ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና በደህንነት ስጋት ምክንያት በቤይጂንግ ድሮን እንዳይሸጥ ልታግድ ነው
ቻይና ከነገ፣ አርብ ጀምሮ በቤይጂንግ ድሮኖችን እንዳይሸጡ ከለከለች። በተጨማሪም በከተማዋ ላይ ድሮን ለማብረር ፈቃድ እንደሚያስፈልግ የሚደነግጉ ሕጎች ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምሩ ተገልጿል።
ድሮኖችና እና ተያያዥ መሣሪያዎች በቤይጂንግ እንዳይሸጡ፣ እንዳይከራዩ ወይም ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ ተከልክሏል።
የድሮን ባለቤቶችም መሣሪያዎቻቸውን ለፖሊስ ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል።
ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የደህንነት ስጋትን በመጥቀስ በድሮኖች ላይ የምታወጣቸውን ደንቦች እያጠበቀች ነው።
የቻይና መንግሥት ድሮኖች እና በራሪ ታክሲዎች በትንሽ ከፍታ የሚበርሩ እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳልጡ መሆናቸውን በመግለጽ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።
ቻይና ከዚህ ዘርፍ እአአ በ2035 290 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዳለች።
በአንዳንድ የቻይና ከተሞች፣ ድሮኖች ለመስተንግዶ፣ ለግብርና እና ሕንፃዎችን ለማጽዳት ጥቅም ላይ ይውላሉ።
የቻይና ኩባንያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው አልባ አውሮፕላኖችን ገበያ ሊቆጣጠሩ ቢችሉም ነገር ግን አገሪቱ ለማብረር በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ ቦታዎች አንዷ እየሆነች ነው።
ድሮኖች ወደ ቤይጂንግ ከመግባታቸው እና ከመውጣታቸው በፊት መመዝገብ አለባቸው።
ተጠቃሚዎች ድሮኖቻቸውን ለጥገና ከከተማ ውጭ የሚልኩ ከሆነም መሳሪያውን ራሳቸው በአካል ተገኝተው እንዲረከቡ ይገደዳሉ።
በቤይጂንግ ከተማ ድሮኖችን ለማብረር በቅድሚያ ፈቃድ ማግኘት ይጠይቃል። የድሮን ተጠቃሚዎች በኦንላየን የሚሰጥ ስልጠናን ማጠናቀቅ እና የሚሰጥ ፈተናን ማለፍ አለባቸው።
ነገር ግን ለጸረ ሽብር ተግባር እንዲሁም ለአደጋ ጊዜ በባለሥልጣናት ፈቃድ ገዝቶ ማስቀመጥ ይቻላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቻይና በአገር ውስጥ ድሮንን ለመጠቀም የሚያገለግሉ ሕጎቿን እያጠበቀች መጥታለች።
በቤይጂንግ ድሮንን ማብረር የሚከለክለው ሕግ የጸደቀው በመጋቢት ወር ሲሆን የከተማዋ ባለሥልጣናት በዝቅተኛ ከፍታ የሚደረግ በረራ ደህንነት ላይ ላሉ "ተገዳሮቶች" የሚሰጠው ምላሽ መጠናከር አለበት ብለው ነበር።
የቤይጂንግ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ የሆኑት ዢዮንግ ጂንግዋ እንዳሉት ዓላማው በደህንነት፣ በቴክኖሎጂ እና በኢኮኖሚ እድገት መካከል ያለውን "ሚዛን መጠበቅ" ነው።
ባለፈው ዓመት የቤይጂንግ አጠቃላይ የአየር ክልል ለሰው አልባ አውሮፕላን ዝግ ተደርጎ ነበር።
በከተማዋ ሰማይ ላይ ድሮን ለማብረር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው አስቀድሞ ከአየር ትራፊክ ቁጥጥር ባለሥልጣናት ፈቃድ ማግኘት ያስፈልገዋል።
በቅርብ ጊዜ የተደነገጉት ደንቦች በቻይና ያለውን ግዙፍ የድሮን ገበያ ሊያውኩት ይችላሉ ተብሏል። በአገሪቱ መንግሥት መረጃ መሠረት ከሦስት ሚሊዮን በላይ የተመዘገቡ ድሮኖች አሉ።
ቻይና በዓለም ላይ ትልቁን የድሮን አምራች የሆነውን ዲጂአይን ጨምሮ የትላልቅ ኩባንያዎች መገኛ ነች።