የአሜሪካ ቴክኖሎጂ መሪዎች እየፈጠነ ያለው የኤአይ እድገት እንዲዘገይ ጠየቁ፤ ቻይናስ ምን ትላለች?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እድገት እጅግ ፈጣን በሆነበት በዚህ ወቅት፣ አንዳንድ የዘርፉ ታዋቂ መሪዎች ቴክኖሎጂው ሊያስከትላቸው ስለሚችሉ አደጋዎች ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎችን እየሰጡ ነው።

የአንትሮፒክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሪዮ አሞዴይ የኤአይ ልማት ፍጥነት ሊቀንስ ይገባል ያሉ ሲሆን፣ የሁለት ተፎካካሪ የኤአይ ኩባንያዎች መሪዎች የሆኑት የኦፕንኤአይ ሳም አልትማን እና ኢሎን መስክ በሀሳቡ እንደሚስማሙ ተናግረዋል።

እንደ ሲሊከን ቫሊ ያሉ ተቋማት ባለሙያዎች ደግሞ ቴክኖሎጂው አንድ ቀን የሰው ልጅ ኅልውናን ሊያሰጋ እንደሚችል እስከመናገር ደርሰዋል።

ሆኖም እነዚህን አደጋዎች ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች፣ በሁለቱ የዓለም የኤአይ ኃያላን አገራት ቻይና እና አሜሪካ መካከል ባለው ከፍተኛ ፉክክር ምክንያት ውስብስብ ሆነዋል።

እነዚህ ሁለት አገራት ስትራቴጂያዊ ተፎካካሪዎች እንደመሆናቸው፣ በኤአይ ዘርፍ የሚኖር እድገትን በአብዛኛው ከብሔራዊ ደኅንነት እና ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም አንፃር ስለሚመለከቱ በሁለቱ መካከል ትርጉም ያለው ትብብር ማድረግ መቻሉ ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል።

በኦስሎ የሰላም ምርምር ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ኢላሪያ ኮሮዛ፣ "ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አሜሪካ እና ቻይና በውይይት አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ ሊያደርጉ ይችላሉ ብሎ የሚጠብቅ ከሆነ፣ ሊያዝን ይችላል" ይላሉ።

ኤአይ "በሰው ቁጥጥር ስር መቆየት አለበት"

ቻይና ትልቅ የኤአይ ዕቅድ አላት። ወደፊት ቴክኖሎጂው ከግብርና እና ከጤና እንክብካቤ ጀምሮ እስከ ወታደራዊ ዘርፍ ድረስ በማኅበረሰቡ እና በኢኮኖሚው ሁሉም ዘርፎች ውስጥ እንዲዋሃድ ትፈልጋለች።

ሆኖም የአገሪቱ መንግሥት ኤአይ ሊያስከትላቸው ስለሚችላቸው አደጋዎች ለረጅም ጊዜ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ፣ ኤአይ የግል ምሥጢሮችን፣ ማኅበራዊ መረጋጋትን እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ሊያሰጋ እንደሚችል ሲገልፅ ነበር።

ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት፣ ቻይና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በኤአይ የተፈበረኩ ይዘቶች ግልፅ ምልክት እንዲደረግባቸው ግዴታ ጥላለች። እንዲሁም ህጻናት ኤአይ ላይ የተመሠረቱ ምናባዊ ጓደኞች እንዳይኖሯቸው ከልክላለች፤ በተጨማሪም የተሳሳተ መረጃ ለማሠራጨት የዲፕፌክ (የውሸት ይዘቶች ፍብረካ) ቴክኖሎጂ መጠቀምን አግዳለች።

በኤአይ ጉዳዮች ላይ በተደረጉ መደበኛ ያልሆኑ የአሜሪካ እና የቻይና ውይይቶች ላይ የተሳተፉት የሆንግ ኮንግ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ዜንግ ጂንግሃን እንደሚሉት፣ ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር ሲነፃፀሩ የቻይና መንግሥታዊ ተቋማት እና የፖሊሲ አማካሪዎች "ተቀባይነት ያለው የኤአይ ልማት ምን እንደሆነ የመወሰን ከፍተኛ ሥልጣን አላቸው"።

ኤአይ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል ለሚለው ስጋት የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ሐምሌ ወር ላይ በሰጡት ማስጠንቀቂያ "ኤአይ ሁልጊዜው በሰው ቁጥጥር ስር መቆየት አለበት" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት፣ በኤአይ አስተዳደር ላይ ዓለም አቀፍ ውይይትን ለማበረታታት በቻይና የተቋቋመው የዓለም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ትብብር ድርጅት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነበር።

የቻይና የበይ ነመረብ ተቆጣጣሪ ተቋም በመስከረም ወር ባሳተመው አዲሱ የኤአይ ደኅንነት ማዕቀፉ ውስጥ፣ ኤአይ "የሰው ልጅን ኅልውና እና እድገት" እንዳያሰጋ ለመከላከል የሚረዱ ፖሊሲዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጿል።

ኤአይ ሊቆጣጠሩት የሚቻል ቴክኖሎጂ ነው?

ምንም እንኳን የቻይና ባለሥልጣናት ኤአይ ከሰው ቁጥጥር ውጭ ሊወጣ ይችላል የሚለውን ስጋት ቢያምኑም፣ ቴክኖሎጂው በሰው ልጅ ኅልውና ላይ ሊያስከትል ስለሚችለው ከፍተኛ አደጋ የሚደረገው ውይይት ከአሜሪካ አንጻር በቻይና ያለው ትኩረት አነስተኛ ነው።

ቤይጂንግ ይህን አደጋ በመንግሥት ፖሊሲዎች ሊፈቱ ከሚገቡ ብዙ ጉዳዮች መካከል እንደ አንዱ ነው የምትመለከተው።

"በቻይና የኤአይ አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ እድገትን መደገፍ፣ የቴክኖሎጂ እና የማኅበራዊ አደጋዎችን መቆጣጠር፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ሥልጣንን ማስጠበቅን ለመሳሰሉ በርካታ ዓላማዎች በአንድ ጊዜ ይውላል" ሲሉ ፕሮፌሰር ዜንግ ተናግረዋል።

የሼንዤን የኤአይ እና ሮቦቲክስ ተቋም ዳይሬክተር ሻኦሻን ሊው "በቻይና የሚደረጉ ውይይቶች በአብዛኛው በኤአይ ቁጥጥር፣ የተሳሳተ አጠቃቀም እና በማኅበራዊ ተፅዕኖዎቹ ላይ ሲያተኩሩ ናቸው።

በአንፃሩ በአሜሪካ ያሉ ውይይቶች ደግሞ ኤአይ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል ወይም የሰው ልጅን ሊያጠፋ ይችላል በሚሉ ግምታዊ ሁኔታዎች ተጽእኖ ስር ወድቀዋል" የሚለውን ሃሳብ ይጋራሉ።

"በኤአይ የሚያሸንፍ በሁሉም ያሸንፋል"

ከኤአይ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ጠንካራ የጂኦፖለቲካ ገጽታም አላቸው።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኤአይ ልማትን ከቻይና ጋር እየተደረገ ያለ ከፍተኛ ፉክክር አድርገው ይገልፃሉ።

"በኤአይ ዘርፍ ቻይናን እየመራናት ነው... እና እውነት ለመናገር ይህ እንዲቀጥል እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም በኤአይ የሚያሸንፍ ሁሉንም ያሸንፋል" ሲሉ ተናግረዋል።

በቻይና መንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኝ አንድ መጽሔት በቅርቡ ባተመው ጽሑፍ የተጠቀሱት የቻይና ከፍተኛ የስለላ ኃላፊ ቼን ይዢንም እንዲሁ ኤኤእን ከጂኦፖለቲካዊ ዕይታ አንጻር ገልጸውታል። ኤአይን "በኃያላን አገራት መካከል ላለው ስልታዊ ፉክክር አዲስ መድረክ" በማለት ነበር የገለፁት።

የኤአይ ልማት ፍጥነት እንዲቀንስ የሚደረጉት ጥሪዎች በአብዛኛው ከአሜሪካ የቴክኖሎጂ ዘርፍ መሪዎች እንጂ ከመንግሥት ባለሥልጣናት የሚመጡ ባይሆኑም፣ በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር ቤይጂንግ እነዚህን ጥሪዎች በጥርጣሬ እንድትመለከት አድርጓታል።

በነሐሴ ወር የአንትሮፒክ መሥራች አባል አሞዴይ ስለ ኤአይ አደጋዎች ማስጠንቀቂያ ከመስጠታቸው ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ፣ የቻይና መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን ኩባንያቸውን ከአሜሪካ የጂኦፖለቲካ ጥቅሞች ጋር በማያያዝ ከሷቸዋል።

በመንግሥታዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲሲቲቪ የሚተዳር የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን "የአሞዴይ አስተሳሰብ ተለውጧል...'አገሬ ትክክል ናት' ከሚለው 'የማይተባበሩ ሁሉ መጨቆን አለባቸው' ወደሚል ተሸጋግሯል" ሲል ጽፏል።

የአንትሮፒክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በቅርቡ የኤአይ ልማት ፍጥነት እንዲቀንስ ያቀረቡት ጥሪ የቻይናን የኤአይ እድገት ለማደናቀፍ ወይም ለመገደብ ያለመ እንደሆነ ነው በመገናኛ ብዙኃኑ የተወሰደው።

በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ጥርጣሬና አለመተማመን ቢቀጥልም፣ ከቀናት በፊት የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ በዋሽንግተን ጉብኝት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በነበራቸው ውይይት ኤአይ ከተነሱ ዋና አጀንዳዎች መካከል አንዱ እንደነበር ተነግሯል።