በኬንያ በተጠራ ተቃውሞ ምክንያት ፖሊስ ዋነኛ መንገዶችን ዘጋ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በኬንያ የታቀደውን አገር አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ፖሊስ ወደ ማዕከላዊ ናይሮቢ የሚወስዱ ዋነኛ መንገዶችን ዘጋ።
ኬንያውያን ወጣቶች ከሁለት ዓመት በፊት ያካሄዱትን የፀረ መንግሥት ተቃውሞ ለመዘከር ዛሬ ሐሙስ አገር አቀፍ ሰልፍ ጠርተዋል።
በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2024 የቀረበውን የግብር ዕቅድ በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያን አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ማሰማታቸው ይታወሳል።
ተቃውሞውን ተከትሎ አወዛጋቢውን የፋይናንስ ረቂቅ ምክር ቤት ውድቅ አድርጎታል።
ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲደረግ የጠሩት ወጣቶች፤ ባለፈው ዓመት የፀረ መንግሥት ተቃውሞው ዝክር ሲካሄድ በፖሊስ የተገደሉ ከ80 በላይ ሰልፈኞች ፍትሕ እንዲያገኙ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።
ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የፀጥታ ኃይሎች ወደ ማዕከላዊ ናይሮቢ (ሲቢዲ) የሚወስዱ ዋነኛ መንገዶችን በመዝጋታቸው በርካቶች መጓጓዝ አልቻሉም።
የተቃውሞ ሰልፎች በናይሮቢ፣ በሞምባሳ እና በማዕከላዊ ኬንያ ከተሞች እንዲካሄድ ጥሪ ተደርጓል።
የተቃውሞ ሰልፎች ከመካሄዳቸው አስቀድሞ የፀጥታ ኃይሎች በዋነኛ የከተማ ማዕከሎች አካባቢ በስፋት ተሰማርተዋል።
በተለይ በናይሮቢ ከፍተኛ የፖሊስ ስምሪት እንደሚኖር ተገልጿል።
በመዲናዋ በቲካ አውራ ጎዳና፣ በሞምባሳ ጎዳና፣ በናይሮቢ-ናማንጋ አውራ ጎዳና፣ ኬንያታ ጎዳና፣ ዋያ ኪዌ መንገድ እና ሌሎችም ዋነኛ መተላለፊያዎች ፖሊሶች በብዛት ይታያሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ተቃዋሚዎች ሰላማዊ እንዲሆኑ እና ከነውጥ፣ ከዝርፊያ እንዲሁም ከንብረት ውድመት እንዲታቀቡ የአገሪቱ ባለሥልጣናት አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር ዜጎች የመቃወም መብት እንዳላቸው ጠቅሰው "ንብረት ለማውደም እና ነውጥ ለማስነሳት የሚሰማራውን እንደማይታገሱ" ገልጸዋል።
የፖለቲካ መሪዎች፣ የሲቪል ማኅበራት እና የሰብአዊ መብት ተቋማት ሰላማዊ ተቃውሞን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
ራስን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መግለጽን የአገሪቱ ሕገ መንግሥት እንደሚፈቅድም አስታውቀዋል።
የፕሬዝዳንቱ የቀድሞ ምክትል እና አሁን ቀንደኛ ተቺያቸው የሆኑት ሪጋቲ ጋቻጉዋ፤ በተቃውሞው ነውጥ ሊነሳ ስለሚችል 'ጀን ዚ' በተባለው የትውልድ ዘመን ውስጥ የሚካተቱት ወጣቶች ከአውራ ጎዳናዎች እንዲርቁ አሳስበዋል።
ኬንያውያን ተቃውሟቸውን ማሰማት የሚችሉበት መንገድ ከቤት አለመውጣት መሆኑን ፖለቲከኛው ተናግረዋል።
ከ2017 እስከ 2025 ባሉት ዓመታት ከተቃውሞ ሰልፍ ጋር በተያያዘ ለደረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ካሳ የሚሆን 15 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል።
የተመደበው ገንዘብ ወደ 2,000 ለሚጠጉ ተጎጂዎች እንደሚሰጥም ተገልጿል።
ሩቶ "ካሳው የነፍስ ዋጋ አይደለም። ቁስልን እና ማጣትንም አይተካም" ብለዋል።
የመብት ተሟጋቾች ግን ካሳው በቂ እንዳልሆነ፣ ግልጽነት እንደሚጎድለው እና አንዳንድ ተጎጂዎችን ማግለሉን በመጥቀስ ተቃውመዋል።
በቀጣይ ዓመት ምርጫ የሚጠብቃቸው ፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ቃል የገቧቸውን ድርጊቶች እንዳልፈጸሙም ተቃዋሚዎች ይናገራሉ።
ሩቶ ግን የሚቀርቡባቸውን ትችቶች አስተባብለው በቀጣይ ምርጫም እንደሚወዳደሩ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters















