ሦስት ድፍድፍ ነዳጅ የጫኑ ግዙፍ መርከቦች መከታተያቸውን በማጥፋት የሆርሙዝ ወሽመጥን ማቋረጣቸውን ሮይተርስ ዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ሳምንት ሦስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ራሳቸውን ከኢራን ጥቃት ለመከላከል የመከታተያ መሣሪያቸውን በማጥፋት ወሽመጡን ማቋረጣቸውን ሮይተርስ ዘገበ።
ሮይተርስ የመርከቦች እንቅስቃሴን ከሚከታተሉት ኬፕለር እና ኤልኤስኢጂ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ እንደዘገበው ሁለት ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ሆርሙዝን ያቋረጡት ትናንት እሁድ ነው።
አንዱ መርከብ ግን ከአምስት ቀን በፊት ማቋረጡን የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚከታተሉትን ድርጅቶች ጠቅሶ ዘግቧል።
አጊዮስ ፋኖውሪየስ I እና ኪያራ ኤም የተሰኙት መርከቦች እያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊየን በርሜል ነዳጅ መጫናቸው ተግለጿል።
አጊዮስ ፋኖውሪየስ I ወደ ቬይትናም የሚያመራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ቀደም ሁለቴ ወሽመጡን ለማቋረጥ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
አጊዮስ ፋኖውሪየስ I የሚያስተዳድረው ኢስተርን ሜዲትራኒያን ማሪታይም ስለመርከቡ ጉዞ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
እሁድ ዕለት ወሽመጡን ያቋረጠው ሌላው ነዳጅ ጫኝ መርክ ኪያራ ኤም የጫነውን ነዳጅ ወዴት እንደሚያጓጉዝ አልታወቀም። መርከቡን የሚያስተዳድረው መቀመጫውን ሻንጋይ ያደረገው ኩባንያ ሲሆን ስለ መርከቡም ሆነ ስለ ጭነቱ የቀረበለትን ጥያቄ ሳይመልስ መቅረቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቀደም ብሎ ከአቡዳቢ ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ 2 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የጫነ መርከብ እአአ ግንቦት 6 የመከታተያ መሣሪያውን በማጥፋት አቋርጧል።
አሜሪካ እና ኢራን ከሁለት ወር በፊት የገቡበት ጦርነትን ተከትሎ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የነዳጅ፣ ጋዝ፣ ፔትሮል፣ ፕላስቲክ እና የምግብ ዋጋ ንሯል።






