"እናቴ ለዓመታት በሐሰት 'በሽተኛ ነሽ' ብላ አሰቃየችኝ"

የፎቶው ባለመብት, Nina Blom
ኒና ብሉም በኔዘርላንድስ በ1970ዎቹ እና በ1980ዎቹ እንዳደጉ አብዛኞቹ ልጆች ናት።
መዝፈን እና መደነስ ትወዳለች። ከእህቷ ጋር መጫወት የልጅነቷ አስደሳች ትውስታ ነው።
እነዚህ የደስታ ቅጽበቶች ግን ውስን ናቸው።
ከቤት መውጣት የሚፈቀድላት አልፎ አልፎ ብቻ ነበር። ከስምንት ዓመቷ ጀምሮ ከፍተኛ ሕመም እንዳለባት እናቷ አሳምናታለች።
በተደጋጋሚ ሆስፒታል እየወሰደች ታስመረምራት ነበር። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ ስድስት ሆስፒታሎች 15 ጊዜ ተምርምራለች።
እናቷ በዊልቼር እንድትሄድ አድርጋታለች።
የኒና እናት የማይድን የጡንቻ ሕመም እንዳለባት እና እንደምትሞት ነግራታለች።
ለዓመታት ብዙ የሕክምና ባለሙያዎች ምርመራ ቢያደርጉላትም ችግሯ ምን እንደሆነ አልታወቀም።
አንድ ሐኪም ግን የኒናን ታሪክ ሰምተው "ሕመሟ" እናቷ መሆኗን ደረሱበት።

የፎቶው ባለመብት, Nina Blom
የመጀመሪያው የሆስፒታል ቆይታ
ወላጆች በሐሰት ልጆቻቸው ላይ ሕመም ሲፈጥሩ ወይም ሲያጋንኑ 'Paediatric Condition Falsification' ወይም 'Fabricated or Induced Illness' ይባላል። ሁኔታው 'Munchausen Syndrome' በሚል ስያሜም ይታወቃል።
ኒና ስምንት ዓመቷ ሳለ ሆዷን አሟት በከፍተኛ መጠን የሰውነት ክብደቷ ቀነሰ።
ሆስፒታል ሾርባ እና የብርቱካን ጭማቂ ሲሰጣት ተሻላት።
"ኒና ተሽሏታል፤ ወደ ቤት መሄድ ትችላለች" ብለው ሐኪሞች ለእናቷ ነገሩ።
እናቷ ግን ሆስፒታል መቆየት አለብን አለች። ኒና ቢሻላትም ሆዷን እያመማት እንደሆነ ለሐኪሞች እንድትናገር እናቷ አስገደደቻት።
በቀጣይ ዓመታትም እናቷ ተመሳሳይ ጫና ማሳደሯን ቀጠለች።
ቤተሰቡ ሽርሽር ላይ ሳለ ኒና ዋና ከዋኘች በኋላ ሰውነቷ እንዳበጠ ተናገረች። እናቷ ወዲያውኑ የጡንቻ መሸማቀቅ እንዳለባት ገልጻ ሆስፒታል ወሰደቻት።
ነገሩ ኒናን ግራ አጋባት።
"ካንሰር ከያዛቸው ልጆች ጋር ሆስፒታል መግባቴ የጥፋተኛነት ስሜት ፈጠረብኝ። እነሱ በጣም ታመዋል። እኔ ምንም ችግር እንደሌለብኝ አውቃለሁ።"

የፎቶው ባለመብት, Nina Blom
'ጨካኝ ናት'
ሆስፒታል ሳለች አጠገቧ የሚገኝ አልጋ ይዞ የነበረ ልጅ ሞተ። ይህም የጥፋተኛነት ስሜትን አባባሰባት።
ኒና ብዙ ምርመራ ተደረገላት። ከምርመራዎቹ መካከል በጣም የሚያመው ከአጥንት ውስጥ ናሙና የሚወሰድበት (bone marrow biopsy) ይገኝበታል።
ሐኪሞቹ ምንም ሕመም አላገኙባትም።
እናቷ ግን ማቆም አልቻለችም። ኒና ስትስቅ ካየች ተበሳጭታ ትቀጣታለች።
አራት ሳምንት ሆስፒታል ተኝታ ሐኪሞች ወደ ቤት እንድትሄድ ወሰኑ። ቤት ስትገባ እናቷ በዊልቼር እንድትንቀሳቀስ አደረገች።
ከትምህርት ቤት ወጥታ ቤት እንድትተኛ ተደረገች። ከጓደኞቿ ጋር መገናኘት አቆመች።
በጣም የምትወደውን ሙዚቃም እናቷ ቀማቻት። ራሷን ለማጽናናት ሹራብ ሥራ ጀመረች።
ሥራው እጇን ያደክመው ነበር። ከዚያም እናቷ እጇን እንዳመማት ነግራት ክንዷን ጠቅልላ አሸገችው።
በጣም አጥብቃ ስላሸገችው ጣቶቿ ደነዘዙ። እናቷ በዚህ የተደሰተች ይመስላል።
"እናቴ ይሄንን እያየች ደስታ እያገኘት መሆኑን ማሰብ በጣም አስቀያሚ ነበር።"

የፎቶው ባለመብት, Nina Blom
'ትሞቻለሽ'
በዓመታት ሒደት እናቷ ታሪኩን ለወጠች።
"እንዳላመመሽ ካወቅኩ እና ይሄንን ሁሉ ፈጥረሽው ከሆነ፤ እኔው ራሴው እጎዳሻለሁ" አለቻት።
ኒና በነገሩ የበለጠ ግራ ተጋባች። የእናቷን ጤና ተጠራጠረች።
አብዛኛውን ጊዜ የምታሳልፈው አልጋ ላይ ስለሆነ እና ክንዷም ስለታሸገ ትዳከም ጀመር።
ሰውነቷ እንዲፍታታ የማገገሚያ ሕክምና (physiotherapy) እንድታደርግ ሐኪሞች አዘዙ።
በሕይወቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ደስተኛ የሆነችበት ወቅት ነበር።
ቅዳሜ እና እሑድ ከሆስፒታል ወጥታ ቤት እንድታሳልፍ ተደረገ።
እናቷ ወዲያውኑ ሕይወቷን መቆጣጠር ቀጠለች። እጇ በድጋሚ እንዲታሸግ አስገደደቻት። ከአልጋ እንዳትወርድም አዘዘቻት።
"የልብ ታማሚ ነሽ አለችኝ። አንድ ቀን ደግሞ 'ትሞቻለሽ' አለችኝ። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቸኝነት ተሰማኝ። ወደ አዘቅት የተወረወርኩ መሰለኝ።"

የፎቶው ባለመብት, Nina Blom
'ሐኪሞች እንድሞት እርዱኝ'
ከዚህ በኋላ ነገሮች ተለወጡ። ኒና አዲስ ሐኪም አገኘች። ዶ/ር ቪሪናትን ይባላሉ።
እጅ እና እግሯን እንዲሁም ጡንቻዋን በተሻለ ሁኔታ ለማንቀሳቀስ የሚደረዳ ሕክምና ከተሰጣት መራመድ እንደምትችል ነገሯት።
ኒና ይሄንን ስትሰማ ማመን አልቻለችም።
እናቷ የነገረቻት ጽኑ የጡንቻ ሕመም እንዳለባት እና በበሽታዋ ምክንያት እንደምትሞት ነው።
እናቷ ይሄንን ስትላት ብትጠራጠርም ጥያቄ የማንሳት ድፍረቱን አላገኘችም።

የፎቶው ባለመብት, Nina Blom
እናቷ የሐኪሙን ምክር ስትሰማ በጣም ተቆጣች። ኒና ቤት ስትመለስ እግሮቿን አጣምራ ከትራስ ጋር አሰረች።
ምግብ እንድታቆም አደረገቻት። በአፍንጫዋ በሚሰካ ትቦ ምግብ እንድትወስድ አስገደደቻት። በቀን 20 የመድኃኒት እንክብሎችም ትወስድ ነበር።
ኒና ወደ ሐኪም ቤት ስትመለስ በሕክምና እርዳታ መሞት ትችል እንደሆነ እናቷ ጠየቀች።
በጣም የደከመችው እና የታመመችው ኒና ለመሞት ከእናቷ ጋር ተስማማች።
"ሐኪሙን 'መሞት እፈልጋለሁ፤ ልትረዳኝ ትችላለህ?' አልኩት።"
ሐኪሙ ደንግጦ ከእናቷ ጋር መነጋገር ጀመረ። ለ24 ሰዓታት የሕመም ማስታገሻ እንድትወስድም አደረገ።
ተኝታ እንድትቆይም ወሰነ።
ኒና ወደ ሌላ ሆስፒታል እንደምትወሰድ ሲነገራት "እባካችሁ እንድሞት ተዉኝ" ብላ መለመን ጀመረች።
እናቷ በዚህ ወቅት ደነገጠች። ሁለት ፖሊሶች በቦታው ነበሩ። ወዲያውኑ በአምቡላንስ ተወሰደች።
እጇ እና እግሯ ላይ የነበረው እሽግ ተፈታላት። በክፍሏ ውስጥ ቪድዮ ካሜራ ተሰቀለ።
ለሁለት ቀናት ከእናቷ እና ከአባቷም ጋር አልተገናኘችም።
ቤተሰቦቿን ስታገኝ 18 ጊዜ ደጋግማ "አልታመምኩም" አለቻቸው።
ካሜራ በክፍሏ መሰቀሉን የረሳችው እናቷ ቁጣዋን ማሳየት ጀመረች። ለዓመታት ይሄንን ማድረጓን የሚያሳይ መረጃ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Nina Blom
ሕይወትን እንደ አዲስ የመገንባት ጉዞ
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኒና ከቤተሰቦቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማቋረጥ ወሰነች።
በሕክምና ማዕከል አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ ወሰደች። ከዚያም አዲስ ማንነት ገንብታ ሕይወቷን መምራት ጀመረች።
ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ከተመረቀች በኋላ ከፍቅረኛዋ ጋር ተገናኝታለች።
ቤተሰቦቿ ለኑሮዋ ዕውቅና አልሰጡም። መርማሪ ቀጥረው ያለችበትን ቦታ ለማወቅ ሞክረዋል። ይህም ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከትቷት ነበር።
ቤተሰቦቿ ላይ ጥቆማ ለመስጠት አስባ የነበረ ቢሆንም ሐሳቧን ለውጣለች። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እናቷ እና አባቷ በተከታታይ ሞቱ።
"ወላጆቼ የፈጸሙብኝ ድርጊት ወንጀል ነው። የልጅ ብዝበዛ ነው። በተአምር ነው የተረፍኩት። በመትረፌ ደስተኛ ነኝ። ብዙ የምኖርለት ምክንያት አለኝ።"















