ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዘመናዊት ኳታር 'አባት' ቢልየነሩ ሼኽ ሐማድ ቢን ኻሊፋ አል ታኒ ማን ነበሩ?
የቀድሞው የኳታር መሪ ሼኽ ሐማድ ቢን ኻሊፋ አል ታኒ በ74 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የዘመናዊት ኳታር መሥራች ተብለው የሚሞካሹት ሼኽ ሐማድ ከአባታቸው ሥልጣን የተረከቡት በአውሮፓውያኑ ሰኔ 1995 ነበር።
የሥልጣን ሽግግሩ 'ደም አልባ መፈንቅለ መንግሥት' በሚል ይታወቃል።
የኳታር 'አዘማኝ' ሼኽ ሐማድ አገሪቱ በምጣኔ ሃብት የበለጸገች፣ የዓለም አቀፍ ስበት ማዕከል እንድትሆን አስችለዋል።
በነዳጅ ሃብት የበለጸገችው ዘመናዊት ኳታር 'አባት' የሚባሉትም ያለ ምክንያት አይደለም።
አሁን ኳታርን የሚያስተዳድሩት ልጃቸው ሼኽ ታሚም ቢን ሐማድ አል ታኒ ናቸው። የኢሚሩ ጽሕፈት ቤት የቀድሞውን መሪ ሞት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ "አገራችን ታላቅ ሰው በማጣቷ አዝነናል" ብሏል።
በኳታር ለቀናት የሚቆይ ሕዝባዊ ሐዘን እንደሚኖር ተገልጿል።
ሰንደቅ ዓላማዎች በግማሽ ዝቅ ብለው ይውለበለባሉ።
ንጉሥ ቻርልስ እና ንግሥት ካማላ "ለረዥም ዓመታት ኳታርን በክብር ያገለገሉ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ሕንድ ብሔራዊ የሐዘን ቀን አውጃ መዝናኛ መሰናዶዎችን ሰርዛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ "ኳታርን ለእድገት እና ለብልጽግና ያበቁ ባለ ራዕይ መሪ" ብለዋቸዋል።
ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎችም ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ በማኅበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ "ኳታር እና አፍሪካ ከብልህ መሪዎች አንዱን አጥተዋል" ብለዋል።
በተለይም በአፍሪካ ቀንድ "ግጭቶች እንዲፈቱ፣ ሰላም እንዲሰፍን" አስተዋጽኦ እንዳደረጉ እና "ለድርድር መሠረት እንደጣሉ" ጠቅሰዋል።
ሼኽ ሐማድ ለኢትዮጵያ "ልዩ ትኩረት" እንደሰጡ እና ከኢትዮጵያ ጋር ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማዳበር ባለው ጠቀሜታ ያምኑ እንደነበር በጽሑፋቸው አትተዋል።
የቀድሞው የኳታር መሪ በአውሮፓውያኑ 2013 ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
ይህንን ጉብኝት በመጥቀስም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "የሁለቱን አገራት ግንኙት ትብብር የመሠረተ" እና "አዲስ ምዕራፍ የከፈተ" ብለውታል።
ልጃቸው በአውሮፓውያኑ 2017 በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት "የዚህ ጉዞ ተከታይ" መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
የዓለም ዋንጫን ወደ 'በረሃዋ አገር' የወሰዱት መሪ
በአውሮፓውያኑ 2022 የዓለም ዋንጫን ኳታር እንድታስተናግድ በማስቻል ሼኽ ሐማድ ስማቸው ይነሳል።
በእርግጥ ከዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ኳታር ውዝግቦች ገጥመዋታል። ግጥሚያው ከፍተኛ ተመልካች ካገኙ የዓለም ዋንጫዎች በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል።
ኳታር አስተናጋጅ አገር ሆና ከመመረጧ ጋር በተያያዘ የሙስና ክሶች ቀርበዋል። አገሪቱ በስደተኛ ሠራተኞች ብዝበዛም ተተችታለች።
ስቴድየሞችን እንዲሁም ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የገነቡ ስደተኛ ሠራተኞች አያያዝን በተመለከተ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ቅሬታ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም ዋንጫን ወደ 'በረሃዋ አገር' የወሰዱት መሪ በሚል ሼኽ ሐማድ ተሞካሽተዋል።
ኳታር 30,000 ስደተኛ ሠራተኞችን ቀጥራ ስቴድየሞች አስገንብታለች።
ከሕንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከባንግላዲሽ እና ከሲሪ ላንካ የሄዱ ሠራተኞች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ኳታር ህልፈታቸው ከዓለም ዋንጫ ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዘ አይደለም ስትል ክሶችን አስተባብላለች።
'ደም አልባ መፈንቅለ መንግሥት'
ሼኽ ሐማድ ቢን ኻሊፋ አል ታኒ ሥልጣን የያዙት ከ31 ዓመት በፊት ነበር። በወቅቱ ኳታር የነዳጅ ክምችቷ እየቀነሰ እንዲሁም የፋይናንስ ቀውስ ገጥሟትም ነበር።
አባታቸው ሼኽ ኻሊፋ ውጭ አገር ሳሉ 'ደም አልባው መፈንቅለ መንግሥት' ተካሄደ። አባታቸው ስዊትዘርላንድ ሳሉ ስልክ ደውለው ሥልጣኑን መውሰዳቸውን ነግረዋቸዋል። አገሪቷም እስከ ወዲያኛው ተለወጠች።
መሪነቱን ከያዙ በኋላ ኳታር የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ አገራት በመላክ ቀዳሚዋ አገር ሆናለች።
የዓለም አቀፍ ትብብሮች አካል መሆን እና የኢንቨስትመንት ስምምነቶችም ምጣኔ ሃብቷ እንዲያንሰራራ አስችለዋል።
ከቀዳሚ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አንዱ የሆነው አል ጀዚራን የመሠረቱት በአውሮፓውያኑ 1996 ነበር። የምዕራቡን ዓለም የመገናኛ ብዙኃን ትርክት በሚገዳደር ዘገባ ስመ ጠርም ነው።
ሼኽ ሐማድ ያቋቋሙት የኳታር ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን በውጭ አገራት ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ይታወቃል።
በዩናይትድ ኪንግደም፣ ለንደን የሚገኘው ቅንጡ መደብር ሃሮድስ፣ ባርክሌይስ ባንክ እና የፈረንሳዩ እግር ኳስ ቡድን ፒኤስጂ ከኢንቨስትመንቶቻቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
ኳታር እስከ 1971 ድረስ በእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳደር ሥር ነበረች። የአል ታኒ ቤተሰባዊ ሥርወ መንግሥት ከ1951 ጀምሮ አገሪቱን መርቷል።
'የዘመናዊት ኳታር አባት'
ሼኽ ሐማድ በአውሮፓውያኑ 1995 ሥልጣን ከያዙ በኋላ "የዘመናዊት ኳታር አርክቴክት" መሆናቸውን ብዙዎች ይጠቅሳሉ።
ሥልጣን በያዙ በዓመቱ የመገናኛ ብዙኃንን አፈና ማስወገዳቸው ይነገርላቸዋል።
በትምህርት፣ ኢንቨስትመንት እና የተፈጥሮ ነዳጅ ንግድ ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል።
በምጣኔ ሃብቱ ብቻ ሳይሆን በኳታር ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ለውጥ በማስመዝገብም ስማቸው ይነሳል።
በእሳቸው አስተዳደር ዘመን የኳታር ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት "ከ24 እጥፍ በላይ መጨመሩን" ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
በአውሮፓውያኑ 2006 ኳታር በፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ የውጭ ንግድ ከዓለም ቀዳሚዋ አገር ሆናለች።
የኳታር የመጀመሪያው ቋሚ ሕገ መንግሥት እንዲወጣ አድርገዋል።
በ2004 በተደረገው የአካባቢ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች መራጭ እንዲሁም ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ ፈቅደዋል።
ኳታር- አሸማጋይ አገር
ሼኽ ሐማድ የተወለዱት በአውሮፓውያኑ 1952 ዶሃ ውስጥ ነው።
የብሪትሽ ሮያል ሚሊተሪ ምሩቅ ሲሆኑ የኳታር ወታደራዊ ኃይልንም መርተዋል። በ1977 መከላከያ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ለልጃቸው ሥልጣን ያስረከቡት በ2013 ነበር። በባሕረ ሰላጤው አገራት ባልተለመደ መንገድ "ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር" እንደነበር ተነግሯል።
ልጃቸው ሥልጣኑን ሲረከቧቸው 33 ዓመታቸው ነበር። እሳቸው ደግሞ 61 ዓመታቸው ነበር።
ሼኽ ሐማድ ኳታርን "አሸማጋይ አገር" በማድረግም ይታወቃሉ።
የሱዳን ዳርፉር ግጭት፣ የሊባኖስ ተዋጊዎች ክፍፍል እንዲሁም የሐማስ እና ፋታህ ውዝግብ የአሸማጋይነት ሚና ከተጫወቱባቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
ኳታር በግዛቷ የአፍጋኒስታኑ ታሊባን ቢሮ እንዲከፍት በመፍቀድ በአሜሪካ እና ታሊባን መካከል ንግግር እንዲካሄድ ማገዟ ይታወሳል።
ኳታር የአረብ አገራትን ያቀጣጠለው የፀደይ አብዮት (አረብ ስፕሪንግ) ከደገፉ ጥቂት አገራት አንዷ ናት።
ሼኽ ሐማድ፤ የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት ባሻር አልአ ሳድ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሳይነሳባቸው በፊት ከሥልጣን እንዲወርዱ ለማግባባት ሞክረዋል።
በሊቢያ ሙአመር ጋዳፊን ከሥልጣን ለማስወገድ የሰሜን አትላንቲን ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ሲሰማራ ድጋፍ ሰጥተዋል።
የፍልስጤምን የነጻነት ትግል በመደገፍም ይታወቃሉ። በጋዛ እና በደቡብ ሊባኖስ የሚገኙ ከተሞች በስማቸው ተሰይመዋል።