የየመን ሁቲ ታጣቂዎች ወሳኝ የቀይ ባሕር ወደብ የሆነችውን ሞካን መቆጣጠራቸው ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, AL MASIRAH/Handout via REUTERS
የየመን ሁቲዎች፣ በሳዑዲ የሚደገፉ የመንግሥት ኃይሎችን በመርታት ስትራቴጂያዊ የሆነችውን በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘውን ሞካ የወደብ ከተማን መያዛቸውን ወታደራዊ ምንጮች እና የዐይን እማኞች ገለፁ።
በኢራን የሚደገፈው ቡድን ሞካን መያዙን ተከትሎ፣ ከባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ ያለው ርቀት 75 ኪሎ ሜትር ብቻ ሆኗል። ይህ ወሽመጥ እስያን እና አውሮፓን የሚያገናኝ እንዲሁም በቀይ ባሕር በኩል ለሚደረጉ የመርከብ ጉዞዎች ቁልፍ የሆነ የንግድ መስመር ነው።
ነገር ግን ሁቲዎቹ በዓለም አቀፍ የመርከብ እንቅስቃሴ ላይ ምንም ስጋት እንደማይፈጥሩ ገልጸዋል። ሆኖም ከሳዑዲ አረቢያ የሚመጡ መርከቦችን ዒላማ እንደሚያደርጉ በድጋሚ ዝተዋል።
ሳዑዲ አረቢያ የአሜሪካ እና የእስራኤል ጦርነት በባሕረ ሰላጤው የሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥን በአብዛኛው ከተዘጋ በኋላ የነዳጅ ምርቶቿን ለመላክ በቀይ ባሕር ላይ ጥገኛ ሆናለች።
በሁቲዎች፣ በየመን መንግሥት ኃይሎች እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ያለው ግጭት መባባሱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል።
ሁቲዎቹ ከአንድ ሳምንት በፊት በየመን ደቡብ ምዕራብ ክፍል ጥቃት ከጀመሩ ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የየመን መንግሥትን የሚደግፈው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምረት፣ በምዕራብ የመን በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ላይ የአየር ድብደባዎችን ፈጽሟል። ሁቲዎች ደግሞ በአጸፋው በደቡብ ሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ከተሞች እና የነዳጅ ተቋማት ላይ የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃት አድርሰዋል።
የሞካ ነዋሪዎች እንዳሉት፣ የሁቲ ተዋጊዎች ከተማዋን የተቆጣጠሩት ረቡዕ ምሽት መንግሥትን ከሚደግፉ ኃይሎች ጋር ከባድ ውጊያ ካደረጉ በኋላ ነው። በዚህም ሳቢያ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።
የወደብ ከተማዋ በሁቲዎች እጅ የወደቀችው በድንገት መሆኑን የገለጠ አንድ የሞካ ነዋሪ፣ "በአካባቢው ድንጋጤ ተፈጥሮ የከተማው ነዋሪዎች በየመንገዱ ተጎድተው ወድቀው የነበሩ ሰዎችን የሚረዳ እንኳን በሌለበት አሳዛኝ ሁኔታ ለመሸሽ ተገደዋል" ሲል ለቢቢሲ አረብኛ ተናግሯል።
ሌላ ሰው ደግሞ ሐሙስ ዕለት የሁቲ ተዋጊዎች በሞካ ጎዳናዎች ላይ ጥበቃ ሲያደርጉ እንደነበር እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ንግድ ቤቶች ደግሞ ተዘግተው መዋላቸውን ገልጿል።
በርካታ የከተማዋ ተፈናቃዮች፣ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የየመን መንግሥት መቀመጫ ወደ ሆነችው በስተምሥራቅ ወደምትገኘው አደን ከተማ ነው ያመሩት።
ከልጆቻቸው ጋር መሸሻቸውን የገለፁ አንዲት እናት፣ "መኝታ አልቀረን፣ ቤት አልቀረን፣ ምንም የቀረ ነገር የለንም። ሁሉም ነገር በአንድ ሰዓት ውስጥ ወድሟል። አስቀድመም አላስጠነቀቁን ወይ ዕድል እንኳን አልሰጡንም" በማለት ከነቤተሰባቸው ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን አመልክተዋል።
ሞካ መያዟን በተመለከተ ከሁቲዎች በኩል ወዲያውኑ ማረጋገጫ አልተሰጠም።
ሆኖም የቡድኑ ከፍተኛ የፖለቲካ ምክር ቤት ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ "የሳዑዲ ጠላት ኃይሎች መባረራቸውን ተከትሎ በምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ያለው ግጭት ቆሟል" ማለቱን በሁቲዎች የሚተዳደረው አል ማሲራ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
አንድ የየመን ወታደራዊ ምንጭ ለኤኤፍፒ እንደገለፀው፣ ሁቲዎች የሮኬት እና የእግረኛ ጦር ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ በቀይ ባሕር የሚገኘውን እና ከሞካ 80 ኪሎ ሜትር ያህል የሚርቀውን ዙቃር ደሴትንም ተቆጣጥረዋል።
በየመን ፕሬዝዳንት የሚመራው የአስተዳደር ምክር ቤት ኃላፊ ራሻድ አል-አሊሚ፣ የየመንን የባሕር ዳርቻዎች ለመጠበቅ እና መንግሥት መልሶ እንዲቆጣጠራቸው የአረብ እና ሌሎች አገራት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሁቲ ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬያ፣ በባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የሳዑዲ ጦር አውሮፕላኖች በምዕራባዊ የመን በሚገኙ በቡድኑ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ይዞታዎች ላይ 64 የአየር ድብደባዎችን መፈፀማቸውን ገልፀዋል።
ከሳዑዲ ጦር በኩል ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ወዲያውኑ የተሰጠ አስተያየት የለም።
ሆኖም፣ ማክሰኞ ዕለት ሁቲዎች በደቡብ ሳዑዲ አረቢያ በርካታ ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ እና የድሮን ጥቃቶችን በመፈፀም 73 ሲቪሎችን ማቁሰላቸውን እንዲሁም በርካታ የነዳጅ ተቋማት በእሳት እንዲያያዙ ማድረጋቸውን የሳዑዲ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ለዚህም አፀፋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ሳዑዲ መራሹ ጥምረት ገልጿል።















