ቀጥታ , ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ 'ኮፕ 31' ያለ ስምምነት ተበተነ

የተባበሩት መንግሥታት ኮፕ31 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የተገኙ የዓለም አገራት በነዳጅ እና በፋይናንስ ጉዳዮች ልዩነቶቸቻውን ማጥበብ ስላልቻሉ፣ አየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችል አዲስ ትልቅ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቀሩ። ድርድሩ አርብ ዕለት እንዲጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፣ የጋራ መግባባት ለማግኘት ሲባል እስከ እሁድ ምሽት ድረስ ቀጥሏል። በቱርክ የተካሄደው ጉባኤ ረጅም ጊዜ የወሰደው የተመድ የአየር ንብረት ኮንፈረንስ ሆኗል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ ኢራን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከተኮሰችው የበለጠ ድሮን እና ሚሳዔል ባለፈው ሳምንት አስወንጭፋለች አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ኢራን “ባለፈው ሳምንት በአንድ ዓመት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ካስወነጨፈችው በላይ ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን” ብትተኩስም፣ ምንም ጉዳት አልደረሰም ሲሉ እሁድ ዕለት ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ዴሞክራቶች በሁለቱም የኮንግረስ ምክር ቤቶች አብላጫ ድምፅ ያሸነፉበትን የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በኢራን እየተካሄደ ካለው ጦርነት መባባስ ጋር አያይዘው አንስተውታል።

    ፕሬዝዳንቱ ጥቅምት 24/2019 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫን በተመለከተ “ሁለት ነገሮችን ተንብየው” እንደነበረ ጠቅሰዋል።

    “አንደኛ፣ ዴሞክራቶች ካሸነፉ የአክሲዮን ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ ይወድቃል የሚል ነበር፤ ይህም ተከስቷል። ሁለተኛው ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ 81,000 ተቃዋሚዎችን የገደለችው እስላማዊቷ የኢራን ሪፐብሊክ ጥቃቷን ይበልጥ ታጠናክራለች የሚል ሲሆን ይህም ሆኗል” በማለት ጽፈዋል።

    በጦርነቱ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ፣ በአሜሪካውያን ስለ ኢኮኖሚው አካሄድ እንዲሰጉ አድርጓል።

    ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስን ጨምሮ ከፍተኛ የሪፐብሊካን አመራሮች ፓርቲያቸው በምርጫው የተሸነፈበት አንደኛው ምክንያት ከኢራን ጦርነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ትራምፕ በበኩላቸው እሁድ ዕለት ባሰፈሩት ፅሑፍ፣ መራጮች የድምፃቸውን ትርጉም “አልተረዱም” ያሉ ሲሆን፣ ምርጫውንም “እጅግ ‘ያልተለመደ’” ሲሉ ገልጸውታል።

    “የኢራን መሪዎች ዴሞክራቶችን የሚመለከቷቸው እንደ ደካማ፣ ውጤታማ ያልሆኑ እና አገር አጥፊ ነው፤ ነገር ግን ይህ እንዲሆን አልፈቅድም! ዴሞክራቶችም ሆኑ ኢራን የነዳጅ ዋጋ በተቻለ መጠን ለረጅም ጊዜ ከፍ ብሎ እንዲቆይ እጅጉን ተፋልመዋል፤ ከምርጫው በሏላ ግን የነዳጅ ዋጋ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ቀንሷል” ብለዋል።

    አክለውም “መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊት ይህንን አለመረዳታቸው በጣም ያሳዝናል፤ ነገር ግን አጠቃላይ ምርጫው እጅግ ‘ያልተለመደ’ ነበር” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    • ተያያዥ ዘገባዎች
  2. ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ 'ኮፕ 31' ያለ ስምምነት ተበተነ

    የተባበሩት መንግሥታት ኮፕ31 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የተገኙ የዓለም አገራት በነዳጅ እና በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶቸቻውን ማጥበብ ባለመቻላቸው፣ አየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችል አዲስ ትልቅ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቀሩ።

    በቱርክ የተካሄደው ድርድር አርብ ዕለት እንዲጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፣ የጋራ መግባባት ለማግኘት ሲባል እስከ እሁድ ምሽት ድረስ ቀጥሏል። በዚህ የተነሳም ጉባኤው ረጅም ጊዜ የወሰደው የተመድ የአየር ንብረት ኮንፈረንስ ሆኗል።

    ይሁን እንጂ በድርድሩ መጨረሻ በቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ የቅሪተ አካል ነዳጅ (ፎሲል ፊውል) በቀጥታ አለመጠቀሱ የአውሮፓ ኅብረት፣ የፓስፊክ ደሴት አገራት እና ሌሎችንም አስቆጥቷል።

    እንደ ነዳጅ፣ ከሰል እና የተፈጥሮ ጋዝ ያሉ የኃይል አማራጮች የወል መጠሪያ የሆው 'ፎሲል ፊዩል'፣ የዓለም ሙቀት መጨመር ዋነኛ መንስኤ ነው።

    በርካታ ደሃ አገራት በበኩላቸው፣ እየጨመረ ከመጣው የዓለም ሙቀት ተፅዕኖ ጋር ራሳቸውን ማላመድ የሚያስችላቸውን ገንዘብ ከበለጸጉ አገራት ስለሚያገኙበት መንገድ በግልፅ ቃል ባለመገባቱ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

    በዓመታዊው የኮፕ ጉባኤ ይህ ዓይነቱ የዋነኛ ፖለቲካዊ ስምምነት አለመሳካት ለመጨረሻ ጊዜ የታየው በአውሮፓውያኑ 2009 ኮፐንሃገን ላይ ነበር።

    ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፉበት በዚህ የኮፕ ጉባኤ ላይ የተገኙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ “እጅግ ማዘናቸውን” ገልጸዋል።

    ጉቴሬዝ “ኃያል የፎሲል ፊውል የጥቅም ፍላጎት” አላቸው ያሏቸውን አካላት ተችተዋል።

    “በሁሉም ስፍራ የሚገኙ ሕዝቦች ዋጋ በሚከፍሉበት በዚህ ወቅት፣ የግዙፍ የትንባሆ ኩባንያዎችን ስልት በመኮረጅ ሳይንሱን በማዛባት፣ ፖሊሲዎችን በማዘግየት፣ እርምጃዎችን በማገድ ትልቅ ትርፍ እያካበቱ ነው” ብለዋል።

    ከቱርክ ጋር በመሆን ጉባኤውን ያዘጋጀችው አውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ በበኩቸላው፣ ኮንፈረንሱ ያለ ስምምነት ለመበተኑ ተጠያቂ ያደረጉት “አስቸጋሪ ጂኦፖለቲካዊ ጊዜ” መኖሩን ነው።

    ላይ ታች ሲሉ የከረሙት የተሳታፊ አገራት ልዑካን ከሁለት ሳምንታት ድርድር በኋላ፣ አለመግባባቱን ለመፍታት ያስችላል የተባለ አዲስ ረቂቅ ስምምነት እሁድ ጠዋት ቀርቦላቸው ነበር።

    ነገር ግን በዚህ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ውስጥ ‘ፎሲል ፊውል’ የሚለው ቃል አንድም ቦታ አልተጠቀሰም።

    የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝን በተመለከተ የተጠቀሰው ብቸኛው ቀጥተኛ ያልሆነ አገላለጽ፣ በአውሮፓውያኑ 2023 በተካሄደው ኮፕ28 ስብሰባ ወቅት አገራት ከፎሲል ፊውል ተጠቃሚነት “ለመሸጋገር” ስምምነት መፈጸማቸውን የሚያስታውስ አንቀጽ ነው።

    የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ የሆኑት አየርላንዳዊው ሚኒስትር ዳራግ ኦብራየን፣ ኅብረቱ ይህንን አካሄድ “በጽኑ” እንደሚቃወም አሳውቀዋል።

    “የተላለፉት ውሳኔዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከሚያስፈልገው የቁርጠኝነት ደረጃ ጭራሽ የሚቀራረቡ አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ባለፈው ሰኞ ዕለት በቀረበው የመጀመሪያው ረቂቅ ላይ ‘ፎሲል ፊውል’ ወይም ‘ፎሲል ፊውልስ’ የሚለውን ቃል ስድስት ጊዜ ተጠቅሶ የነበረ ሲሆን፣ ነዳጅ አምራች አገራት ግን ተቃውመውታል።

    የሳዑዲ አረቢያ ልዑክ መሐመድ አዩብ የአረብ አገራት “በቅን ልቦና መሳተፋቸውን እንደቀጠሉ” አንስተው፣ ነገር ግን አረብ አገራቱ በታሪክ ውስጥ የነበራቸው የበካይ ጋዝ ልቀት ድርሻ አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል።

    ሩሲያ በበኩሏ ሀገራት እንደ የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ካሉ የኃይል አማራጮች ተጠቃሚነት በፍጥነት የሚወጡ “የነዳጅ ድኅነት” ይከሰታል ስትል ሞግታለች።

    • ተያያዥ ዘገባዎች
  3. የኅዳር 14 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባ ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የሰኞ ኅዳር 14 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።