የኢራን ሕግ አውጪዎች ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ላይ ለፈጸመችው ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu
ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ላይ እየቀዘፈ የነበረ የኢራን የንግድ መርከብ ላይ የድሮን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ አንድ ከፍተኛ የኢራን ሕግ አውጪ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ አስጠነቀቁ።
በኢራን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት የአጻፋ ምላሽ አለው ያሉት የሕግ አውጪው ይህንን አሜሪካ እና እስራኤል ያውቃሉ ብለዋል።
የኢራን ፓርላማ ብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ፖሊሲ ኮሚሽን ሰብሳቢ የሆኑት ኢብራሂም አዚዝ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልዕክት አሜሪካ እና እስራኤል “ማንኛውም በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ምንጊዜም ዋጋ እንደሚያስከፍል ያውቃሉ። ይህ ደግሞ ዛሬም እውነት ነው” ብለዋል።
አክለውም “ዩክሬን በቅርቡ ኢራን ድርጊቱ ምላሽ ሳያገኝ እንደማትተወው ትማራለች” ብለዋል።
አዚዝ “አሳንሰው የሚገምቱን ዝርዝር እየጨመረ ነው የመጣው” ብለዋል።
እሁድ ዕለት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ዩክሬን በኢራን የንግድ መርከብ ላይ የፈጸመችው ጥቃት የመንግሥታቱን ድርጅት ቻርተር የጣሰ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም በጥቃቱ አንድ ባህረተኛ መገደሉን አሳውቀው “ምላሽ ሳይሰጠው አይቀርም” ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ አገራቸው በካስፒያን ባሕር ላይ ረዥም ርቀት ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ “ጠንካራ ውጤቶችን” ማግኘቷን አስታውቀዋል።
አክለውም ጥቃቱ የተፈጸመው “ኢራን በተሳተፈችበት ወታደራዊ ጭነት በጫነች መርከብ ላይ” መሆኑን ተናግረዋል።

