እግራችንን በተደጋጋሚ ከሚያጋጥም ወለምታ እንዴት መጠበቅ እንችላለን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰውነታችን የሚያጋጥመው ንቅናቄ ዋነኛ ተቀባይ ናቸው። ሚዛንን ለመጠበቅ፣ ለመቆም፣ ለመራመድ እና ለመሮጥም እጅግ ወሳኝ ናቸው። ነገር ግን አብዛኞቻችን ጉዳት እስካልደረሰብን ድረስ ስለ ቁርጭምጭሚቶቻችን እምብዛም አናስብም።
እንዲህ ዓይነት ሕመም የሚያስከትሉ አደጋዎች እጅግ የተለመዱ መሆናቸውን የአካል ብቃት ፊዚዮቴራፒስት የሆኑት ጄኔቪቭ ታዊያ ይናገራሉ።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ድንገተኛ ሕክምና ክፍል ከሚገቡ ታካሚዎች ውስጥ አምስት በመቶው ከቁርጭምጭሚት ጋር የተያያዙ ጉዳቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
"ጠንካራ እና ስለ እግርዎ፣ ቁርጭምጭሚትዎ እና ተፅዕኖ ስለሚያሳድርበት የሰውነት ሰንሰለት የሚያውቁ ከሆነ" ግን እነዚህን ጉዳቶች ማስቀረት እንደሚቻል ታዊያ ያስረዳሉ።
ቁርጭምጭሚትዎን ለማጠንከር የሚረዱ ሦስት መንገዶች በዚህ ዘገባ ተዘርዝረዋል።
1. የአእምሮ እና የሰውነት ትስስርን ያጠናክሩ
ጠንካራ ቁርጭምጭሚት እንዲኖርዎት ለማድረግ እና የጉዳት ስጋትን ለመቀነስ የሚያስችለው ዋነኛ መሠረት "ከአእምሮ እስከ ሰውነት ግንዛቤ መኖር" እንደሆነ ታዊያ ገልጸዋል።
ይህም ማለት ወደ ታች አጎንብሰው እግርዎን ሳይመለከቱ ቁርጭምጭሚቶችዎ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነ በስሜት መረዳት መቻል ነው።
"ከአእምሯችን እስከ እግራችንና ቁርጭምጭሚታችን ድረስ መረጃ መላክ፤ በዚህም ቀጥሎ ለሚመጣው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጥሩ መሠረት መገንባት ነው" ይላሉ።
ታዊያ፣ የአእምሮ እና የሰውነት ግንዛቤን ለመፍጠር የሚያስችሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምሳሌዎችን ዘርዝረዋል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚሠሩት እግርን እየተመለከቱ ነው።
በትናንሽ የእግር ጣቶች እንቅስቃሴዎች መጀመርን የሚመክሩት ታዊያ፣ ይህንን ማድረግ "በቁርጭምጭሚት አማካኝነት [ክብደት] የምንሸከምበት መንገድ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይገልጻሉ።
ሁለቱ ምሳሌዎች እነዚህ ናቸው፦
- የአውራ ጣትዎን ጫፍ ወለል ላይ መጫን፣ ለተወሰነ ጊዜ ይዞ መቆየት እና የእግርዎ ቅስት (arch) ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሚኖረው መመልከት። "ይህ እንቅስቃሴ በእግርዎ ቅስት ውስጥ አንድ ነገር እየሳብዎት እንዳለ ዓይነት ስሜት ይፈጥራል" ይላሉ።
- ወለል ላይ ከአውራ ጣትዎ ጎን እና ትይዩ አድርገው እስክሪብቶ ማስቀመጥ፤ በመቀጠልም አውራ ጣትዎን ወደ እስክሪብቶው ለማንቀሳቀስ መሞከር፤ ይህም እንቅስቃሴ የጣት 'አብዳክሽን' ይባላል።
2. ጥንካሬን፣ ቁጥጥርን እና ሚዛን የመጠበቅ አቅምዎን ይገንቡ
ታዊያ እንደሚናገሩት፣ የቁርጭምጭሚት ሥራ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ፣ ክብደት እንድንሸከም እና ኃይልን እንድናስተላልፍ መርዳት ነው።
ጥንካሬን ለመጨመር ከሚደረጉ እንቅስቃወዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
- ተረከዝን ማንሳት - ጠንካራ ከሆነ መደገፊያ አጠገብ ቆመው፣ ተረከዝዎን ከወለሉ ላይ በማንሳት በጣቶችዎ ጫፍ ላይ ይቁሙ፤ በዚህ ጊዜ ቁርጭምጭሚቶችዎ እንደማይወዛወዙ ወይም ወደ ውጭ እንዳይወጡ ያረጋግጡ።
- ሚዛን መጠበቅ - የጂምናስቲክ ተወዳዳሪ በጠባብ አግዳሚ መስመር ላይ እንደሚራመድ ሁሉ፣ አንዱን እግር ከሌላኛው ፊት በማድረግ በአንድ መስመር ይራመዱ፤ የእግር ቁጥጥርዎንም ይጠብቁ።
- ቁጥጥር - አንዱን ወይም ሁለቱንም እግሮች በመጠቀም ከተቀመጡበት መነሳት እንዲሁም ደረጃዎችን መውጣት እና መውረድ የቁርጭምጭሚት ሚዛንን እና ቁጥጥርን ለማሻሻል ከሚያግዙ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች መካከል ናቸው።
ታዊያ፣ "ደረጃ ሲወጡ ሁልጊዜ በአንድ እግርዎ ቀድመው የሚወጡ ከሆነ፣ በሌላኛው እግርዎ ቀድሞ መውጣትን ይለማመዱ" በማለት ይመክራሉ።
ከእግር ወለምታ ጉዳት እያገገሙ ያሉ ሰዎች በአንድ እግር ቆመው ኳስን ወደላይ እየወረወሩ እና እየቀለቡ ሚዛናቸውን የመጠበቅ እንቅስቃሴን መስራት ይችላሉ። ወይም ወደ ግራ እና ቀኝ በመዝለል የሚያርፉበት እግር ላይ ሚዛናቸውን በመጠበቅ ቁጥጥራቸውን ማሻሻል ይችላሉ።
ከባድ የጅማት ሕመም ያለባቸው ሰዎች ደግሞ ቀስ ያለ እና ከባድ ጫና ያለው ልምምድ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ 'ሌግ ፕረስ' ማሽን ላይ ክብደት በመጨመር የባት ጡንቻን የማንሳት እንቅስቃሴን መሞከር ይችላሉ።
3. ትክክለኛውን ጫማ ያድርጉ
ትክክለኛውን የጫማ ዓይነት መምረጥ ቁርጭምጭሚትን ለመደገፍ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ታዊያ ይናገራሉ።
"ብዙ ሰዎች ጠፍጣፋ የባሌ ጫማዎችን፣ ጫፋቸው ሹል የሆኑ ጫማዎችን ወይም የፊት ክፍላቸው ጠባብ የሆኑ የስፖርት ጫማዎችን የማድረግ ልምድ አላቸው።
የጫማው የላይኛው ክፍል ባይኖር ኖሮ፣ ጣቶችዎ በቂ ቦታ ይኖራቸው ነበር ወይስ አውራ ጣትዎ ወደ ጎን ይገፋ ነበር ብሎ ማሰብ ጠቃሚ ነው" ይላሉ።
በባዶ እግር እየሄድን እንደሆነ እንዲሰማን የሚያደርጉ ጠፍጣፋ ጫማዎች ተወዳጅነታቸው እየጨመረ መሆኑን የሚያነሱት ታዊላ፣ "ጠቃሚም ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን እነርሱን ከመጠቀምዎ በፊት ጥሩ የእግርና የቁርጭምጭሚት መሠረታዊ ጥንካሬ መገንባት እና እግርን ቀስ በቀስ ማላመድ አስፈላጊ ነው" በማለት ያስረዳሉ።
በተጨማሪም የሚያደርጉት ጫማ "የእግር ቅስትን በተወሰነ መልኩ የሚደግፍ" እንዲሆን ይመክራሉ።
ይህንን ዓይነቱን ጫማ ማድረግ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ወቅት ክብደትዎን የሚሸከምበት መንገድ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አክለዋል።
የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተለያዩ ዓይነት ጫማዎች እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጸዋል።
"የስኳት እንቅስቃሴ የሚሠሩ ከሆነ፣ ምናልባት የሚያስፈልግዎት ጠፍጣፋ ጫማ ነው። ለስላሳ ስፖንጅ የመሰለ ሶል ያለው ጫማ ካደረጉ ሚዛንዎን ለመጠበቅ እና ክብደቱን በትክክለኛው ቦታ ላይ ለማሳረፍ አስቸጋሪ ይሆንብዎታል።
በአንጻሩ እየሮጡ ከሆነ ግን፣ ግጭትን ወይም ድንጋጤን ለመቀነስ ተጨማሪ ትራስ ድጋፍ የሚሰጥ የሩጫ ጫማ ይበልጥ ተስማሚ ሊሆን ይችላል" በማለት አብራርተዋል።
አክለውም፤ ወጣ ገባ በሆነ መሬት ላይ ለረዥም ጊዜ ለሚደረግ የእግር ጉዞ "የተራራ መውጫ ቡትስ ጫማዎች ማድረግ ከባድ የቁርጭምጭሚት መወዛወዝ ስጋትን በመቀነስ ጠቃሚ ናቸው። ይሁን እንጂ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ለረዥም ሰዓታት እነዚህን ጫማዎች ማድረግ የቁርጭምጭሚትን የመተጣጠፍ ችሎታ በተወሰነ ደረጃ ስለሚገድብ፣ የቁርጭምጭሚት መገተርን ሊያስከትል ይችላል" ብለዋል።



































