ሩሲያ እና ዩክሬን የሦስት ቀን ተኩስ አቁም ሊያደርጉ ነው

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሶቪየት ኅብረት ናዚ ጀርመንን ድል ያደረገችበትን በዓል ለማክበር በተናጠል ያወጁት ተኩስ አቁም በሌላኛው ወገን እንደተጣሰ በመግለጽ ሲካሰሱ የቆዩት ሩሲያ እና ዩክሬን፤ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ተኩስ አቁም እንደሚያደርጉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ "ይህ ተኩስ አቁም የትኛውንም ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማቆምን እንዲሁም ከእያንዳንዱ አገር 1,000 እስረኞችን መለዋወጥን ያካትታል" ብለዋል።

ከቆይታ በኋላ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜለንስኪ ዩክሬን በተኩስ አቁሙ ተሳታፊ እንደሆነች ያረጋገጡ ሲሆን፤ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃንም ሞስኮ በዕቅዱ መስማማቷን ገልጸዋል።

ሁለቱም አገራት አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ቀጥለዋል። የሞስኮ ከንቲባ ከተማዋ ሌሊቱን በድሮኖች ዒላማ ስትደረግ ማምሸቷን ተናግረዋል።

ትራምፕ የሦስት ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ራሳቸው መጠየቃቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፉት ጽሑፍ ገልጸዋል። "ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ፕሬዝዳንት ቭሎዲሚር ዜለንስኪ ለጥያቄዬ በመስማማታቸው እጅግ አመሰግናለሁ" ብለዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ዛሬ ከሚከበረው የድል ቀን አስቀድመው ለአርብ እና ቅዳሜ የሚቆይ የተኩስ አቁም አውጀው ነበር። ኪየቭ በበኩሏ ከረቡዕ ሚያዝያ 28/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ አስቀድማ ጠይቃ ነበር።

ሩሲያ፤ ዩክሬን የድል በዓል በሚከበርበት 'ቀይ አደባባይ' ላይ ጥቃት ለመፈጸም እንዳትሞክር አስጠንቅቃለች። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ መሃል "ከፍተኛ አጸፋዊ የሚሳዔል ጥቃት" እንደሚያደርስ ዝቷል።

የውጭ አገር ዲፕሎማቶች እስከ ግንቦት 1 ድረስ የዩክሬንን ዋና ከተማ ለቅቀው እንዲወጡም አስጠንቅቋል። ሩሲያ ከሁለት አሥርተ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የድል ክብረ በዓል ሰልፍ ላይ ወታደራዊ አቅሞቿን አታሳይም።

ዩክሬን በዓሉን ለማስተጓጎል ትሞክራለች የሚል ስጋት በመኖሩ ሞስኮ ውስጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው። የሞስኮ እና የሴንት ፒተርስበርግ ነዋሪዎችም ለደኅንነት ሲባል የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎታቸው እንደሚገደብ ተነግሯቸዋል።

ከዚህ ቀደም በዓሉ ሲከበር በርካታ የውጭ አገር እንግዶች ወደ ሞስኮ ይጓዙ ነበር። በዚህኛው በዓል ላይ የሚገኙት የቤላሩስ፣ ማሌዥያ እና ላኦስ መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ስመ ጥር ሰዎች ብቻ ይታደማሉ።