የአማራ ክልል መንግሥት በግጭቱ ምክንያት ተፈናቀሉ ያላቸው ከሁለት ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ወሰነ

አማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Amhara Communications

የምስሉ መግለጫ, 738 መምህራንን ጨምሮ ከሁለት ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች መደበኛ ሥራቸው ላይ አልነበሩም ተብሏል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአማራ ክልል መንግሥት መስተዳደር ምክር ቤት በክልሉ ከ2015 ዓ. ም. ጀምሮ በተቀሰቀሰው የትጥቅ ግጭት ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል ያላቸው 2,167 የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ወሰነ።

የክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት ባደረገው 6ተኛ ዙር 5ተኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ነው ይህን ውሳኔ ያሳለፈው።

በክልሉ ኮምኒኬሽን ቢሮ በኩል ይፋ የሆነው ይህ የምክር ቤቱ ውሳኔ በክልሉ የደረሰውን "ከፍተኛ" ጉዳት ጠቅሷል።

መግለጫው ፋኖን በስም ሳይገልፅ "የጥፋት ኃይል" ብሎ የገለፀው ሲሆን፤ ቡድኑን "ተናግረው" የተቀላቀሉ ያላቸው ሰዎች ወደ ሰላም እየተመለሱ ነው ብሏል።

"መንግሥት ዛሬም ሰላምን ለማስፈን ካለው ፅኑ እምነት በመነሳት" ውሳኔው መወሰኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ የፋኖ ታጣቂ ኃይሎችን ተቀላቅለው የነበሩ እና በፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራቸውን ጥለው የሄዱ እንዲሁም ከአምስት ዓመታት በፊት በጭልጋ እና አካበቢው በተፈጠረ ግጭት "በማንነታቸው ምክንያት የተባረሩ" የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ወስኗል።

መግለጫው ምን ያህሎቹ ታጣቂ ኃይሎችን ተቀላቅለው የነበሩ፤ ምን ያህሎቹ ደግሞ በስጋት ሥራቸውን የለቀቁ እንደሆኑ ለይቶ አላብራራም።

የክልሉ መንግሥት፤ የመንግሥት ሠራተኞች በምን መልኩ 'ከትጥቅ' እንዲመለሱ እንደተደረገ፤ በፀጥታ ችግር ምክንያት የተመደቡበትን ሥራ ጥለው የወጡ ሠራተኞች ከውሳኔው ባለፈ እንዲመለሱ የሚያስችል የተወሰደ እርምጃ ስለመኖሩም ያለው ነገር የለም።

በጭልጋ አካባቢ በነበረው ግጭት "በማንነታቸው ምክንያት የተባረሩ" ናቸው ያላቸው ሠራተኞችንም በሚመለከት ግልጽ መረጃ ያላወጣ ሲሆን፤ ከ2012 ዓ. ም. ጀምሮ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በቅማንት ታጣቂዎች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የግጭቱ ዋነኛ ምክንያት በ2008 ዓ. ም. በተደረገው የወሰን ማካለል ላይ ሦስት ቀበሌዎች ላይ አለመግባባቱ በመፈጠሩ ነው። በግጭቱ በንጹኃን እና በፀጥታ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።

ወደ ሥራ ገበታቸው ይመለሳሉ ከተባሉት ውስጥ 115ቱ "በማንነታቸው" ምክንያት ተሰናብተው የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች እንደሆኑ የክልሉ መንግሥት ገልጿል።

738 መምህራንን ጨምሮ ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት የመንግሥት ሠራተኞች አሁንም በቀጠለው የክልሉ ግጭት ምንክያት መደበኛ የሥራ መደባቸው ላይ ያልነበሩ ሲሆኑ፤ በምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረት ወደ ሥራቸው ተመልሰው "ከሚመደቡበት" ቀን ጀምሮ ደመወዝ ይከፈላቸዋል።

ሐምሌ 2015 ዓ. ም. የፋኖ ኃይሎች ዋና ዋና ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ ወደ ግጭት የገባው አማራ ክልል ግጭቱ እልባት ሳያገኝ እንደቀጠለ ነው።

ግጭቱ ሲቀሰቀስ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመፈፀሚያ ጊዜው ለካፈ በኋላም እንደቀጠለ ነው።

ምንም እንኳ መንግሥት ክልሉ "አስተማማኝ ሰላም" እየሰፈነበት ነው ቢልም፤ በክልሉ በነፃነት መንቀሳቀስም ሆነ የተረጋጋ መደበኛ ሕይወት እንደሌለ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በቅርቡ የክልሉ መንግሥት ከ33 በላይ የፋኖ ታጣቂዎች "የሰላምን አማራጭ" ተቀብለው ትጥቅ ፈትተዋል ሲል፤ የፋኖ ኃይሎች ደግሞ 'ማረክናቸው' እና 'ተቀላቀሉን' የሚሏቸውን የመንግሥት ወታደሮች በስም እየዘረዘሩ፤ በምሥልም ይፋ ያደርጋሉ።

በማስረሻ ሰጤ የሚመሩ ከፊል የፋኖ ኃይች በዓለም አቀፍ "አደራዳሪዎች" በኩል ከመንግሥት ጋር ተደረሰ የተባለ የሰላም ስምምነት ባለፈው ኅዳር ይፋ ተድርጓል።

ስምምነቱ "ሰላምን የሚያረጋግጥ" እና "ለሕዝቡ ትልቅ እፎይታ" የሚሰጥ ነው ቢባልም፤ ከስድስት ወራት በኋላ የስምምነቱ ትግበራን በተመለከተ ለሕዝብ ይፋ የተደረገ መረጃ የለም።

ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት ግጭቱን የገታ አይደለም።

የፋኖ ኃይሎች በስማቸው ተፈርሟል ያሉት ስምምነት በውግዘት በተለዩ አመራሮች የተፈረመ መሆኑን በመጥቀስ ስምምነቱን ውድቅ አድርገዋል።