ዶናልድ ትራምፕ በባሕረ ሰላጤው አገራት ጥያቄ መሠረት ኢራን ላይ የሚፈጸምን አዲስ ጥቃት ማስቀረታቸውን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በኢራን ላይ ለመፈጸም አቅደውት የነበረውን ጥቃት በባሕረ ሰላጤው አገራት ጥያቄ መሠረት መሰረዛቸውን አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም "አሁን ኮስተር ያለ ድርድር እየተካሄደ ነው" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ልጥፍ ጥቃቱ እንዲቀር የጠየቁት አገራት ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ አሜሪካ "በጣም የምትቀበለው" ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል እንደተነገራቸው ገልጸው "ኢራን የጦር መሣሪያ አይኖራትም" ሲሉ አክለዋል።

ነገር ግን ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ አሜሪካ "በተነገራት ቅጽበት ሙሉ ጥቃት ኢራን ላይ ለመፈጸም በተጠንቀቅ ናት" ብለዋል።

ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ አዛዥ በበኩላቸው አሜሪካ "ዳግመኛ ስትራቴጂክ እና የስሌት ስህተት" እንዳትሰራ ሲሉ ተናግረዋል።

እስራኤል እና አሜሪካ በጋራ በመሆን ቴህራን ላይ ጥቃት የጀመሩት የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ነበር። ኢራን በምላሹ በባሕረ ሰላጤው አገራት በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሠፈሮች ላይ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን ፈጽማለች።

አሁንም የባሕረ ሰላጤው አገራት ፍራቻ አሜሪካ ዳግም ቴህራን ላይ ድብደባ የምትፈጽም ከሆነ የአጸፋ ምላሽ የምትሰጠው የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት በመፈጸም በመሆኑ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ያላቸው ቅቡልነት እየወረደ መምጣቱን ያሳያሉ።

64 በመቶ የሚሆኑ መራጮች ኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸው ስህተት ነበር ያሉ ሲሆን፣ 37 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ እንደ ፕሬዚዳንት ትክከለኛውን ሥራ መስራታቸውን ይናገራሉ።

ኢራን ጦርነቱ ዳግም የሚጀመር ከሆነ ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የፔትሮኬሚካል ተቋማት እና የውሃ ማከፋፈያዎች የምታስወነጭፋቸው ድሮኖች እና ሚሳዔሎች አሁንም እንዳሏት ይታመናል።

ቀደም ሲል ትራምፕ ለጋዜጠኞች በሁለቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ስላላው ድርድር ሲናገሩ "በጣም በጎ እርምጃዎች አሉ፤ ነገር ግን ምን ማለት እንደሆነ እና እንዳልሆነ የምናየው ይሆናል" ብለው ነበር።

አክለውም "ስምምነት ላይ እንደደረስን፣ እንደተቃረብን የተሰማን ወቅት ነበር፤ ነገር ግን እንደገመትነው አልሆነም። ይህ ግን የተለየ ነው" ብለዋል።

ትራምፕ ከኢራን ጋር ከስምምነት ላይ ለመድረስ ጥሩ ዕድል" ያለ ይመስላል በማለት "በቦምብ ሳንደበድባቸው ያንን ማድረግ ከቻልን በጣም ነው ደስተኛ የምሆነው" ብለዋል።

በሚያዚያ ወር በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም የተደረሰ ሲሆን አልፎ አልፎ ከሚደረግ የተኩስ ልውውጥ በስተቀር በአብዛኛው ጸንቶ ቆይቷል።

ኢራን የዓለም 20 በመቶ የሚሆነው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ የዘጋች ሲሆን ይህም የዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል።

አሜሪካ በበኩሏ ቴህራን ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና በመፍጠር ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንድትመጣ ለማድረግ በሚል ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡም ሆነ የሚወጡ መርከቦችን ከልክላለች።

ሰኞ ዕለት የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ ጠላት ጥቂት ልምድ ባለው ግንባር አዲስ ግንባር ሊከፈት እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውን እና ይህም በጣም ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ማስጠንቀቃቸውን ዘግቦ ነበር።

በኋላ ላይ ታስኒም ጠቅላይ መሪው መጋቢት 3 2018 ዓ.ም. ያስተላለፉትን መልዕከት ዳግም ማጋራቱ ታውቋል።

የኢራን መገናኛ ብዙኃን አሜሪካ የተጨበጠ ስምምነት ከቴህራን ላይ ለድረስ አለመቻሏን ዘግበዋል።

እሁድ ዕለት ትራምፕ "ለኢራን ሰዓቱ እያበቃ ነው፤ በፍጥነት መንቀሳቀስ አለባቸው ወይም ምንም የሚተርፋቸው ነገር አይኖርም" ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።

ከበርካታ ቀናት በፊት እንዲሁ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ለመፍረስ "በቋፍ ላይ ነው" በማለት ቴህራን ያቀረበችውን ጥያቄዎች "ፍጹም ተቀባይነት የሌለው" ሲሉ ውድቅ አድርገው ነበር።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ኢስማኤል ባጌይ በበኩላቸው አገራቸው ያቀረበቻቸው መደራደሪያዎች "ኃላፊነት የሚሰማቸው" እና "ፍትሃዊ" መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ታስኒም ዘገባ ከሆነ ኢራን ያቀረበችው መደራደሪያ ነጥቦች በሁሉም ግንባሮች ጦርነቱ ወዲያውኑ እንዲቆም፣ ይህም እስራኤል በሄዝቦላህ ላይ የከፈተችውን ጥቃት ያካትታል፣ የአሜሪካ ባሕር ኃይል በኢራን ወደቦች ላይ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ፣ ኢራን ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንደማይፈጸም ዋስትና እንዲሰጥ የሚሉ ናቸው።

በተጨማሪም በጦርነቱ ለደረሱባት ጉዳቶች ካሳ እንዲሁም በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የኢራንን ሊዓላዊነት እንዲረጋገጥ የሚሉ ነጥቦች እንደተካተቱበት ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢራን አንድ የኒውክሌር ተቋም ብቻ እንዲኖራት እና ያበለጸገችውን ዩራኒየም ለአሜሪካ እንድታስረክብ የሚል አንቀጾች እንደተካተቱበት ተዘግቧል።

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ኢራን ለ20 ዓመት ያህል የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለማቆም የምትስማማ ከሆነ ሊቀበሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ይህም መጀመርያ ላይ ይዘውት ከነበረው እና ሁለቱን አገራት ካላስማማው ሙሉ በሙሉ የኒውክሌር ፕሮግራሟን እንድታቆም ከሚጠይቀው አቋም የተለየ ነው።

አሜሪካ እና የአውሮፓ አጋሮቿ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መታጠቅ ትፈልጋለች ሲሉ ይከስሷታል። ቴህራን ግን በተደጋጋሚ ፕሮግራሙ ለሰላማዊ ዓላማ ፤ ለኃይል ማመንጫ ብቻ የሚውል ነው ስትል ታስተባብላለች።