ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳይ ፖሊስ ኖቤል መሰል ሽልማት ፈጥሮ ራሱን የሸለመው ምሁር ላይ ምርመራ ከፈተ
ከኖቤል ጋር የሚመሳሰል ሽልማት ፈጥሮ ራሱን የሸለመው ፈረንሳዊ ምሁር ላይ ምርመራ ተከፈተ።
ፍሎረንት ሞንታክሌር የተባለው ምሁር የፈጠረው ሐሰተኛ ሽልማት በፊሎሎጂ (የቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍ እና ታሪካዊ አመጣጡ ጥናት) ዘርፍ የሚሰጥ እንደሆነ ገልጾ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2016 ላይ በፓሪስ በተካሄደ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ምሁሩ ሽልማቱን ለራሱ ሰጥቷል። ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሚኒስትሮች እና የኖቤል ተሸላሚዎች ታድመው ነበር።
ይህ ሽልማት እንዲሁም ሽልማቱን ሰጥቷል የተባለው 'ኢንተርናሽናል ሶሳይቲ ኦፍ ፊሎሎጂ' አካልም ልብ ወለዳዊ ናቸው።
ምሁሩ ለ20 ዓመታት ያስተማረበት ዩኒቨርስቲ ከሥራ አባሮታል። ሐሰተኛው ሽልማት ላይም ምርመራ ተከፍቷል።
ጉዳዩን እየተከታተሉ ያሉት ዐቃቤ ሕግ ፖል-ኤዱዋርድ ላሎስ "ነገሩ ፊልም ነው የሚመስለው" ሲሉ ገልጸውታል።
ዐቃቤ ሕጉ እንደተናገሩት ምሁሩ ሐሰተኛውን ሽልማት ማስተዋወቅ የጀመረው በአውሮፓውያኑ 2015 ነው።
በሚያስተምርበት ዩኒቨርስቲ ጋዜጣ ላይ "ለኖቤል መታጨቱን" የሚገልጽ ዘገባ እንዲወጣ አድርጓል።
ታዋቂውን ዓለም አቀፍ ሽልማት ለማግኘት ከሚፎካከሩ አምስት ምሁራን አንደኛው እንደሆነ በዘገባው ተመልክቷል።
ከዚያም የሽልማቱ አሸናፊ መሆኑ ተገልጿል። ከወራት በኋላ ደግሞ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል።
በዚያው ዓመት ምሁሩ አሜሪካዊውን ፈላስፋ እና የቋንቋ ባለሙያ ኖም ቾምስኪ ወደ ብራሰልስ ጋብዞ ከሐሰተኛው ተቋም የወርቅ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
በወቅቱ ቾምስኪ 88 ዓመታቸው ነበር። የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ቪድዮም በበይነ መረብ ይገኛል።
በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከአውሮፓውያኑ 1967 አንስቶ በዘርፉ ታዋቂ የሆኑ ባለሙያዎች ዝርዝር ቀርቧል። ታዋቂውን ፈላስፋ እና ጸሐፊ ኡምቤርቶ ኢኮም ዝርዝሩ ውስጥ ተካትተዋል።
በአሜሪካ ዳላዌር ግዛት ከሚገኝ ዩኒቨርስቲ በፈረንሳይኛ ሥነ ጽሑፍ እና ሰዋሰው የዶክትሬት ዲግሪ ማግኘቱን ምሁሩ ቢናገርም ይህም ሐሰተኛ መሆኑ ተደርሶበታል።
ዐቃቤ ሕጉ "የፊሎሎጂ የወርቅ ሜዳልያው ሐሰተኛ ነው። ሽልማቱን ሰጠኝ ያለውን ድርጅትም የፈጠረው ራሱ ነው። የጠቀሰው ዩኒቨርስቲም በይነ መረብ ላይ ቢኖርም እውነተኛ አይደለም" ብለዋል።
ምሁሩ የፈጠረው ሐሰተኛ ተቋም በቀጣይ የሚሸልመው ሮማንያዊው የፊሎሎጂ ባለሙያ ዩጂን ሳይመን እንደሆነ ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው ነገሩ አጠራጣሪ መሆኑ መሰማት የጀመረው።
ሮማንያዊያን ጋዜጠኞች ባደረጉት ምርመራ እውነታውን ደርሰውበታል። የሮማንያዊው ባለሙያ መሸለም በአውሮፓውያኑ 2019 ይፋ ሲደረግ ፈረንሳይ ውስጥ አንዳችም ጥርጣሬ አልነበረም።
ምሁሩ አምና በፈረንሳይ ሐሰተኛ ዜናን የሚመለከት ውይይትን እንደሚመራ ሲገለጽ የሥራ ባልደረቦቹ ከሮማኒያ የሰሙትን ጭምጭምታ ማስተጋባት ጀመሩ።
የፈረንሳዩ ለ ሞንድ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ ፖሊሶች የምሁሩን ቤት ሲፈትሹ "ነገሩ ሜዳልያውን የተመለከተ ነው" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ሜዳልያውን ፓሪስ ከሚገኝ ጌጣ ጌጥ ሠሪ በ250 ዩሮ ነበር የገዛው።
"እያጭበረበርኩ አይደለም። በትምህርቱ ዓለም አዲስ ዕውቅና ለመፍጠር ነው የሞከርኩት። ሙከራዬም ከሽፋል" ብሏል።
የዐቃቤ ሕግ ቢሮ እያደረገ ያለው ምርመራ፤ ሐሰተኛው ሽልማት የምሁሩን የሥራ ሁኔታ አሳድጎ ከሆነ ይፈትሻል።
ምሁሩ የወንጀል ድርጊት ፈጽሟል የሚለውን ማሳየት ከባድ ሊሆን ይችላል።
ምሁሩ እንዳለው ከሆነ ሐሰተኛ ሽልማት መፍጠር ሕግ አይጻረርም። ሽልማቱን ኖቤል አስመስለው ያቀረቡትም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ናቸው ብሏል።