"ከአባቴ የተሰጠኝ ምሕረት ለአሜሪካም ለአባቴ ሌጋሲም ጥሩ አልነበረም"- የጆ ባይደን ልጅ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ የሆነው ሀንተር ባይደን ከአባቱ የተሰጠው ምሕረት "ከማንም በላይ ዕድለኛ" እንዳደረገው ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃል ምልልስ ተናገረ።

ባይደን ከሥልጣን ሳይወርዱ በፊት ልጃቸው ከዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ተጠያቂነት ነጻ እንዲሆን ምሕረት ሰጥተዋል።

ሀንተር ባይደን ከአባቱ የተሰጠው ምሕረት "ለአሜሪካ እንዲሁም ለአባቴ ሌጋሲ ጥሩ አልነበረም" ብሏል።

ከቢቢሲ ኒውስናይት ጋር ባደረገው ቆይታ ስለተሰጠው ምሕረት፣ የአባቱ ካንሰር እየተስፋፋ ስለመሆኑ እና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አስተያየቱን ሰጥቷል።

በምርጫ የመወዳደር ፍላጎት እንደሌለው እና ሱሰኞች እንዲያገግሙ ስለ መርዳት አንስቷል።

በአውሮፓውያኑ 2024 በተሰጠው ይቅርታ ላይ የሚነሱ ትችቶችን እንደሚረዳ ጠቅሶ "አባቴ ያንን ባያደርግልኝ ኖሮ ስለ እሱ ምን ታስቡ ነበር" ብሏል።

"በቀላሉ ትችት የሚነሳበት ጉዳይ ነው፤ [ትችቱ] በቂ ምክንያትም አለው። ፍትሐዊ አይደለም። ስላደረገልኝ ደስተኛ መሆኔን ግን አውቃለሁ" ሲልም ተናግሯል።

የተሰጠው ምሕረት "ለአሜሪካውያን፣ ለሕገ መንግሥቱ እንዲሁም ለአባቱ ሌጋሲ ጥሩ እንዳልሆነ" ገልጿል።

አባቱ ምሕረት ያደረጉለት በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዒላማ ይደረጋል ብለው በመስጋት መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

"በዓለም ላይ ያንን ሊያደርግልኝ የሚችል ብቸኛ ሰው ከሆነው ከአባቴ ያንን [ምሕረት] ማግኘት የቻልኩኝ ብቸኛው ሰው ነኝ።"

ምሕረቱ ከመሰጠቱ በፊት በጉዳዩ ላይ ከአባቱ ጋር ምንም ዓይነት ውይይት አለማድረጋቸውን ገልጿል።

"እንደዚያ ያለ ውይይት አድርገን ለሕዝብ ይፋ ላይሆን የሚችልበት ዕድል የለም።"

ባይደን ለልጃቸው ሙሉ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለበት ምሕረት ያደረጉት ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

ይህንን ከማድረጋቸው በፊት፣ ከልጃቸው የሕግ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ጣልቃ እንደማይገቡ በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር።

ምሕረት እንደሚሰጡት ይፋ ሲያደርጉ ልጃቸው "ሆነ ተብሎ ተለይቶ፣ በኢ ፍትሐዊ መንገድ እንደተከሰሰ" ገልጸዋል።

ባይደን ለልጃቸው የሰጡት ምሕረት ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2024 ድረስ ያሉትን ዓመታት የሚሸፍን ነው።

በእነዚህ ዓመታት ሽጉጥ ከመግዛት እና ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ሀንተር ባይደን ላይ ክሶች ቀርበዋል። ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።

ሀንተር በቀን አንድ ጠርሙስ ቮድካ እስከመጨረስ እና በየ15 ደቂቃው ኮኬይን እስከመውሰድ የደረሰ ሱስ ውስጥ ተዘፍቆ እንደነበር ተናግሯል።

ያ ወቅት "በምድር ላይ ገሀነም ውስጥ የመኖር ያህል ነው፤ አንዳችም ደስ የሚል ነገር የለውም" ሲል ገልጿል።

አደንዛዥ ዕፅ እና መጠጥ ውስጥ የገባው "የፕሬዝዳንት ልጅ ስለሆንኩ ምንም አይደርስብኝም" በሚል ነው የሚሉ አስተያየቶች ቢሰነዘሩም እውነታው ይህ እንዳልሆነ ተናግሯል።

ወደ ሱስ የገባው ከጭንቀት እና ብቸኛነት ለመሸሽ መሆኑን በመጥቀስም "መርሳት ውስጥ መግባት ብቻ ነበር የምፈልገው" ሲልም ገልጿል።

አደንዛዥ ዕፅ እና መጠጥ መፍትሔ ቢመስሉም "ሊገድሉኝ ከጫፍ አድርሰውኝ ነበር" ይላል።

ሀንተር ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርግ በተለይም ስለ አባቱ ጤና ሲናገር ስሜታዊ ሆኖ ነበር።

"ካንሰር በጣም ከባድ ነው። ይሄንን መመልከት እጅግ ያሳዝናል" ብሏል።

የጆ ባይደን ካንሰር "እንደተስፋፋ እና ወደ አጥንታቸው ዘልቆ እንደገባ" ተናግሯል።

ይህም "ከፍተኛ ሕመም እንዳስከተለ እና አቅም እንዳሳጣቸው" ገልጿል።

"አባቴ እስከዛሬም ድረስ የቤተሰባችን ማዕከል ነው። ድንቅ አባት፣ ድንቅ ባል፣ ድንቅ አያትም ነው። አባቴ ስለ ጤናው ብዙ እያማረረ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር።"

ሰኔ 2024 የተደረገውን እና የአባቱን የፖለቲካ ሕይወት የገታውን ፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ክርክር በተመለከተም አስተያየቱን ተጠይቋል።

ካሊፎርንያ በሚገኘው ቤቱ ክርክሩን ሲመለከት አንዳች ትክክል ያልሆነ ነገር መኖሩን እንደተገነዘበ ገልጿል። "ደነገጥኩ፤ የሆነ ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ ታወቀኝ" ብሏል።

ከዚህ በፊት ስለ አባቱ የክርክር ብቃት መዳከም ሲናገር መንስዔው በብዙ ጉዞ ምክንያት የተከሰተ አካላዊ ድካም እንደሆነ ተናግሯል።

ጆ ባይደን ካንሰር እንዳለባቸው ከታወቀ በኋላ ምናልባትም ጫና እያሳደረባቸው የነበረው ሕመሙ ሊሆን ይችላል ብሎም ልጃቸው ገምቷል።

አባቱ አሁንም ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ እንዳላቸው እና በአደባባይ መናገር እንደሚቀጥሉም ገልጿል።

ሀንተር ባይደን ወደ ፖለቲካ እንደሚገባ እና ለፕሬዝዳንትነትም ሊወዳደር እንደሚችል ጭምጭምታዎች መሰማታቸውን በተመለከተ "በምርጫ ለመወዳደር እና ለፖለቲካም ምንም ፍላጎት የለኝም" ሲል አቋሙን ገልጿል።

ጊዜውን ማሳለፍ የሚፈልገው ሱሰኞች እንዲያገግሙ በመርዳት መሆኑን ተናግሯል። ይሄ ዓላማው የአሜሪካን ፖለቲካው ክፍፍል መጠገን የሚያስችል መሆኑን ያምናል።

"ሱስ እና ከሱስ የማገገም ተስፋ ሁላችንንም ያስተሳስሩናል ብዬ አምናለሁ።"

አባቱን ሲያስብ ምን እንደሚያኮራው ተጠይቆም "ጽናቱ ያኮራኛል" ሲል መልሷል።

አባቱ ሥልጣን ላይ ከነበሩበት ወቅት ይልቅ "ጽኑነትን" እንደሚያደንቅ ተናግሯል።

"በጣም የምኮራው በጽናቱ ነው። ብትወድቅም መልሰህ መነሳት እንደምትችል ደጋግሞ አሳይቷል። ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ጠንካራው እሱ ነው።"