ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ውስጥ ታስረው ነበር የተባሉት ከ200 በላይ የሶማሊያ ወታደሮች ወደ አገራቸው ተመለሱ
የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው በመግባታቸው ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ታስረው ነበር የተባሉት የሶማሊያ ጦር አባላት እሁድ ዕለት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አንድ ሶማሊያ አገሪቱ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው ነበር የተባሉት ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ሳውዝ ዌስት ግዛት መመለሳቸውን የኤልበርዴ ወረዳ አስተዳዳሪ አብዲራህማን ኬይሬ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ቋንቋ አገለግሎት ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው፣ ወታደሮቹ የታሰሩት ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል። የአገሪቱ ሳውዝ ዌስት ግዛት ቴሌቪዥን ጣቢያ በበኩሉ ለሦስት ወር ገደማ መታሰራቸውን በዘገባው ጠቅሷል።
ሶማሊያ ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና ላይ የነበሩት ከ200 በላይ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መሻገራቸው የተሰማው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ነበር። ቢቢሲ ጉዳዩን ለማረጋገጥ ያደረጋቸው ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል።
ይሁን እንጂ የሶማሊያ መንግሥት የብሔራዊ ደኅነነት አማካሪ የሆኑት አዋይስ ሐጂ የሱፍ ከዚህ ቀደም ከአንድ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ የወታደሮቹን ወደ ኢትዮጵያ መሻገር አረጋግጠዋል።
የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የወታደሮቹን በኢትዮጵያ መገኘት እንደሚያውቅ ገልጸው፣ የሠራዊት አባላቱ የተጓዙት ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ እንደሆነም በወቅቱ ተናግረው ነበር።
ለቢቢሲ ሶማሊኛ ቋንቋ ቃለ መጠይቅ የሰጡት የኤልበርዴ አስተዳዳሪ እንደሚስረዱት ወደታሮቹ በማዕከላዊ ሶማሊያ በሚገኘው ጋልጋዱድ ክልል የተሰጣቸውን ወታደራዊ ሥልጠና አጠናቀው እየተመለሱ ነበር።
"ወታደሮቹ በመጀመሪያ የተመለመሉት ከእነዚህ የድንበር አካባቢዎች ነው፤ መጀመሪያ የነበሩበት ካምፕም የሚገኘው በኤልበርዴ ነው። ከዚያም በጋልጋዱድ ወደምትገኘው ሃናንቡሬ ለሥልጠና ተወሰዱ። ሥልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት በታደሙበት ሥነ ሥርዓት ተመርቀዋል። [ከዚያም] ቤተሰቦቻቸውን እንዲጠይቁ ከመንግሥት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል" ብለዋል።
አክለውም፣ ወታደሮቹ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ እያለፉ በነበረበት ወቅት ተይዘው ወደ ጅግጅጋ ከተማ እንደተወሰዱ እና ኋላም በድሬዳዋ ከተማ እንዲታሰሩ መደረጉን ገልጸዋል።
ወታደሮቹን ለእስር የዳረጋቸው ምክንያት በኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ተሰጥቷል ከተባለ "ወታደራዊ ሥልጠና ጋር" በማያያዝ በተሠራጨ ሐሰተኛ መረጃ ምክንያት ነው ብለው እንደሚያምኑ ባለሥልጣኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸው ወታደሮች እንቅስቃሴም ጥርጣሬ መፍጠሩን አክለዋል።
"ወታደሮቹ 222 ነበሩ። የመንግሥታት ሕጎች ደግሞ ይለያያሉ። ይህን ያህል ቁጥር ያለው ጦር የተሟላ መረጃ ሳይያዝ በአንድ ጊዜ ሲንቀሳቀስ ጥርጣሬ መፍጠሩ አይቀርም። ወታደሮቹን የያዟቸው የጸጥታ አካላት እንደነገሩን አስቀድሞ የደረሳቸው መረጃ አልነበረም ነበር" ብለዋል።
ይህንን ክስተት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ፌደራልም ሆነ ከሶማሌ ክልል መንግሥታት በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም።
ይሁን እንጂ የአገሪቱ ሳውዝ ዌስት ግዛት ቴሌቪዥን ጣቢያ ወታደሮቹ ወደ አገራቸው ሲመለሱ የነበረውን አቀባበል በተመለከተ ባሰራጨው የቪዲዮ ዘገባ ላይ የሶማሌ ክልል የጸጥታ አካላትን ደንብ ልብስ ያደረጉ ሰዎች ታይተዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል የጸጥታ አካላት፣ ወታደሮቹን ለሶማሊያ ባለሥልጣናት አሳልፈው እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል። አንዱ ግለሰብ "ስላደረጋችሁልን አቀባበል እናመሰግናለን። 220 የሚሆኑት ወታደሮች ለእናንት አሳልፈን እየሰጠን ነው። ይኸው ተሰልፈዋል፤ መቀበል ትችላላችሁ" ሲል ንግግር አድርጓል።
ሌላኛው የጸጥታ አካል ደግሞ "ከ220 ወታደሮች ውስጥ 17 ያህሉ ሴቶች ናቸው፤ የተቀሩት ወንዶች ናቸው" ሲል ተናግሯል።
ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ከአንድ ወር እስር በላይ ቆይተዋል የተባሉት ወታደሮች እሁድ ጥቅምት 15/2019 ዓ.ም. ወደ አገራቸውም መመለሳቸውን የኤልበርዴ አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል። ልጅ በመውለዷ ጅግጅጋ ከተማ ውስጥ ከቀረች አንዲት ሴት ወታደር በስተቀር፣ ሁሉም ወታደሮች መለቀቃቸውን ገልጸዋል።