አርሲ ውስጥ ባለፉት ዓመታት በተፈፀሙ ጥቃቶች ብዙ ሰዎች የተገደሉባቸው የትኞቹ ናቸው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በኦሮሚያ ክልል በአዲሱ አደረጃጀት በደቡብ ምሥራቅ ዞን ሥር በተካተተው የቀድሞው አርሲ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተፈፅመዋል።

በዋናነት ማንነት እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ እንደሆኑ የሚነግርላቸው እነዚህ ጥቃቶች አሁንም የቀጠሉ ሲሆን የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። በተጨማሪም በርካቶች የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው፣ አስገድዶ መሰወር፣ መፈናቀል እና ከፍተኛ የንብረት ውድመትም አስከትለዋል።

በአካባቢው በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመው ማንነት ተኮር ጥቃት በ2014 ዓ. ም. መጀመሩን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል። ከ2016 ዓ. ም. ወዲህ ደግሞ ጥቃቱ ተባብሶ መቀጠሉን ኢሰመጉ በዚሁ የምርመራ ሪፖርቱ ገልጿል።

ከ2014 ዓ. ም. ጀምሮ እስካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ድረስ ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ በአርሲ በተፈፀሙት ጥቃቶች "458 ሰዎች" ሲገደሉ፤ "38 ነዋሪዎች ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ በሥፍራው ባለሙያዎችን አሰማርቶ ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡን ኢሰመጉ አስታውቋል።

ይህ ሪፖርት ይፋ ከሆነ በኋላም የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፉ መሰል ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተፈፅመዋል። ከ2016 ጀምሮ የተፈፀሙትን ዋና ዋና ጥቃቶች በዚህ ዘገባ ዳስሰናል።

ጥቅምት 2019 ዓ. ም.

በሽርካ ወረዳ በሳምንት ልዩነት ውስጥ በተፈጸመ አዲስ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሕጻናትን ጨምሮ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸው ሦስት የዐይን እማኞች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሦስት የቀበሌው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ቅዳሜ ጥቅምት 14/2019 ዓ. ም. ንጋት ላይ በጀመረው ጥቃት በአጠቃላይ "46 ሰዎች" ተገድለዋል። ሟቾቹ በአካባቢው በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን "በአንድ ጉድጓድ" መቀበራቸውንም የዐይን እማኞች እና የተጎጂ ቤተሰቦች ገልፀዋል።

በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል አደረጃጀት በአርሲ ዞን ሥር በነበረው ሽርካ ወረዳ ቢርቢሩ ጮሌ ቀበሌ ቅዳሜ ዕለት በተፈፀመው ጥቃት "20 ገደማ" የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ነዋሪዎች አስረድተዋል።

ሆስፒታል የገቡት ሰዎች "በጣም በከባዱ የተጎዱ ናቸው" ያሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሟቾቹ ቁጥር "ሊጨምር እንደሚችልም" ስጋታቸውን ገልፀዋል። ሆስፒታል ከገቡ ተጎጂዎች መካከል ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 16/2019 ዓ. ም. የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን አንድ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል።

የሽርካ ወረዳ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ የቢቢሲ ምንጭ፣ የትናንቱን ጥቃት "እስካሁን ከተደረጉት ድርጊቶች ትልቁን ቁጥር የያዘ ነው" ብለዋል።

የቅዳሜውን ጥቃት በሽርካ ወረዳ በአንድ ሳምንት ልዩነት ውስጥ የተፈፀመ ሁለተኛው ጥቃት ነው።

ከጥቅምት 2 እስከ 7/2019 ዓ .ም. ባሉት ቀናት በሽርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና በትንሹ አምስት ሰዎች መታገታቸውን ነዋሪዎች ተናግረው ነበር።

ጥቅምት 3 ሌሊት ደግሞ አጎራባች በሆነው መርቲ ወረዳ ጎራ ሲሊንጎ ቀበሌ ከ15 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አንድ የወረዳው ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግንቦት 2018 ዓ. ም.

በቀድሞው የአርሲ ዞን ሁለት ወረዳዎች ግንቦት 23 እና 24/ 2018 ዓ. ም. በተፈፀሙ ጥቃቶች ቢያንስ 13 ሰዎች መገደላቸውን እና አንድ ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን ነዋሪዎች እና የአካባቢው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገረ ስብከት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአካባቢው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎችን ስም ዝርዝር ይፋ ደያረጉ ሲሆን፣ የአካባቢው አስተዳደር ባለሥልጣናት ደግሞ ስለተፈጸመው ጥቃት እና ስለደረሰው ጉዳት መረጃ እንደሌላቸው ገልፀዋል።

ጥቃቱ እሑድ ግንቦት 23/2018 ዓ. ም. መጀመሩን የተናገሩት የቢቢሲ ምንጮች፣ በስልጣና ወረዳ ልዩ ስሙ በቼቶ በተባለ አካባቢ ሁለት፣ በአሰኮ ወረዳ ደግሞ 11 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመበት የአርሲ እና ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ባወጡት መግለጫ፣ በሁለቱ ቀናት ውስጥ በአርሲ በተፈፀሙት ጥቃቶች "13 ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸውን፣ ከ280 በላይ ምዕመናን መፈናቀላቸውን እና የ101 ዓመት ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን" አመልክተዋል።

ይህን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በምዕመናን እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚፈፀመው ጥቃት መቀጠሉ "እስከ መቼ" የሚል ሐዘን እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ፣ ንጹኃንን እና የሃይማኖት ተቋማትን ዒላማ በማድረግ የተፈፀሙ ጥቃቶች ዓላማቸው "አገሪቱ እንዳትረጋጋ እና ምርጫውን ለማደናቀፍ የተደረገ ዕቅድ ተከታይ ነው" ሲሉ ገልፀዋል።

ለጥቃቱ "ኦነግ ሸኔ"ን ተጠያቂ ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ፣ በፀጥታ ኃይሎች "በተወሰደበት እርምጃ ፍላጎቱን ማሳካት ባለመቻሉ ስስ ዒላማዎች ላይ በማተኮር የሃይማኖት እና የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ" በአርሲ ዞን ጥቃት ፈጽሟል ሲል ታጣቂ ቡድኑን ወንጅሏል።

መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው እና ኦነግ ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በጥቃቱ ውስጥ እጁ እንደሌለበት በመግለጽ አስተባብሏል።

የካቲት 2018 ዓ. ም.

በቀድሞው የአርሲ ዞን ከየካቲት 15/2018 ዓ. ም. ጀምሮ አንድ ሳምንት በሚሆን ጊዜ ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከጥቃቶቹ ውስጥ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው ሐሙስ የካቲት 19/2018 ዓ. ም. እንደሆነ ምንጮቹ አስረድተዋል። በሽርካ ወረዳ ጃዊ ዋጩ ቀበሌ በተፈፀመው በዚህ ጥቃት 19 ሰዎች እንደተገደሉ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸውን ሦስት ምንጮች እንደተናገሩት፤ በማግሥቱ አርብ ከቀኑ 9 እስከ 10 ሰዓት ገደማ በዚሁ ቀበሌ በተፈፀመ ሌላ ጥቃት ደግሞ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል። አምስት ሰዎች ደግሞ ታግተው መወሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ገልፀዋል።

ማክሰኞ የካቲት 17/2018 ዓ. ም. ደግሞ በመርቲ ወረዳ ፈቀርሳ ቀበሌ በተፈፀመ ጥቃት አራት ሰዎች እንደተገደሉ እና እሑድ የካቲት 22 ምሽት በተፈፀመ ጥቃት ደግሞ ቢያንስ ሁለት ሰዎች እንደተገደሉ ከዐይን እማኞች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ጥቅምት 2018 ዓ.ም

በጥቅምት ወር 2018 ዓ. ም. በቀድሞው የአርሲ ዞን በጉና፣ በመርቲ፣ በሽርካ እና በሆሎንቆ ዋቤ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ "ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች" በተፈጸሙ ጥቃቶች ሕጻናትን ጨምሮ 25 ሰዎች መገደላቸውን የተጎጂዎች ቤተሰቦች እና በአካባቢው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ገልፀዋል።

በጥቃቶቹ ከተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች ውስጥ "ስምንቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት" እንደሆኑ አራት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሟቾቹ በተጨማሪ፣ የአራት እና የስምንት ዓመት ሕጻናትን ጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ነበሩ።

መጋቢት 2016 ዓ. ም.

መጋቢት ወር 2016 ዓ. ም. በአርሲ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከተፈፀሙባቸው ጊዜያት አንዱ ነው።

በዚህ ወር ውስጥ ታጣቂዎች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት እና ምዕመናን ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የቤተ ክርስቲያኗ ምንጭ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በቀድሞው አርሲ ዞን ሥር በሚገኘው የዶዶላ የደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሁለት አገልጋዮች ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው መጋቢት 16/2016 ዓ. ም. መገደላቸውን የቤተ ክርስቲያኗ ምንጮች ገልፀዋል።

ሁለቱ አገልጋዮች ከአምስት ቤተሰቦቻቸው ጋር በጥይት የተገደሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም መጋቢት 8 እና 15 በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ሌሎች ሰዎች የተገደሉባቸው ጥቃቶች ተፈፅመዋል።

በምሥራቅ አርሲ ዞን የቤተክርስቲያኗ አገልጋይ የሆኑ ቄስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ቤተክርስቲያንን እና ምዕመናንን ዒላማ ባደረጉ ጥቃቶች ከመስከረም 2016 ዓ. ም. ወዲህ በአካባቢው ከ80 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል።

ኅዳር 2016 ዓ. ም.

ኅዳር ወር 2016 ዓ.ም ላይ በቀድሞው አርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች 36 ምዕመናን መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።

ቤተ ክርስቲያኗ፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ያለቻቸው እነዚህ ጥቃቶች የተፈፀሙት በሽርካ ወረዳ ሶሌ ሚካኤል፣ በዲገሎ ማርያም፣ በሮቤ እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ማርያም አብያተ ክርስቲያናት እንደሆነ ገልጻለች።

ከተገደሉት ምዕመናን መካከል 28ቱ በሶሌ ዲገሉ እና ጢጆ ለቡ በተባሉ ቀበሌዎች ከየቤታቸው ተወስደው መገደላቸውን ያተተው መግለጫው፣ የጥቃቱ ሰለባዎች ዕድሜያቸው ከሃያ ስምንት ቀን ጨቅላ እስከ 70 ዓመት አዛውን እንደሚደርስ ጠቅሷል።

ሮይተርስ የዜና ወኪልም ኅዳር 14 እና 17/2016 ዓ. ም. በአካባቢው ታጣቂዎች በሦስት መንደሮች ላይ በፈፀሙት ጥቃት ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

ተጠያቂው ማን ነው?

የተጠቀሱትን ዋና ዋና ጥቃቶች ጨምሮ ከአራት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በተለይም ከ2016 ዓ. ም. ወዲህ በአርሲ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረጉ በርካታ ጥቃቶች በየጊዜው ተፈፅመዋል።

ማባሪያ ያጣው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመው ይህ የአርሲው ጥቃት ብዙዎችን ያስቆጣ ድርጊት ቢሆንም እስካሁን ለጥቃቶቹ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።

አሁን በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምስራቅ ዞን ሥር በተጠቃለለው በቀድሞው አርሲ ዞን ውስጥ ለተፈፀሙት ለብዙዎቹ ጥቃቶች መንግሥት 'ሸኔ' ሲል የሚጠራውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተጠያቂ ሲያደርግ፣ ውንጀላውን የሚያስተባብለው ታጣቂ ቡድኑ በተቃራኒው ለጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ይከስሳል።

ይሁን እንጂ፣ መንግሥት ሕዝቡን የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት አለመቻሉ ንፁኃንን ዒላማ ያደረገው ጥቃት በተደጋጋሚ እንዲፈፀም እና እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል በሚል የሰብአዊ መብት ተቋማት እና በርካታ ዜጎች ይተቻሉ።

አብዛኛውን ጊዜ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በዝምታ የሚያልፈው መንግሥት፣ አልፎ አልፎ ጥቃቶች ሲፈፀሙ በሚሰጣቸው መግለጫዎች ግን የጥቃቱ ፈፃሚ ናቸው ብሎ በሚፈርጃቸው ታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ይገልጻል።

ባለፈው ቅዳሜ ቅዳሜ ጥቅምት 14/2019 ዓ.ም በደቡብ ምሥራቅ ዞን ሺርካ ወረዳ ቢርቢሩ ጮሌ ቀበሌ ንፁኃን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን ያረጋገጡት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ በዚህ ጥቃት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች መኖራቸውን ቢገልፁም የሟቾቹን ቁጥር አልጠቀሱም።

በሽብርተኝነት የተፈረጀውን እና "ኦነግ ሸኔ" ያሉትን ታጣቂ ቡድን ለጥቃቱ ተጠያቂ አድርገዋል።

እስካሁን የሚቀርቡበትን መሰል ክሶች የሚያስተባብለው እና መንግሥትን መልሶ የሚከሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ስለአሁኑ ክስ በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም።

መንግሥት በታጣቂ ቡድኑ ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝም አቶ ኃይሉ ተናግረዋል። ሆኖም መንግሥት በተደጋጋሚ ወሰድኩ የሚላቸው እርምጃዎች ጥቃቱን ማስቆም ካለመቻላቸውም በላይ ስለተገኘው ውጤት በይፋ የሚገለፅ ነገር የለም።