ሩሲያ የኒውክሌር ሳተላይት ልታመጥቅ ነው መባሉን ተከትሎ ኔቶ ጠፈር ላይ የሚፈጠሩ ስጋቶችን እንደሚከላከል ገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሩሲያ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ የታጠቀ ሳተላይት ለማምጠቅ እየተዘጋጀች መሆኗን የሚገልጹ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጥምረቱ ጠፈር ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ስጋት እንደሚከላከል ተናገሩ።

ሳተላይቱ በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውስጥ ሊመጥቅ እንደሚችል የሚገልጹ የስለላ ሪፖርቶች በዚህ ወር ለኔቶ አባል አገራት መሰጠቱን የጀርመን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ሪፖርቱ የተዘጋጀው በየትኛው አገር እንደሆነ ግን በግልጽ አልታወቀም።

ስለዚህ ጉዳይ ጥያቄ የቀረበላቸው የኔቶ ዋና ፀሐፊ ሩተ፣ "እያንዳንዱን የኔቶ ግዛት እየተከላከልን መሆኑን ሁልጊዜ እናረጋግጣለን፤ ይህ በጠፈር ጉዳይም ደኅንነታችን የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥን ያካትታል" ብለዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔሽኮቭ በበኩላቸው ከሰሞኑ የወጡትን ዘገባዎች እንዳልተመለከቱ ተናግረው፣ "ያልታወቁ ምንጮችን" የሚጠቅሱ ዘገባዎች "በቁም ነገር መታየት የለባቸው" ሲሉ አጣጥለዋል።

በበርሊን የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ለአንድ የጀርመን መገናኛ ብዙኃን በሰጠው አስተያየት፣ ክሶቹን "መሠረት የለሽ ውንጀላዎች" በማለት ውድቅ አድርጓቸዋል። ዘገባዎቹ "የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ" አካል መሆናቸውን በመግለጽም ተቃውሟል።

ሩተ በበርሊን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኔቶ ምላሽ ሊሰጥ የሚችልባቸው የተለያዩ አማራጮች እንዳሉት ተናግረዋል።

"ወደ ወታደራዊው ዘርፍ ሲመጣ፣ ሁልጊዜ የመከላከል እና የመመከት አቅማችንን እንገመግማለን፤ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜም ማሻሻያዎችን እናደርጋለን" ብለዋል።

ሩሲያ የኒውክሌር ሳተላይት ልታመጥቅ ነው የሚለውል ዘገባ ያወጡት ኤንዲአር (NDR) እና ደብሊውዲአር (WDR) እንዲሁም ዙድዶይቸ ሳይቱንግ የተባለው ጋዜጣ ናቸው።

ማንነታቸው ያልተገለጸ የጀርመን ወታደራዊ እና የስለላ ምንጮችን የጠቀሱት እነዚህ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ የሩሲያው ሳተላይት 'ስፑትኒክ-ኤስ' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ሳተላይቱ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደተገጠመለትም ገልጸዋል።

ሳተላይቱ ወሳኝ የኮሚዩኒኬሽን እና የምልከታ ሳተላይቶችን ጨምሮ ሌሎች ሳተላይቶችን ለማስተጓጎል ወይም ለማውደም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

ከኔቶው ዋና ፀሐፊ ጋር በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የጀርመን ቻንስለር ፍሪድሪክ መርትዝ የሩሲያን ዕቅድ በተመለከተ ለወጡት ዘገባዎች ማረጋገጫ ወይም ማስተባበያ አልሰጡም። ነገር ግን ዘገባዎቹ "ሩሲያ ልትከተል የተዘጋጀችውን ውጥረትን የማባባስ ደረጃ በግልጽ ያሳያሉ" ብለዋል።

የአውሮፓ የስፔስ ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት ጆሴፍ አሽባኻ በጠፈር ውስጥ የኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች መኖራቸው "እጅግ የከፋው አስፈሪ ሁኔታ" እንደሆነ መናገራቸውን የጀርመኑ ሃንደልስብላት ጋዜጣ ዘግቧል።

ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 1967 የተዘጋጀውን እና ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎችን በጠፈር ምህዋር ውስጥ ማስቀመጥን የሚከለክለውን የጠፈር ስምምነት ከፈረሙ አገራት መካከል ነች።

አሜሪካን እና ቻይናን ጨምሮ ሌሎች አገራትም ከስምምነቱ ውጭ የሆኑ መንገዶችን በመጠቀም የተቀናቃኝ አገራትን ሳተላይቶች ዒላማ ለማድረግ የሚጠቅሙ የጦር መሣሪያዎችን በጠፈር ላይ አሰማርተዋል ወይም ለማሰማራት አቅደዋል።

በእነዚህ ዓይነት መሣሪያዎች ዒላማ ሊደረጉ የሚችሉት ሳተላይቶች ለወታደራዊ ግንኙነት፣ ለስለላ እና ለአቅጣጫ ጥቆማ ወሳኝ መሣሪያ ናቸው።