ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል ጦር ሊባኖስ ውስጥ በድንግል ማሪያም ሐውልት ላይ በተሳለቀው ወታደር ላይ ምርመራ ጀመረ
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በደቡባዊ ሊባኖስ ሲጋራ እያጨሰ በድንግል ማሪያም ምሥል በተሠራ ሐውልት ላይ ሌላ ሲጋራ ሲያስቀምጥ በታየ ወታደሩ ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ።
ወታደሩ ድርጊቱን ሲፈጽም ፎቶ የተነሳው በደቡባዊ ሊባኖስ ክርስቲያኖች በሚኖሩበት ዴበል መንደር ውስጥ ነው።
ባለፈው ወር በዚህ ስፍራ ሌላ ወታደር የኢየሱስን ሐውልት በመዶሻ ሲመታ እና ሲያፈርስ የሚያሳይ ምሥል ተጋርቶ ነበር።
የእስራኤል ጦር ረቡዕ ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ክስተቱን በጥብቅ እንደሚመረምር ገልጾ ድርጊቱን የፈጸመው ወታደር "ከአባላቱ ከሚጠበቀው ዕሴት ሙሉ በሙሉ ያፈነገጠ ነው" ብሏል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቁጣን የቀሰቀሰው ይህ ፎቶግራፍ፣ ወታደሩ ራሱ ሲጋራ እያጨሰ በድንግል ማሪያም ሐውልት አፍ ላይ ሌላ ሲጋራ ሲያስቀምጥ ያሳያል።
ባለፈው ወር በዚሁ መንደር ውስጥ ሌላ የእስራኤል ወታደር የኢየሱስ ክርስቶስን ሐውልት በከባድ መዶሻ ሲሰብር የሚያሳይ ፎቶግራፍ በስፋት ተጋርቶ ሰፊ ውግዘት ማስከተሉ ይታወሳል።
በዴቤል የሚገኘው ቤተ እምነት ኃላፊ አባ ፋዲ ፌልፌሊ ለቢቢሲ "እውነቱን ለመናገር ይህ ጉዳይ በተለይ ስለ መስቀሉ ይቅርታ ከተጠየቅን በኋላ መሆኑ በጣም አስቆጥቶናል" ብለዋል።
"በተጨማሪም [በእስራኤል] ሠራዊት ውስጥ ሥነ ምግባር እና ዕሴት የጎደላቸው እንዲሁም ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ግለሰቦች እንዳሉ ያሳያል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ አክራሪነትን ያሳያል።"
አባ ፌልፌሊ የድንግል ማሪያም ሐውልት አሁንም ሳይበላሽ እና ሳይሰበር በስፍራው እንደሚገኝ አረጋግጠው፤ ነገር ግን የወታደሩን ድርጊት "ሥነ ምግባር የጎደለው" ሲሉ ጠርተውታል።
"በተለይም ሰላምን እና ገለልተኛነትን በሚመርጥ እንዲሁም በጦርነቱ ውስጥ በማይሳተፍ መንደር መታየት የሌለበትን ጽንፈኝነትን እና አለመቻቻልን የሚያንፀባርቅ ነው።"
የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተወካይ ድርጊቱን "አክብሮት የጎደለው እና አስጸያፊ ባህሪ" ሲሉ ማውገዛቸው ተገልጿል።
በአካባቢው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ኃላፊ ለእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ "የእስራኤል መንግሥት እና የመከላከያ ሠራዊቱ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ተቀባይነት እንደሌለው፣ ድጋሚ መፈጠር እንደሌለበት የሚያሳይ እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን። ጉዳዩን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያዩትም ጥሪያችንን እናቀርባለን" ሲሉ ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ናዳቭ ሾሻኒ ፎቶው የተነሳው ከጥቂት ሳምንታት በፊት መሆኑን በመግለጽ፣ በምርመራው ግኝቶች መሠረት በወታደሩ ላይ "እርምጃ" እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
በተጨማሪም "የመከላከያ ሠራዊቱ የሃይማኖት እና የአምልኮ ነፃነትን እንዲሁም የሁሉም ሃይማኖቶች እና ማኅበረሰቦችን ቅዱስ ቦታዎችን እንዲሁም የሃይማኖት ምልክቶችን ያከብራል" ብለዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስን ሐውልት በመዶሻ ያፈረሰው እና ድርጊቱን ፎቶግራፍ ያነሳው ወታደር ዓለም አቀፍ ውግዘት ከደረሰ በኋላ ለ30 ቀናት በወታደራዊ እስር ቤት እንዲቆዩ ተፈርዶባቸዋል።
በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ቢሆንም በሺዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ወታደሮች በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ ስፍራዎችን መቆጣጠራቸውን እንደቀጠሉ ነው።
በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከሄዝቦላህ ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም አልቻለም።
በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶች ላይ የእስራኤል ጦር ተደጋጋሚ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን ይናገራል።
በዚሁ ጥቃት የተነሳ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ120 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ እና በሰሜን እስራኤል በሚገኙ ወታደሮች ላይ ሮኬቶችን፣ ድሮኖችን እና ሞርታሮችን እንደሚተኩስ ተናግሯል።
የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ ረቡዕ ምሽት ለመጀመሪያ ጊዜ እስራኤል በቤይሩት ውስጥ ጥቃት ፈጽማለች።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በዳሂህ የተፈፀመው ጥቃት የሄዝቦላህ ከፍተኛ ጦር አዛዥ አህመድ አሊ ባውት መግደሉን ተናግሯል። ከሄዝቦላህ ግን ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አልተሰጠም።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሊባኖስ ቢያንስ 2,715 ሰዎች ተገድለዋል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት በደቡብ ሊባኖስ 17 ወታደሮች እና አንድ ሰላማዊ ዜጋ እንዲሁም በሰሜን እስራኤል ሁለት ሲቪሎች መገደላቸውን ተናግረዋል።