ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአይኤስ ተዋጊዎችን አግብተው ነበር የተባሉ ሴቶች ከሶሪያ ወደ አውስትራሊያ ተመለሱ
ከእስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) ጋር ግንኙነት ያላቸው 13 ሴቶች እና ሕጻናት በሶሪያ የእስር ማዕከል ውስጥ ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ ወደ አውስትራሊያ ቤታቸው ተመለሱ።
ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ አል ሮጅ በተባለው የእስር ካምፕ ውስጥ የነበሩት ሴቶች ጉዳይ አውስትራሊያ ውስጥ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ክርክር ያስነሳ ነው። የአገሪቱ መንግሥት እነርሱን ለመመለስ እገዛ እንደማያደርግ ገልጿል።
የአንድ ቤተሰብ አባል እንደሆኑ የሚታመኑት ሦስት ሴቶች እና ስምንት ሕጻናት ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ሜልበርን የደረሱ ሲሆን አንዲት ሌላ ሴት እና ልጇ ደግሞ ከቆይታ በኋላ ሲድኒ ውስጥ አርፈዋል።
ፖሊስ እንደገለጸው የተወሰኑት ሴቶች አውስትራሊያ ከደረሱ በኋላ እስር ይጠብቃቸዋል። ሌሎቹ ላይ ደግሞ "ምርመራ እንደሚቀጥል" አስታውቋል።
ሜልበርን የደረሱት አያት የሆኑት ካውሰር አባስ እንዲሁም የአዋቂ ዕድሜ ያላቸው ሁለት ልጆቻቸው እና ስምንት የልጅ ልጆቻቸው እንደሆኑ ዘገባዎች ጠቁማል።
የአባስ ባለቤት የሆኑት መሐመድ አሕመድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ይመራሉ። የአውስትራሊያ ፖሊስ ይህ ድርጅት ለአይኤስ ገንዘብ ያስተላልፋል የሚል ጥርጣሬ አለው። ግለሰቡ በ2019 ሶሪያ እስር ቤት ውስጥ ከተገኙ በኋላ ከአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ 'ኤቢሲ' ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ክሱን ውድቅ አድርገዋል።
ሲድኒ የደረሰችው ሌላኛዋ ሴት ጃናኢ ሳፋር እንደምትባል እና ሶሪያ ውስጥ ከተወለደ የዘጠኝ ዓመት ልጇ ጋር እንደመጣች የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ሲድኒ ውስጥ የነርስነት ትምህርት ስትከታተል የነበረችው ሳፋር በአውሮፓውያኑ 2015 ወደ ሶርያ የተገወዘች ሲሆን በዚያም የአይኤስ ተዋጊ የሆነው ሰውን እንዳገባች ተዘግቧል።
2019 ላይ ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ወደ ሶሪያ የተጓዘችው በራሷ ፈቃድ መሆኑን ተናግራለች። እታሰራለሁ እና ልጄ ይወሰድብኛል የሚል ፍርሃት ስላለባት ወደ አውስትራሊያ መመለስ እንደማትፈልግ ገልጻ ነበር።
የፖሊስ ኮሚሽነሯ ክሪሲ ባራት፤ ከተመሱት ሴቶች የተወሰኑት እንደሚታሰሩ እና ክስ እንደሚመሠረትባቸው አረጋግጠዋል። ሊቀርቡባቸው ከሚችሉ ክሶች መካከል ወደ ተፈረጁ ቦታዎች መግባት እና በዚያ መቆየት ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም የሽብርተኝነት ወንጀሎች እንዲሁም የባርያ ንግድ ውስጥ መሳተፍን የመሰለ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀልም ይገኝበታል።
ከሴቶቹ መካከል አንዷ ወደ ሜልበርን ሲጓዝ የነበረው አውሮፕላን ዶሃ ላይ በቆመበት ጊዜ ከኤቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራት ቆይታ ወደ ቤት ለመመለስ መጓጓቷን ገልጻለች። ለእነርሱ አውስትራሊያ "ልክ እንደ ገነት" መሆኗንም ተናግራለች።
የአውስትራሊያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ቶኖ ቡርኬ በበኩላቸው፤ "እነዚህ ሰዎች አደገኛ ሽብርተኛ ድርጅትን ለመቀላቀል እና ልጆቻቸውን ለመናገር በሚከብድ ሁኔተ ውስጥ በመክተት አስከፊ ውሳኔ መርጠዋል" ብለዋል።