ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን 'ከኢትዮጵያ የተነሳ ነው' ባለችው ድሮን ኻርቱም የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ሕንፃ ተመታ
በሱዳን ዋና ከተማ ኻርቱም እሑድ በደረሰ የድሮን ጥቃት መኖሪያ ቤቶች እና የተባበሩት መንግሥታት ሕንፃ መመታቱን የዐይን እማኞች እና ድርጅቱ ገለፁ።
ከለሊት 8 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት 10፡30 የዘለቀው የድሮን ጥቃት በኻርቱም አየር ማረፊያ እና በሌሎች የከተማዋ ክፍሎች ተሰምቷል።
አንድ የዐይን እማኝ በድሮን ጥቃቱ ምክንያት መኖሪያ ቤት መወደሙን ሲናገሩ፣ የሱዳን ጦር ደግሞ ድሮኖቹ የተነሱት ከኢትዮጵያ ነው ብሏል።
"ንጋት ላይ የደረሰው ጥቃት ኢትዮጵያ የሱዳንን ድንበር እየጣሰች መሆኗን ማሳያ ነው። ምክንያቱም ድሮኖቹ የተነሱት ከኢትዮጵያ የባሕር ዳር አየር ማረፊያ ነው" ሲሉ አንድ ምንጭ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የሱዳን ጦር ኢትዮጵያ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድጋፍ እያደረገች ነው ሲል በተደጋጋሚ ይወቅሳል። የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2023 ጀምሮ ውጊያ ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ሱዳን የምታቀርብባትን ክስ ውድቅ የምታደርግ ሲሆን፣ ለአሁኑ የድሮን ጥቃት ክስም የኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠው ምላሽ የለም።
የኤኤፍፒ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እንደሚያሳዩት በርካታ ቤቶች ፈራረሰዋል። የቤት ውስጥ ዕቃዎች እና አልባሳትም ወዳድቀው ይታያሉ።
ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ የሚኖረው አል-ኑር አደም ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ወደ ቤት ሲገባ "አንድ ሰው ግራ እጁ፣ ደረቱ እና ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ደርሶበት አልጋ ላይ ወደቆ ነበር" ሲል ለዜና ወኪሉ ተናግሯል።
"ጥቃቱ ወታደራዊ ዒላማ ያማከለ አይደለም" ይላል አደም።
"እንቅልፍ ላይ ሳለህ ጥቃት ሊደርስብህ ይችላል። ስትነሳ ልጆችህን ልታጣቸው ትችላለህ. . . በጣም ያሳዝናል። ምንም ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።"
ሌላኛው የአካካቢው ነዋሪ ያስር ሐሰን "ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት መጠለያ አጥተው ሲንከራተቱ የቆዩ ሰዎች ናቸው" ሲል ተናግሯል። "አሁን የድሮን ጥቃት ደረሰባቸው። የት መሄድ እንችላለን?"
ሌላ የዐይን እማኝ ጀበል አውሊያ ተብሎ በሚታወቀው ከኻርቱም በስተደቡብ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ መንደር የድሮን ጥቃት የአንድ መስጂድ አዛን የሚሉ ግለሰብ ቤት ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
"ሰዎች ከፍርስራሽ ውስጥ በሕይወት የተረፉትን ለማውጣት ሲረባረቡ ነበር" ሲሉ እማኙ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ "የድርጅቱ ንብረት የሆነ ቅጥር ግቢ ሠራተኞች ባሉበት ተመትቶ ጉዳት ደርሶበታል" ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) በኤክስ ገፁ በለቀቀው መግለጫ "ጥቃቱ የደረሰው ሰላማዊ ሰዎች በሚኖሩበት መንደር ነው" ብሏል።
ኦቻ፤ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያደርሱ ሰዎች ላይ ስጋት መደቀኑን አውግዞ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ለመሰል አደጋ መጋለጣቸው "ተቀባይነት የለውም" ብሏል።
ለሱዳን መደበኛ ጦር ድጋፍ የምታደርገው ሳዑዲ አረቢያ በኤክስ ገፅ "መሰል ጭካኔ የተሞላባቸውን ጥቃቶች" እንደምታወግዝ አስታውቃለች።
የሱዳንን ጦርን የምትደግፈው ግብፅም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል በሰጠችው መግለጫ ጥቃቱን "በፅኑ እንደምታወግዝ" ገልፃለች።
የሱዳን ባለሥልጣናትም ሆኑ የተባበሩት መንግሥታት በጥቃቱ የሞቱ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር ይፋ አላደረጉም።
በሱዳን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና በጦር ሠራዊቱ መካከል በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት እስካሁን 200 ሺህ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ሱዳን የዓለማችን ከፍተኛው ረሀብ እና መፈናቀል ያለባት አገር እንድትሆንም አድርጓታል።
የተባበሩት መንግሥታት ሁለቱም ወገኖች ድሮኖ መጠቀማቸውን አውግዞ በአውሮፓውያኑ 2026 የመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ ከ1 ሺህ 100 በላይ ሰዎች በድሮን መገለዳቸውን ጠቁሟል።
በዚህ ዓመት በጦርነቱ ከተገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ሁለት ሦስተኛው የድሮን ሰለባ ናቸውም ብሏል።
የሱዳን ጦር ባለፈው ሳምንት በዌስት ኮርዶፋን ግዛት ባደረሰው የድሮን ጥቃት 15 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ወገኖች በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት በማዕድን የበለፀገችውን ኮርዶፋን ግዛት በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ከፍተኛ ውጊያ እያደረጉ ነው።