ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ ከንቲባ ካዋታ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው ብለዋል። የጃፓን ማኅበረሰብ እርግዝናን ከግምት ውስጥ ያስገባ ስርዓት ባለመንደፉ ወድቋል ሲሉ አንድ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል።
ሌላኛው ደግሞ ካዋታ ቤተሰብን በማስቀደማቸው እና ሌሎች ሴቶች ወደ ፖለቲካ እንዲገቡ ቀለል በማድረጋቸው በጎ ተምሳሌት ሆነዋል ብለዋል።
ተቺዎች ደግሞ ማኅበረሰቡ ከጣለባቸው ኃላፊነት ዞር ማለታቸውን "ኃላፊነት የጎደለው" በማለት ያጣጣሉ ሲሆን መፀነስ ከፈልጉ "ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ማደረግ ነበረባቸው" እያሉ ነው።
አንድ አስተያየት ሰጪ ለረጅም ጊዜ እረፍት የሚወጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት "ሥራቸውን መልቀቅ አለባቸው" ብለዋል። ሌሎች ደግሞ በወሊድ እረፍቱ ወቅት ደመወዛቸው ሊቆረጥ ይገባል ሲሉ አንፅንኦት ሰጥተዋል።
ሥራቸውን እንደሚወዱ የሚገልጹት ከንቲባ ካዋታ ትችቶችን ወደ ጎን ብለዋቸዋል። ልጅ ለመውለድ እና ቤተሰባቸውን ለመጀመር ጊዜው አሁን ነው ብለው ያምናሉ።
"የወሊድ ፈቃድ የሚወጡ ፖለቲከኞችን ስንተች ይህ ማለት መፀነስ የሚችሉ ከ20ዎቹ እስከ 40ዎቹ ያሉ ሁሉንም ሴቶች ከሕዝባዊ ሥልጣኖች እያገለልን ነው" ሲሉ ሞግተዋል።
በሂሮሺማ ግዛት የአኪታካታ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ የሆኑት ሺንጂ ኢሺማሩ እውነተኛው ጉዳይ በወሊድ ፈቃድ ወቅት ኃላፊነቶችን እንዴት እንወጣ የሚለው እንደሆነ ያምናሉ።
በዩቲዩብ ገፃቸው የወሊድ ፈቃድ በጎ እንደሆነ ሰዎች እንደሚስማሙ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ሰሞነኛው ጉዳይ የማዘጋጃ ቤት ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ የሚያደርግ መፍትሔ ለማፈላለግ ገንቢ ውይይት እንዲያቀጣጥል ፍላጎት አላቸው።
ካዋታ በ33 ዓመታቸው የጃፓን በእድሜ ትንሿ የጃፓን ሴት ከንቲባ ሆነዋል። በወንዶች የበላይነት በተያዘው ፖለቲካ ቀስ በቀስ ወደ መሪነት መጥተዋል። እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ የጃፓን ከተሞችን ከሚመሩ ከንቲባዎች መካከል አራት በመቶዎቹ ብቻ ሴቶች ናቸው።
ምንም እንኳ አገሪቱ በመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር እየተመራች ቢሆንም የጃፓን መንግሥት ሴቶች ወደ ፖለቲካ እንዲገቡ አበረታች እርምጃዎችን ባለመውሰድ በተደጋጋሚ ትችቶች ይቀርቡበታል።
አንዳንዶች በወንዶች የበላይነት የሚመራውን ካቢኔ እና ጃፓንን ከአስርት ዓመታት የመራውን ገዢው 'ሊብራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ' የችግሩ አካል አድርገው ይመለከታሉ።
እ.አ.አ በ2025 ይፋ የሆነ የካቢኔ ጥናት፤ በርካታ መሰናክሎች ሴቶች ወደ ፖለቲካ እንዳይገቡ እንደሚያደርጉ ለይቷል። ከእነዚህም መካከል እርግዝና፣ ፖለቲካ የወንዶች ሚና ነው የሚል እምነት እና ትንኮሳ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ጃፓን የዓለማችን አራተኛ ባለግዙፍ ምጣኔ ሀብት ብትሆንም በስርዓተ ፆታ አመላካች ዝርዝሮች ግን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ናት።
በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ይፋ የሆነ የቅርብ ጊዜ ሪፖርት በስርዓተ ፆታ ከ147 አገራት ጃፓንን 118ኛ ላይ አስቀምጧታል። ጃፓን በፆታ እኩልነት በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ያላት የቡድን ሰባት አገር ናት።
ምንም እንኳ በአገሪቱ እረፍት እና ከፊል የገቢ ካሳን የሚሰጥ ሕጋዊ የወሊድ ፈቃድ ለእናቶች እና ለአባቶች ቢኖርም ሁሉም ሰዎች ግን የሚወስዱት አይደለም።
ሴቶች ከወሊድ በፊት ስድስት ሣምንት እና ከወሊድ በኋላ ደግሞ ስምንት ሣምንት የወሊድ ፈቃድ አላቸው። አባቶች ደግሞ ልጃቸው በተወለደ በስምንት ሣምንታት ውስጥ በፈለጉት ጊዜ መውሰድ የሚችሉት አራት ሣምንት እረፍት ይሰጣቸዋል።
"ሴት ከንቲባ ሆና ልጅ መውለድ በተግባር የሚሆን ነገር እንደሆነ በርካታ ሰዎች እየተመለከቱ ነው ብዬ አምናለሁ" ሲሉ ምክትል ከንቲባ ሺግቶ ኖስ ተናግረዋል።
ከንቲባ ካዋታ የወደፊት ልጃቸው በእርግዝናቸው ስለፈጠረው ትኩረት ምን እንደሚያስብ ሲጠየቁ ይህን ብለዋል።
"ሴት ሁለቱንም መስራት እንደምትችል እና ከሥራ እና ከቤተሰብ ለመምረጥ አለመገደድ መደበኛ የሚሆንበት ማኅበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ።"