የሕንድ ትምህርት ሚኒስትር ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ለሳምንታት የተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ቆሙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሕንድ ትምህርት ሚኒስትር ዳርሜንድራ ፕራዳን ከሥልጣን ከለቀቁ ከሰዓታት በኋላ ለአምስት ሳምንታት የዘለቀው የተቃውሞ ሠልፍ ተቋረጠ።
የሕንድ ኮክሮች ጃንታ ፓርቲ (ሲጄፒ) የሚኒስትሩን ከሥልጣን መልቀቅ ለዲሞክራሲ ድል ነው ሲል ጠርቶታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሠልፈኞች ደስታቸውን በዴልሂ ዋና የተቃውሞ ሥፍራ በሆነው በጃንታር ማንታር መግለጻቸውን ቀጥለዋል።
በኤአይ የተሰራ የበረሮ ምሥልን እንደመለያ የሚጠቀመው እና በኦንላየን ስላቆችን በማቅረብ የተጀመረው ይህ ዘመቻ በእውነተኛ የፖለቲካ ፓርቲ ባይመራም ቡድኑ ግን ራሱን ሲጄፒ በማለት ይጠራል።
የፓርቲው እንቅስቃሴ ወጣቶች ተስፋ መቁረጣቸውን እና ቅሬታቸውን የሚገልጹበት መድረክ በመሆን አገልግሏል።
እንቅስቃሴው የተጀመረው የሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሱሪያ ካንት በጋዜጠኝነት እና በአክቲቪዝም ውስጥ የሚሳተፉ ሥራ አጥ ወጣቶችን "በረሮ" እና "ፓራሳይት" ሲሉ አወዛጋቢ አስተያየት ከሰጡ በኋላ ነበር።
ይህንን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መንግሥት ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጣ የታየበት ነው ተብሏል።
ሰኞ ዕለት ወደ ፓርላማ ለመሄድ የሞከሩ የተቃውሞ ሠልፈኞች ላይ ፖሊስ እርምጃ በመውሰዱ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዳርሜንድራ ፕራድሃን በኤክስ ገጻቸው ላይ በሂንዲ ቋንቋ ባሰፈሩት መልዕክት "የወጣቶችን ምኞት፣ ህልሞች እና ግምቶች እንደሚያከብሩ" እና ባለፉት ጥቂት ቀናት በተከሰቱት "ሁኔታዎች መረበሻቸውን" በመግለጽ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
"በጃንታር ማንታር እና በመላ አገሪቱ ያለውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ፀረ ብሔራዊ ኃይሎች እንዳይጠቀሙበት ለመከላከል፣ ብሔራዊ አንድነትን ለመጠበቅ፣ የአንድም የሕንድ ተማሪ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በሕግ ውስብስብ ጉዳዮች ውስጥ አለመግባቱን ለማረጋገጥ፣ እና ልጆቻችን ጊዜያቸውን በትምህርት እንዲያሳልፉ እና የሥራ ሕይወታቸውን በመገንባት ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ የሥራ መልቀቂያዬን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገብቻለሁ" ሲሉ ጽፈዋል።
የፕራድሃን ከሥልጣን መልቀቅ ዜና ሲሰማ የሲጄፒ መሥራች አቢጂት ዲፕኬ በጃንታር ማንታር በሚገኘው የተቃውሞ ሥፍራ "አድርገነዋል" በማለት ሲጮህ ታይቷል።
ሚኒስትሩ ከሥልጣን መልቀቃቸው ከተሰማ በኋላ በተቃዋሚ ሰልፈኞች መካከል ከፍተኛ ደስታ ተፈጥሮ ሲዘፈኑ፣ ሲጨፍሩ፣ መፈክር ሲያሰሙ እና ጣፋጮችን እየተጋሩ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
ሲጄፒ የተቃውሞ ሰልፉ ማብቃቱን ካሳወቀ እና መሪዎቹ ቦታውን ለቀው ከሄዱ በኋላ ሠልፈኞች እስከ ሌሊት ድረስ በቦታው በመሆን ደስታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ብዙዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህንን ቀን ለሳምንታት እንደጠበቁት እና ደስታቸውን ሳይገልጹ ለመሄድ ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ለሳምንታት የተቃውሞ ድምጽ የታየበት ሥፍራ የፌሽታ ማዕከል የሆነ ሲሆን በጎ ፈቃደኞች ሕዝቡን ለማስተናገድ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።
በአካባቢው በርካታ ፖሊሶች ተሰማርተው የነበረ ቢሆንም የሕግ ጥሰት ካላዩ ጣልቃ እንደማይገቡ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሲጄፒ የተመሰረተው የሕንድ ዋና ዳኛ የተቃውሞ ስብስቡን ፊታቸውን ወደ ጋዜጠኝነትና አክቲቪዝም ያዙሩ ጥቂት ሥራ አጥ ወጣቶች "በረሮዎች" ብለው ከጠሯቸው በኋላ ነው። በኋላ ላይ ዳኛው በተለይ "ሐሰተኛ ዲግሪ" ያላቸውን ሰዎች ለማመልከት መሆኑን በማስረዳት አስተባብለዋል። ነገር ግን ከእርሳቸው ዘለፋ በኋላ ቡድኑ "ኮክሮች" የሚለውን በመጠሪያነት መጠቀም ቀጥሏል።
ንቅናቄው የሚመራው በ30 ዓመቱ የፖለቲካ ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂስት እና የቦስተን ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪ በሆነው በአቢጂት ዲፕኬ ነው።
ሲጄፒ በፍጥነት በኢንስታግራም ላይ 26 ሚሊዮን ተከታዮችን በማፍረት የተቃውሞ ምልክት ሆነ።
በሕንድ የትምህርት ስርዓት ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ፣ የፈተና ወረቀቶችን አሹልኮ በማውጣት ረገድ የበለጠ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና የፕራዳን ከሥልጣን መልቀቅን ጠይቋል።
አክቲቪስት እና የትምህርት ባለሙያ የሆነው ሶናም ዋንግቹክ እአአ ሰኔ 28 ላይ ተቃወዋሞ ሠልፈኞቹን ከተቀላቀለ በኋላ እና ጥያቄዎቻቸውን ለመደገፍ ላልተወሰነ ጊዜ የረሃብ አድማ ከጀመረ በኋላ ሠልፉ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቧል።
ሕንዳዊው አክቲቪስት ሶናም ዋንግቹክ የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ እንዲደረግ የጠየቁ ወጣቶችን ተቃውሞ በመደገፍ የጀመረውን የረሃብ አድማ ከ26 ቀናት በኋላ አቁሟል።
"ሶናም ሰር" በመባል የሚታወቀው ዋንግቹክ፣ "በተለያዩ ጉዳዮች ረዥም ሰዓት የፈጀ ድርድር ከተደረገ በኋላ" እንዲሁም "በአገሪቱ ሊኖር የሚችል ግጭትን" ለመቀልበስ በሚል የረሃብ አድማውን ማቆሙን በኤክስ ገጹ አስታውቋል።
ከአንድ ወር በላይ በዘለቀ በወጣቶች የሚመራ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከትምህርት ሚኒስትርነት እንዲወርዱ ሲጠየቁ የነበሩት ዳርሜንድራ ፕራድሃን፤ ከሥልጣን መልቀቃቸውን ያስታወቁት ቅዳሜ ዕለት ነበር።















