ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን በሁቲ ታጣቂዎች ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ይሁንታቸውን መስጠታቸውን
የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ አክሲዮስ ዘገበ።
ሳዑዲ ሰኞ ዕለት በሰነዓ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን ይህንን ተከትሎ በኢራን የሚደገፉት
የሁቲ ታጣቂዎች እአአ ከ2022 ወዲህ ትልቅ ነው የተባለ የአጸፋ እርምጃ ወስደዋል።
ይህም ለአራት ዓመታት ዘልቆ የቆየውን ይፋዊ ያልሆነ የሰላም ስምምነት ያፈረሰ መሆኑ ተገልጿል።
የሳዑዲው ልዑል አስቀድመው ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት አገራቸው ከሁቲ ታጣቂዎች ጋር ባለው መጠነ ሰፊ ግጭት ዙሪያ ስጋት
እንደገባት እና የአሜሪካን ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንደምትፈልግ መጠየቃቸው ተገልጿል።
ሳዑዲ አረቢያ ይህንን ጠየቀችው ባለፈው ሳምንት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሐሙስ ዕለት በዋሺንግተን የሳዑዲ አምባሳደር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ጋር ተገናኝተዋል።
ከአንድ ቀን በኋላም ሩቢዮ የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሳል ቢን ፋርሃንን ጋር ተነጋግረዋል።
አርብ ዕለት ደግሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሳዑዲው ልዑል ጋር በስልክ ተወያይተዋል ተብሏል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሳዑዲው ልዑል በሁቲ ላይ የሚፈጸም ወታደራዊ እርምጃን አሜሪካ እንድትደግፍ ትራምፕን መጠየቃቸውን
ተናግረዋል።
ዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ቢጠየቅም በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም።
በዋሺንግተን የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲም በዘገባው ላይ ያለው ነገር የለም።
በሳዑዲ እና በሁቲ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ የተጀመረው ከአስር ቀን በፊት የኢራን አውሮፕላን ሁቲዎች በሚቆጣጠሩት ሰነዓ
አውሮፕላን ማረፊያ ካረፈ በኋላ ነው።
አውሮፕላኑ የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነስርዓትን ላይ ለመገኘት የሚሄዱ የልዑካን ቡድንን ጭኖ
መመለሱ ተገልጿል።
ሳዑዲ አረቢያ ከአስር ዓመት በፊት ከኢራን ወደ ሰነዓ የሚደረግ በረራን አግዳለች።
ሰኞ ዕለት የኢራን አውሮፕላን የልዑካን ቡድንኑን ይዞ ሲመለስ ሳዑዲ የሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያን ደብድባለች።
አውሮፕላኑ አቅጣጫውን ቀይሮ በአል ሁዳይዳህ ለማረፍ ተገድዷል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ የጦር መሣሪያዎችን፣ የሚሳዔል ክፍሎችን እና ወታደራዊ ባለሙያዎችን ጭኗል ሲሉ ከስሰዋል።
ሁቲዎች የሳዑዲ ጥቃትን ተከትሎ በደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ ወደሚገኘው አብሃ አውሮፕላን ማረፊያ ባሌስቲክ ሚሳዔል አስወንጭፈዋል።