ለሳምንታት ስኳር መመገብ ብናቆም በጤናችን ላይ ምን ለውጥ ይፈጠራል?

የፎቶው ባለመብት, BBC/ Getty Images
ስኳር የተጨመረባቸው ምግቦች የትም ነው ያሉት። አንዳንዴ በሚያስገርሙ ቦታዎች ላይ ጭምር እናገኛቸዋለን።
ታዲያ ከእነዚህ ምግቦች መቆጠብ ምን ያህል ቀላል ይሆናል? በጤናችን ላይስ ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል?
የቢቢሲ የሳይንስ ዘጋቢ ሜሊሳ ሁግንቡን ለስድስት ሳምንታት ስኳርን በመተው የተማረችውን ቁምነገር በዚህ ዘገባዋ አጋርታለች።
ብዙውን ጊዜ በቤት ወስጥ የሚዘጋጁ ጤናማ ምግቦችን ብመገብም ጣፋጭ ነገር እወዳለሁ ትላለች ሜሊሳ።
ጣፋጭ ቼኮላቶችን መመገብ ትፈልጋለች- ቢበዛ በቀን ሁለት ቼኮላቶች።
ይህ ለሜሊሳ የሚያስገርም አይደለም። ምክንያቱም በዘመናዊ የአመጋገብ ሥርዓታችን ስኳር ያላቸው ምግቦችን አብዝቶ መመገብ በጣም የተለመደ ነው።
ሆኖም እነዚህ ምግቦች ለጥርሳችን ብሎም ለጤናችን ጎጂ ናቸው።
ብዙ ስኳር ለረዥም ጊዜ የአእምሮ ብቃት ችግር ሊያጋልጥ እንደሚችል የሚያሳዩ አንዳንድ መረጃዎችም አሉ።
ሜሊሳ ሥራዋ ጤና እና ደኅንነት ጉዳዮች የሚመለከት ጭምር ስለሆነ የተቀነባበሩ እና ብዙ ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች ያላቸው ጣፋጮችን መመገብ ያሳስባት ጀምሯል።
በመደበኛነት የምትመገበው ጣፋጭ በቀን እንድትወስድ ከምትመከረው የስኳር መጠን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ይይዛል።
በአሜሪካ ያለው የአመጋገብ መመሪያ ከምግብ እና መጠጥ የምናገኘው የስኳር መጠን ከ12 የሻይ ማንኪያ ወይም ከ50 ግራም ያነሰ እንዲሆን ይመክራል።
በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት በቀን ከሰባት የሻይ ማንኪያ (30 ግራም) ያነሰ ስኳር መመገብን ነው የሚመክረው።
እንደ የአሜሪካ ብሔራዊ የጤና እና ሥነ ምግብ የዳሰሳ ጥናት ከሆነ በተግባር የአሜሪካ አዋቂዎች በቀን ከ16 እስከ 17 የሻይ ማንኪያ (ከ65 እስከ 70 ግራም) በላይ ስኳር ይመገባሉ።
አራት ግራም ማለት በአንድ የሻይ ማንኪያ ድርበብ ይሰፈራል።
ሜሊሳም ታዲያ ስኳርን በቀላሉ ማቆም ቀላል ባይሆንም በቀን ውስጥ የምወስደውን የስኳር መጠን ማቆም እችል እንደሆነ ለማየት ወሰንኩ ትላለች።
ለስድስት ሳምንታት ማንኛውንም የተቀነባበሩ ስኳር ያላቸው ምግቦች ላለመብላት ለራሷ ፈተና አስቀመጠች።
ማር እና የፍራፍሬ ጭማቂዎችንም ከምግቦቿ አስወጣች።
"ነገር ግን ከፍራፍሬ የማገኘውን ተፈጥሯዊ ስኳር እንዲሁም ካርቦሃይድሬት ያላቸው ምግቦች መመገቤን ቀጠልኩ" ትላለች።
ካርቦሃይድሬት ያላቸውን ምግቦች (ኃይል ሰጪ ምግቦችን) ስንመገብ ተሰባብረው ወደ ግሉኮስ የሚቀየሩ ሲሆን፣ ለሰውነታችን እና ለአንጎላችን ዋነኛ የኃይል ምንጭ በመሆን ይጠቅማሉ።
መጀመሪያ አካባቢ ባለኝ ኃይል (ጉልበት) የተወሰኑ ለውጦችን ተመለከትኩ የምትለው ሜሊሳ፣ ከምሳ በኋላ ይመጣ የነበረ ድካምም መጥፋቱን መስክራለች።
ነገር ግን የሆነ የምትመገበው ጣፋጭ ነገር አገኝ እንደሆነ እያለች ብዙ ጊዜ ራሷን ማቀዝቀዣው አካባቢ ታገኘው ነበር። የሆነ ነገር እንደጎደለ ነበር የሚሰማት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስኳር የትም ቦታ አለ
መጀመሪያ ላይ ምን ያህል ስኳር ምግባችን ውስጥ እንደተጨመረ ማወቅ ተገቢ ነው። ሜሊሳ ይህንን ስታደርግ አስገራሚ ነገር ነበር የገጠማት።
"በአካባቢዬ የሚገኝ የገበያ ማዕከል መደርደሪያ ስመለከት 5.7 ግራም ስኳር ያለውን የኮምጣጣ ዳቦ (ሳዎርዶ) ሳንዱዊች እና 9 ግራም ስኳር ያለው ተዘጋጅቶ የሚሸጥ በጣሊያን የተለመደ የሥጋ ሦስን ጨምሮ ባልጠበቅኳቸው ምግቦች ውስጥ ስኳር እንዳለ ተመለከትኩ" ትላለች።
ይህ ብቻም አይደለም።
ብዙ ጊዜ ለቁርስ የምንጠቀምባቸው አዝዕርቶች ስኳር ያላቸው ሲሆን፣ በየሱፐርማርኬቱ የሚሸጡ ዳቦዎችም በእያንዳንዱ ቀጭን ቁራጭ ውስጥ 1.2 ግራም ስኳር ነበራቸው።
ስኳር በተቀነባበሩ ምግቦች ውስጥም በብዛት ይገኛል። እነዚህ ምግቦች የተለያየ የጤና ጉዳት የሚያስከትሉ ሲሆን ከፍራፍሬ፣ ከአትክልት እና ከጥራጥሬ ያነሰ የምግብ ይዘቶችን የያዙ ናቸው።
እየወጡ ያሉ አዲስ ጥናቶችም ብዙ የስኳር መጠን ያላቸው ምግቦች ውጥረት እና ድብታን ጨምሮ የአእምሮ ጭንቀት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አሳይተዋል።
በምግቦቻችን ውስጥ ስኳርን በተለያየ ዓይነት መልኩም እናገኘዋለን።
ግሉኮስ የተለመደው ቢሆንም በፍራፍሬ እና ሲረፖች (ጣፋጭ ፈሳሾች) ውስጥ ፍሩክቶስ፣ በወተት ውስጥ ላክቶስ እና በገበታ ላይ በሚቀርበው ስኳር ሱክሮስ ይገኛል። ይህ 'ስኳር ያልተጨመረበት' እያልን የምንጠቀማቸውን ስኳር ይጨምራል።
ጭማቂዎች፣ ሲረፖች፣ ማር ሳይቀር ከስኳር ነፃ ተብለው ተደርድረው እናገናቸዋለን። ሆኖም እነዚህ የተቀነባበሩ ከስኳር ነፃ የሆኑ ምግቦች ለሚገጥሙን የጤና ችግሮች ብዙውን ድርሻ ይይዛሉ።
በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት አሽሊይ ጊርሃርዲት ጣፋጭ መውደድ ተፈጥሯዊ መሆኑን እና በማህፀን ውስጥ ሳለን እንዲሁም ከተወለድንም በኋላ ከእናት ጡት ወተት የምንለማመደው እንደሆነ ያስረዳሉ።
"ችግሩ ግን ጣፋጭ ምግቦችን በጣም ርካሽ በሆነ ዋጋ ማቅረብ ላይ ብርቱ መሆናችን ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስኳር ምን ያደርገናል?
ብዙ ስኳር ያላቸውን ምግቦች ስንመገብ በፍጥነት በደማችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በፍጥነት እንደሚጨምረው ጥናት ያመለክታል።
ከተመገብን በኋላ ይህ መከሰቱ የተለመደ ሒደት ቢሆንም ብዙ ጊዜ የሚከሰት ከሆነ ኢንሱሊን መቋቋም እንድንችል እና ለዓይነት ሁለት የስኳር ህመም የመጋለጥ እድላችን እንዲጨምር ያደርጋል።
ብዙ የስኳር መጠን ያላቸውን ምግቦች መመገብ ለጥርስ ህመም፣ ለሰውነት መቆጣት፣ ከልክ ላለፈ ውፍረት እና ለመርሳት በሽታ ብሎም ለካንሰር ሊያጋልጥ ይችላል።
"እንደ ስኳር ያሉ ከአመጋገብ ጋር የሚያያዙ በሽታዎች ከአልኮል እና ዕፅ በላይ ሰዎችን እየገደለ ነው። ጤናማ ያልሆነ ምግብ ከትንባሆ ጋር ሲነፃፀር በዓለም ገዳይ እየሆነ ነው" ይላሉ ጊርሃርዲት።
ለምሳሌ ስኳር የጉበት ስብን እንደሚጨምር ተደርሶበታል።
ተሳታፊዎች በክትትል ሥር እንዲሆኑ ተደርጎ በተሠራ አንድ ጥናት ከፍተኛ ስኳር ያላቸው መጠጦችን የወሰዱ ሰዎች ምንም እንኳን ተመሳሳይ የካሎሪ መጠን ቢወስዱም በጉበታቸው ያለውን ስብ በእጥፍ እንደጨመረው አሳይቷል።
ስኳር የሚያስከትለውን ጉዳትን በተመለከተ የተሠራውን ምርምር የመሩት ሮበርት ለስቲንግ በበቆሎ ሲረፕ የሚገኘው ፍሩክቶስ ሰውነታችን ተግባሩን እንዲያከናውን ለሚረዳው የኃይል ሥርዓት መርዛማ እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህም ድካምና መጫጫን እንዲሰማን እንዲሁም የአንጎል ሥርዓት መዛባት እና ትኩረት ማጣትን እንደሚጨምር አስረድተዋል።
ሜሊሳም ስኳር ባቆመችባቸው ሳምንታት በቀኑ አጋማሽ ላይ ያላት ጉልበት ጤናማ እንደነበር ተመልክታለች።
እየወጡ ያሉ ጥናቶችም ብዙ ስኳር ያላቸው ምግቦች ድብርት እና ውጥረትን ጨምሮ ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ ጭንቀትን እንደሚያስከትሉ አመልክተዋል።
ምንም እንኳን ይህ የሚያሳስብ ቢሆንም በጤናማ አመገጋብ ሥርዓት ስኳርን በመጠኑ መጠቀም ጥሩ ነው።
ሆኖም ከፍተኛ ስኳር ለሚጠቀሙ ሚሊዮኖች የሚወስዱትን መጠን መቀነሳቸው የጤና ጠቀሜታ አለው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሱስ የማስያዝ ባህሪያት
ሜሊሳ ራሷን ከስኳር ባራቀችባቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በተለይ በማኅበራዊ ፕሮግራሞች ላይ ጣፋጮች ሲቀርቡ መመገብ በጣም ያምራት ነበር።
ይህ የሚሆነበት ሥነ ሕይወታዊ (ባዮሎጂካል) ምክንያት አለው።
በአሜሪካ ቢንግሃምተን ዩኒቨርሲቲ የጤና እና ደኅንነት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሊና ቤግዳች ስኳር በምንመገብበት ጊዜ በተወሰነ መልኩ የአንጎላችንን ኬሚስትሪ ሊለወጥ ይችላል ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ አንጎል ምላሽ የሚሰጥበትን ሥርዓት ያነቃቃል።
ስኳር የመመገብ ጠንካራ ፍላጎት ያላቸው ወይም አምሮት ያላቸው ሰዎች እነዚህን ምግቦች በሚመገቡበት ወቅት ጥሩ ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርገውን የዶፓሚን ሆርሞናቸውን መጠን እንደጨመረው ጥናት አሳይቷል።
ይህም ቶሎ ቶሎ እንዲያሰኘን ያደርጋል።
በመሆኑም በርካታ ባለሙያዎች ስኳር ሱስ የማስያዝ ባህሪይ እንዳለው ያስባሉ። ይህ ግን አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
እንደ ፍራፍሬ ያሉ ተፈጥሯዊ ጣፋጮች ግን ለዶፓሚን ሆርሞን ሥርዓታችን ያን ያህል ተፅዕኖ አያሳድሩም ይላሉ ግርሃርዲት።
የስኳር ፍላጎታችን በመጨመረ ቁጥር ተጨማሪ እንድንፈልግ አእምሯችን ቶሎ ምላሽ ይሰጣል።
ይህም ዑደቱን በማጠናከር እና አእምሯችን የበለጠ እንዲፈልገው ሊያደርግ ይችላል።
ለምሳሌ በየዕለቱ ከፍተኛ የስኳር እና የስብ መጠን ያላቸውን ምግቦች ለስምንት ሳምንት እንዲመገቡ የተደረጉ የጥናት ተሳታፊዎች አእምሮ ለስኳር ምግቦች በከፍተኛ ሁኔታ ምላሽ ሰጪ ሆኗል።




































