ኢራን፣ ፓኪስታን፣ ሳዑዲ እና ቱርክ የቀጣናውን ደኅንነት “ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት” ለማስጠበቅ መስማማታቸው ተገለጸ
የኢራን፣ ፓኪስታን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቴህራን በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
የኢራን ከፍተኛ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ ሞሼን ራይዚ “ቀጣናዊ ደኅንነት ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት መረጋገጥ አለበት” የሚል ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ገልጸዋል።
አሜሪካ እና ኢራንን እያደራደሩ ያሉት የፓኪስታን ጦር ኃይሎች አዛዥ አሲም ሙኒር፣ የሳዑዲ አረቢያ የመከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሰልማን እና የቱርክ የደኅንነት ኃላፊ ኢብራሒም ካሊን በቴህራኑ የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተዋል።
ሞሼን ራይዚ ለኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፤ እስራኤል ከደቡብ ሊባኖስ፣ ደቡብ ሶሪያ፣ ጋዛ፣ ዌስት ባንክ እና ዮርዳኖስ ወንቅ መውጣት እንዳለባት የውይይቱ ተሳታፊዎች ተስማምተዋል።
የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺም በውይይቱ ተገኝተዋል።
የኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት፤ የፓኪስታን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በቴህራን መገኘታቸው “የአሜሪካ ማስፈራሪያ ውጤታማ እንዳልሆነ እንደሚያሳይ” ገልጿል።
ውይይቱ ቀጣናዊ አንድነትን ለማረጋገጥ “ተጨባጭ ጅማሮ” እንደሚሆን ተስፋ እንዳለውም አስታውቋል።
የኢራን፣ ሳዑዲ፣ ቱርክ እና ፓኪስታን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቴህራን እንደሚወያዩ ካስታወቁ በኋላ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እንዳይባባስ ማድረግ “ወሳኝ ነው” ብለዋል።