ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤአይ የሰው ልጆችን 'ሊያጠፋ' የሚችልባቸው አራት መላ ምቶች
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል የሚለውን ስጋት ባለሙያዎች ማስተጋባታቸውን ቀጥለዋል።
ኤአይ የሰው ልጆችን በቀጣይ አሥርታት ሊያጠፋ የሚችልበት ዕድል ከ10 በመቶ በላይ ነው የሚለው የቅርብ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ዓለምን አስደንግጧል።
በሌላ በኩል ደግሞ ትልቁ ስጋት ኤአይ ሰዎችን ያጠፋል የሚለው አይደለም ብለው የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ። ባለሙያዎቹ የበለጠ የሚያሳስባቸው የሰው ልጆች ኤአይን ተጠቅመው ሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ማስከተላቸው ነው።
ኤአይ ለሰው ልጆች የኅልውና ስጋት ነው የሚሉት ወገኖች ለወደፊት ይፈጠራሉ የሚሏቸው የተለያዩ መላ ምቶችን ያስቀምጣሉ።
የቢቢሲ የበይነ መረብ ዘጋቢ ጆ ቲዲ አራት መላ ምቶችን እንደሚከተለው አስቀምጧል።
መላ ምት አንድ- መሠረተ ልማቶችን 'ሀክ' ማድረግ
ለወደፊት ሊፈጠሩ ይችላሉ ተብለው ከሚገመቱ ሁኔታዎች የመጀመሪያውን ያስቀመጠው ጄኮብ ኮክስን ነው።
በኦፕንኤአይ እና በአንትሮፒክ የቀድሞ ተማራማሪ የነበረው ጄኮብ፤ ኤአይ ለሰው ልጆች ኅልውና አደጋ መሆኑን ተናግሯል።
ባለሙያው ከአንድ ወር በፊት ከአንትሮፒክ ኩባንያ ሥራውን ለቅቋል። የኤአይ ኩባንያዎች "በሰዎች ሕይወት ላይ ቁማር እየተጫወቱ ነው" ሲልም ተችቷል።
ኤአይ እያደገበት ያለው "ከፍተኛ ፍጥነት" ከዚህ ቀደም በሳይንሳዊ ልብ ወለዶች ላይ ይታይ የነበረን ፈጠራ "እውነት እያደረገ" መምጣቱን ባለሙያው ይናገራል።
"ለምሳሌ ዓለም ላይ ለሚደረግ እንቅስቃሴ መሠረት የሆኑ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ ኤአይ የበይነ መረብ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል" ብሏል።
ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ኤአይ፤ የኢንተርኔት አቅርቦት እና የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች የሚዘወሩባቸው የኮምፒውተር ሥርዓቶች ውስጥ ሰርጎ ሊገባ እንደሚችልም ያስረዳል።
ኤአይ ሁሉንም መሠረተ ልማቶች ቢዘጋ፤ መብራት፣ ኢንተርኔት እና የሙቀት መቆጣጣጠሪያዎች አገልግሎት ያቆማሉ።
ከዚህም በላይ የከፋ የሚሆነው የኒውክሌር ቀውስ የሚከተልበት ዕድል መኖሩ ነው።
መላ ምት ሁለት- ኤአይ ሁሉንም ነገር ሲቆጣጠር
ሁለተኛው መላ ምት መነሻው በአውሮፓውያኑ 2025 ይፋ የተደረገ ጥናት ነው።
የኤአይ ባለሙያዎች የሠሩት ዝርዝር ይዘት ያለው እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነው 'ኤአይ 2027' የተባለው ጥናት ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ያስቀምጣል።
ከፀሐፊዎቹ አንዱ ቶማስ ላርሰን ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ ይህ ሪፖርት ከወጣ በኋላም የቴክኖሎጂው እድገት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። በጣም የሚያስፈራውን ሁኔታም እንዲህ ይገልጻል።
"ኤአይ በፍጥነት ራሱን እያሻሻለ ነው። በምጣኔ ሃብት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዙት እና አብዛኛውን ሥራ የሚያከናውኑት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሮቦቶች በኤአይ ቁጥጥር ሥር ናቸው። ነገር ግን እንደ ወዳጆቻችን ልናያቸው አንችልም።"
ባለሙያው እንደሚለው ኤአይ በሒደት "መሣሪያዎች ፈጥሮ አብዛኛውን ሰዎች ሊገድል እና በሮቦት የሚዘወረውን ምጣኔ ሃብት በራሱ ሊመራ" ይችላል።
በዚህ ውስጥ "ሰዎች ከዚህ በኋላ አስፈላጊ አይደሉም" በሚል እርምጃውን ሊወስድ እንደሚችልም ያስረዳል።
መላ ምት ሦስት- ኤአይ ግቡን ሲለውጥ
ሦስተኛው መላ ምት መነሻው ከ20 ዓመት በፊት በስዊድናዊው ፈላስፋ ኒክ ቦስትሮም የተሠራ ምናባዊ ምርምር ነው።
በዚህ ምናባዊ ምርምር ኤአይ በቻለው መጠን የወረቀት ማጣበቂያ ብረት እንዲያመርት ተጠየቀ።
ኤአይ የወረቀት ማጣበቂያ ብረቱን በተቻለው መጠን እንዲያመርት ስለታዘዘ በማንኛውም መንገድ ይሁን ትዕዛዙን ለመወጣት ሞክሯል።
በምድር ላይ የሰው ልጆች ባይኖሩ የቻለውን ያህል ማምረት እንደሚችልም አምኗል።
"ኤአይ አይጠላንም፤ አይቀየመንም። ነገር ግን አንድ ግብ ሲኖረው ያንን ግብ ለማሳካት ብቻ ይሠራል። የበለጠ ኃያል የመሆን ወይም ራሱን ከፍተኛ ልኅቀት ላይ የማድረስ ዓላማ ይኖረዋል" ሲል ፈላስፋው ያስረዳል።
ወረቀት ማጣበቂያ ብረት ማምረትም ይሁን ሌላ ዓይነት ግብ ሲሰጠው ያንን ግብ እውን ለማድረግ ሲል "የሰው ልጆችን ማጥፋትን" ጨምሮ ሌሎችም እርምጃዎች ሊወስድ ይችላል።
ይህንንም "የትኛውም ሰው ሊያስቆመው እንደማይችል" ይናገራል።
ኤአይ ለሰው ልጆች አደጋ የሚሆንበት ነጥብ ላይ የሚደርሰው አንዳች "እኩይ ዓላማ" ስለተሰጠው ሳይሆን ማንኛውንም ግብ ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ እንደሆነ ይገልጻል።
ኤአይ ያለው አቅም አጓጊ ቢሆንም አደጋው ያሰጋዋል።
መላ ምት አራት- የማይታወቀው ዓለም
ሌላኛው ከኤአይ ደኅንነት ጋር የሚያያዘው ዕሳቤ፤ ቴክኖሎጂው ለምን እና እንዴት የሰው ልጆችን ሊገድል ይችላል ብሎ ለመተንበይ መሞከር ትርጉም የለውም ይላል።
ይሄንን ነጥብ ያነሳው የዓለም አቀፍ የኤአይ ደኅንነት ጥበቃ ማኅበር ፕሬዝዳንት ስቱዋርት ረስል ነው።
"ለምሳሌ ዝንጀሮዎችን ጋር ሄደን የሰው ልጆች እንዴት ሊያጠፏችሁ ይችላሉ? ብለን ብንጠይቅ መልስ አናገኝም። ምክንያቱም ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ለዝንጀሮዎች ግልጽ አይደለም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ስለ ኤአይ ብዙ መላ ምቶች ማስቀመጥ ቢቻልም ከሰው ልጆች ልህቀት የበለጠ ክህሎት ያለው መሣሪያ ከተፈጠረ በኋላ ለወደፊት ምን ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አይቻልም።
የማይክሮሶፍት ኤአይ ኃላፊ ሙስጠፋ ሱሌይማን እንደሚለው፤ የቴክኖሎጂ ተቋማት ገንዘብ ለማግኘት እና ሃብት ለማካበት በሚል የራሳቸውን ዓላማ ኤአይ ላይ መጫናቸው አስጊ ነው።
"ምንም ያህል ለሰው ልጆች ቢሳሳልን እና ቢወደንም እንኳን ከሰዎች ጋር ለግብዓት የሚፎካከር ነገር መፍጠር ማለት ነው" ይላል።
መላ ምቶቹ እውን ይሆናሉ?
ከላይ የተጠቀሱት መላ ምቶች ጨለምተኛ እና ሳይንሳዊ ልብ ወለድ የሚመስሉ ናቸው። አንዳንድ የኤአይ ባለሙያዎች አንዳንዶቹ መላ ምቶች እውን ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ።
የኦፕንኤአይ፣ አንትሮፒክ እና ሜታ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሞዴሎች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው የበይነ መረብ ጥቃት ማድረሳቸው በርካቶችን አስግቷል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ለዚህ ተጠያቂዎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቹ ናቸው።
የቀድሞው የአሜሪካ የበይነ መረብ ደኅንነት ኃላፊ እና አሁን ላይ የዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ደኅንነት ኮንፍረንስ መሪ የሆነችው ጄን ኢስተርሊ "እነዚህ የማይደክማቸው እና የተሰጣቸውን ግብ የሚያሳድዱ ማሽኖች ሥራ የሚያከናውኑት ዲዛይን በተደረጉበት መንገድ ነው" ትላለች።
ስለዚህም የቴክኖሎጂው ፈጣሪዎች ኤአይን ዲዛይን ሲያደርጉ እና ሲሞክሩ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለደኅንነት ጥበቃ መሆኑን ታሳስባለች።
ለረዥም ጊዜ የኤአይ ኩባንያዎችን ሲተች የቆየው ሳይንቲስት እና ፀሐፊ ጌሪ ማርከስ እንደሚለው ተቋማቱ ግልጽነት በጎደለው እና ሕግ በማይገዛው መንገድ ይሠራሉ።
በእርግጥ ቴክኖሎጂው የሰው ልጆች ያጠፋል ብሎ አያምንም።
"ኤአይ የሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ቢፈልግ እንኳን ሰዎች መታገላቸው አይቀርም" ይላል።
የሰው ልጆች የመጥፋት ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው ይናገራል። ሆኖም ግን ትኩረት ሊደረግ የሚገባው የሰው ልጆች ኤአይን በመጠቀም የሚያደርሱት የበይነ መረብ ጥቃት ነው ይላል።
ኦፕንኤአይ፣ አንትሮፒክ እና ሜታ የኤአይ እድገትን እንዴት ማዝገም እንደሚቻል ውይይት እያደረጉ ነው።
ተመራማሪው ቶማስ ላርሰን "የኤአይ ደኅንነት በስተመጨረሻ የሚገባውን ትኩረት ስላገኘ በጣም ደስ ብሎኛል" ሲል ይገልጻል።
"በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅሬታ መነሳቱ ፖሊሲዎች እንዲወጡ እና አደጋው እንዲቀንስ ይረዳል" በማለትም ያክላል።
ዓለም አቀፍ ሕግ ማውጣትን በተመለከተ ውይይቶች ቢጀመሩም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኤአይ ለሰው ልጆች ኅልውና ስጋት ነው የሚለውን "ሐሰተኛ" ሲሉ አጣጥለዋል።