በቬንዝዌላ በተከሰቱ ርዕደ መሬቶች ሳቢያ ቢያንስ 32 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቬንዝዌላ መዲና ካራካስ በሰከንዶች ልዩነት በተከሰቱ ሁለት ከፍተኛ ርዕደ መሬቶች ሳቢያ ቢያንስ 32 ሰዎች እንደሞቱ እና 700 ሰዎች እንደተጎዱ ተገለጸ።
በ7.5 ማግኒትዩድ የተለካው የመሬት መንቀጥቀጥ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ከተመዘገቡት ከፍተኛው ነው።
ሕንጻዎች ተንኮታኩተው ሲወድቁ ነዋሪዎች ነፍሳቸውን ለማዳን እየሮጡ ወጥተዋል።
የመጀመሪያው ርዕደ መሬት 7.2 ሁለተኛው ደግሞ 7.5 ሲሆን፤ የቬንዝዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ደልሲ ሮድሪገዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገዋል።
አውሮፕላን ማረፊያዎች የተዘጉ ሲሆን የባቡር መስመሮችም ሥራ አቋርጠዋል።
የመጀመሪያው ርዕደ መሬት በካራካስ ከተማ በስተምዕራብ በምትገኘው ያራኩይ ነበር የተከሰተው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም እንዳለው ርዕደ መሬቱ እስከ 22 ኪሎሜትር በሚደርስ ጥልቀት ነው የተከሰተው።
ከ39 ሰከንዶች በኋላ የተከሰተው ርዕደ መሬት እስከ 10 ኪሎሜትር ርቀት የሚደርስ ጥልቅት እንደነበረው ተገልጿል።
ሁለቱም የመሬት መንቀጥቀጦች ከመዲናዋ በቅርብ ርቀት ቢከሰቱም በመላው ከተማዋ ንዝረታቸው ተዳርሷል።
የተወሰኑ ሕንጻዎች ሲነቃነቁ፣ ፈርሰው የወደቁ እንዳሉም ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ንዝረቱ በ1,000 ኪሎሜትር ርቀት በምትገኘው የኮሎምቢያ መዲና ቦጎታም ተሰምቷል።
ከሁለቱ ርዕደ መሬቶች በመቀጠል ከ20 በላይ ድኅረ መንቀጥቀጦች በመላው ቬንዝዌላ ተከስተዋል። ይህም በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙት የባሕር ዳርቻዎች (ላ ጉዋሪያ፣ አርጉዋ፣ ካራቦቦ እነ ኣፋልኮን) ደርሷል።
የመሬት መንቀጥቀጦቹ የተከሰቱት ቬንዝዌላ ብሔራዊ ክብረ በዓል ላይ ሳለች ነው።
በአውሮፓውያኑ 1821 የስፔን ቅኝ ገዢዎችን የቬንዝዌላው የነጻነት ታጋይ ሳይመን ቦልቪየር ያሸነፉበት ቀን እየተዘከረ ነበር።
በአጠቃላይ በርዕደ መሬቱ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ እስካሁን ዝርዝር መረጃ አልወጣም።
ምሥሎች እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የሕንጻ ፍርስራሾች እና ነዋሪዎች በየመንገዱ ተሰብስበው ያሳያሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞች ከፈራረሱ ሕንጻዎች ሥር ሰዎችን ለማውጣት እየሞከሩ ይገኛሉ።
ጊዜያዊው ፕሬዝዳንቷ እንዳሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጨማሪ ግብዓት ለማግኘት እና የሰዎችን ሕይወት የመታደግ ሥራውን ለማፋጠን ይረዳል።
ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ባይጠቅሱም ለተጎጂዎች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።
ጎረቤት አገሮቹ ብራዚል፣ ኤል ሳልቫዶር እና ኢኳዶር እገዛ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
የቻኮዶ ከተማ ከንቲባ ጉስታቮ ዱዌዝ ሱዌዝ ሁለት ሕንጻዎች መፍረሳቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
500 የድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞች እንደተሰማሩ እና 18 ሰዎች በሕይወት ማትረፍ እንደተቻለ ገልጸዋል።
የቬንዝዌላ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ባወጣው ማሳሰቢያ ሕንጻዎች ሊፈርሱ ስለሚችሉ ዜጎች ከቤት ውጭ እንዲሆኑ ጠይቋል።
ወደ ዋና ከተማዋ የሚገባው ነዳጅ እንዲሁም ኢንተርኔት መቋረጡም ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአሜሪካ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም እንዳለው በርዕደ መሬቱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች 10,000 የሚደርሱበትን ዕድል በ36 በመቶ ይገመታል። 100,000 ሰዎች ሊሞቱ የሚችሉበት ዕድል ደግሞ 40% ይገመታል ብሏል።















