አጫጭር ቪድዮ በመሥራት እስከ 160 ሺህ ዶላር የሚያገኙት ወጣቶች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ኤክኖር ሲንግ ስልኩ እና ጥሩ ኢንተርኔት እስካለው ድረስ በዓመት 160 ሺህ ዶላር አካባቢ ማግኘት እንደሚችል ይናገራል።

የ22 ዓመቱ ኤክኖር ለንደን ይኖራል። አጫጭር የቁም (ቨርቲካል) ቪድዮዎች እየሠራ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይለጥፋል። ገንዘብ የሚከፍሉት ደንበኞቹ ቪድዮዎቹ ከፍተኛ ዕይታ እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጋሉ።

እነዚህ አጫጭር ቪድዮዎችን የሚሠሩ ባለሙያዎች (ክሊፐርስ) ከፍተኛ ገንዘብ እያገኙባቸው ነው።

ኤክኖር "ክሊፖቹ ብዙ ተመልካች ሲያገኙ እኛም የምናገኘው ገንዘብ ይጨምራል" ይላል።

አልባሳት የሚሠሩ ባለሙያዎች፣ የሙዚቃ አዘጋጆች፣ የፊልም ስቱዲዮ ባለሙያዎች፣ ፖድካስት አዘጋጆች ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እነዚህ አጫጭር ቪድዮዎች እንዲሠሩ ገንዘብ ይከፍላሉ።

አጫጭር ቪድዮዎቹ የሚቀነጨቡት ዘለግ ካለ ቪድዮ ተቆርጠው ነው።

ከረዥሙ ቪድዮ ውስጥ ጥሩ የሆነው ከ30 እስከ 60 ሰከንድ ክሊፕ ይመረጣል። ከዚያም በኢንስታግራም፣ ዩቲዮብ፣ ቲክቶክ አልያም በሌላ ማኅበራዊ ሚዲያ ይጫናል።

አጫጭር ቪድዮዎችን የሚሠሩ 'ክሊፐሮች' በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 25 ዓመት ይሆናል።

በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ተመልካቾች ምን እንደሚፈልጉ ያውቃሉ። ቪድዮዎቹ በበርካቶች ዘንድ እንዲደርሱም ያደርጋሉ።

በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በ1,000 ተመልካች እስከ 3 ዶላር ይከፈላቸዋል።

ክሊፖች የሚያገኙት ተመልካች ቁጥር ሲጨምር ገቢውም ከፍተኛ ይሆናል።

ኤክኖር ክሊፖች መሥራት የጀመረው አምና ነው። የድምጻዊቷ ዱዋ ሊፓን ቪድዮ ኢንስታግራም ላይ ከጫነ በኋላ 300 ዶላር አገኘ። ወደ ሙያው የተሳበው ከዚህ በኋላ ነበር።

"አንድ ቪድዮ በመለጠፍ ብቻ ይሄን ያህል ገንዘብ ማግኘት ይቻላል ብዬ አሰብኩ። ምን ያህል ትርፋማ እንደምሆን አወቅኩ" ይላል።

አሁን ቢያንስ በወር እስከ 10 ሺህ ፓውንድ ያገኛል።

አስቂኝ፣ በፍጥነት የሚታዩ እና የተመልካቾችን ትኩረት የሚስቡ ክሊፖችን እንደሚመርጥ ይናገራል።

ዝነኞች ለየት ያለ ልብስ አድርገው በሚታደሙበት ዓመታዊው ገንዘብ ማሰባሰቢያ መሰናዶ (ሜት ጋላ) ለኤክኖር ከፍተኛ ገቢ አስገኝቷል።

ድምጻዊ እና ተዋናይት ሳብሪና ካርፔንተር ኒው ዮርክ ውስጥ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ያደረገችው ልብስ ረዘም ያለ ተጎታች ያለው ነበር። ልብሷን ሰዎች ሲረግጡ የሰጠችውን ምላሽ አጭር ቪድዮ በመቁረጥም በማኅበራዊ ሚዲያው አጋርቷል።

ይሄ ክሊፕ እንዲሠራ ማን ገንዘብ እንደከፈለው ኤክኖር አልገለጸም።

የ24 ዓመቱ ኢታን ዌምስ የሚኖረው አሜሪካ ካንሳስ ሲሆን እሱም እንደ ኤክኖር 'ክሊፐር' ነው።

የተለያዩ ቪድዮዎችን የሚሠራው ኢታን ከክሊፖች "በወር ቢያንስ እስከ 1,000 ዶላር" እንደሚያገኝ ይናገራል።

ዩቲዩበሩ እና ፖድካስት አዘጋጁ ካሌብ ሀመር ከሚሠራቸው ቪድዮዎች ክሊፖችን ቆርጦ በማውጣት ይታወቃል።

'ፋይናንሻል ሶዲት' በተባለው መሰናዶ የሚታወቀው ካሌብ የሚያቀርባቸው እንግዶች ስለ ሃብታቸው ያወራሉ።

ኢታን ከቪድዮው ውስጥ ክሊፖች ቆርጦ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማጋራት በሚያገኘው ገንዘብ ይተዳደራል።

ጥሩ ገቢ ስለሚያገኝ ሰፊ ጊዜ ከባለቤቱ እና ከአንድ ዓመት ልጁ ጋር ማሳለፍ መቻሉን ይናገራል።

"በየቀኑ ቢሮ የሚወስድና ከሦስት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት የሚያቆይ መደበኛ ሥራ አልፈልግም" ይላል።

የተወሰኑ 'ክሊፐሮች' ጥሩ ገቢ ቢያገኙም ሁሉም እንዳልሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ አማካሪ ሊያ ሀበርማን ትናገራለች።

"አብዛኞቹ የሚያገኙት ገንዘብ ውስን ነው" ትላለች።

ቪድዮ የማሠራጨት ሙያ ተንታኝ ዴቨን ናሽ እንደሚለው በዘርፉ ስኬታማ መሆን ቀላል አይደለም።

'ክሊፐሮች' "ለሰዓታት የሚዘልቁ ቪድዮዎችን መመልከት አለባቸው። ሙሉ ዓለማቸው እሱ ነው" ይላል።

ባለሙያዎቹን ከደንበኞች ጋር የሚያገናኙ ድረ ገጾች የሥራ ማስታወቂያ ዝርዝርም ያወጣሉ።

እንደ ሬዲት እና ዲስኮርድ ያሉ ማኅበራዊ ገጾች ላይ ክሊፖች ይለቀቃሉ። ለክሊፖች ብቻ የተዘጋጁ እንደ ክሊፒንክ ካልቸር፣ ቪይሮ፣ ውፕ እና ኪክ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችም ዝነኛ ናቸው።

ኪክ ከተለያዩ ኩባንያዎች ገንዘብ በመቀበል ክሊፖችን ያሠራጫል። ክሊፒንግ ካልቸር ደግሞ እንደ ካፒታል ሪከርድስ፣ ዩኒቨርሳል ሚውዚክ ግሩፕ እና ኤችቢኦ ማክስ ካሉ ኩባንያዎች ጋር ይሠራል።

በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ እና ቤታቸው ሆነው ክሊፕ የሚሠሩ ወጣቶችን መቅጠር ለኩባንያዎቹ አዋጪ ነው። ማስታወቂያ የሚሠሩ ተቋማት ከሚጠይቁት ገንዘብ አንጻር ወጣቶቹን መቅጠር ይቀላል።

ወጣቶቹ ተመልካቾችን ይስባሉ።

ተገጣጥመው የተሠሩ (ሞጁላር ሆምስ) አምራቹ ላስ ቬጋስ የሚገኘው ቦክስቤል ተቋም ማስታወቂያ የሚያሠራው በዚህ መንገድ ነው።

መሥራቹ ጋሊያኖ ቲማኒ "እስካሁን ድረስ በክሊፖች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾች አግኝተናል" ይላል።

ቀድሞ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አማካሪ ጂሚ ማክሎይን 'ጂሚስ ጆብስ ኦፍ ዘ ፊውቸር' የተባለ ፖድካስት ያዘጋጃል።

"ክሊፖች ዋናውን መሰናዶ ለማስተዋወቅ ይረዳሉ" ሲል ይገልጻል።

በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ ቡርንሃም ጋር የተደረገ ሙሉ ቆይታ 50,000 ጊዜ ሲታይ፣ ከቪድዮው የተቆረጡ ክሊፖች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተመለከቷቸው ይናገራል።

የክሊፒንግ ካልቸር መሥራች እና ኃላፊ ኢቫን ስታንፊልድ 21 ዓመቱ ነው።

አምና ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ካንሳስ ትምህርቱን አቋርጦ ነበር ድረ ገጹን የከፈተው።

ድረ ገጹ 340 ሺህ የሚደርሱ 'ክሊፐሮችን' በመላው ዓለም ከሚገኙ ከኩባንያዎች ጋር እንደሚያገናኝ ይናገራል።

ክሊፖች ዝነኛ የሆኑት "ሰዎች ዘለግ ላለ ነገር ትኩረት መስጠት ስለቀነሱ ነው" ሲል ያስረዳል።

አብዛኞቹ የክሊፕ ተመልካቾች ወጣቶች ስለሆኑ 'ክሊፐሮችም' ወጣቶች መሆናቸውን ይገልጻል።

ወጣቱ ኤክኖርም "ያለ ማቋረጥ ክሊፕ እቆርጣለሁ። የትም ቦታ ሆኜ መሥራት እችላለሁ። እረፍት ላይ ብሆንም እንኳን ገንዘብ አገኝበታለሁ" ይላል።