ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኦነሠ በሽርካ ወረዳ "ሌሎች ታጣቂ ኃይሎችም ጥቃቶች" መፈጸማቸውን በመግለጽ "ኃላፊነት ወስዷል" መባሉን አስተባበለ
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ወረዳ "እርምጃ" ከወሰደ በኋላ "ሌሎች ታጣቂ ኃይሎችም ጥቃቶች" ፈጽመዋል ሲል ከሰሰ።
ታጣቂ ቡድኑ ከ40 በላይ ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት "ኃላፊነት ወስዷል" መባሉን ትናንት አርብ ኅዳር 11 ቀን 2019 ዓ.ም. ባወጣው ማብራሪያ አስተባብሏል።
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጥቅምት ላይ በቀድሞው አርሲ ዞን የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ከዚህ ቀደም ያወጣው መግለጫ "በተዛባ መንገድ እንደተተረጎመ" ገልጿል።
ኦነሠ፣ ጥቅምት 18 ቀን የተፈጸመውን እና ከ40 በላይ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት በተመለከተ ሰኞ ዕለት መግለጫ አውጥቶ ነበር።
ነዋሪዎች፣ በዕለቱ በሽርካ ወረዳ ቦርቢና ጮሌ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት "ቢያንስ አምስት ሕጻናትን" ጨምሮ 46 ሰዎች መገደላቸውን በወቅቱ ተናግረዋል።
ሁለት የተለያዩ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በከፈተው ጥቃት 41 ያህል ሰዎች ተገድለዋል ሲል ከስሷል።
የተገደሉትም "23 በቀበሌ ደረጃ የተደራጁ ጸጥታ አካላት፣ 5 የሚሊሻ አባላት እንዲሁም 13 ሰላማዊ ሰዎች" እንደሆኑ ገልጿል።
የኢሰመኮን ሪፖርት ውድቅ በማድረግ ሰኞ ዕለት መግለጫ ያወጣው ታጣቂ ቡድኑ፣ በዕለቱ "እርምጃ' መውሰዱን ገልጾ፣ የተገደሉት ግን "መደበኛ ነዋሪ የሆኑ የትርፍ ጊዜ ተዋጊዎች" ብሏል።
"የወደቁት ሲቪሎች በመከላከያ ሠራዊት እና በፀረ ሽምቅ ኃይሎች ከግል ሕይወታቸው ተመልምለው የወጡ የትርፍ ጊዜ ተዋጊዎች ነበሩ" በማለት አክሏል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ከዚህ መግለጫ ጋር በተያያዘ "ለተሰጡ የተዛቡ ትርጓሜዎች" ምላሽ ለመስጠት ትናንት አርብ ማብራሪያ አውጥቷል።
መገናኛ ብዙኃን "የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሲቪሎችን መግደሉን ኃላፊነት እንደወሰደ አድርገው መተርጎማቸውን በጽኑ" ተቃውሟል።
ኦነሠ ጥቃት የፈጸመው "በመንግሥት መደበኛ የጸጥታ ኃይሎች ትዕዛዝ" የሚንቀሳቀሱ፣ "የታጠቁ ሲቪሎች" በነበሩበት "የወታደራዊ ስምሪት ካምፕ" ላይ መሆኑን ገልጿል።
ታጣቂ ቡድኑ በቀደመው መግለጫው፣ "በግጭቱ ወቅት እና በኋላም የሲቪሎች ሞት መከሰቱን ቢያረጋግጥም፣ [የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት] ያልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ጥቃት ፈፅሟል አላለም" ሲል አስተባብሏል።
በዕለቱ በፈጸመው ጥቃት ዒላማ ያደረገው "ከመንግሥት ኃይሎች ጎን በግጭቱ ውስጥ በቀጥታ የሚሳተፉ ታጣቂዎችን" እንደሆነ በማብራሪያው አስፍሯል።
"የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከአካባቢው ከወጣ በኋላ" ጥቃቶች እንደቀጠሉም አክሏል። "[የ]ኦነግ–ኦነሠ ተዋጊዎች ከአካባቢው ከሄዱ በኋላ ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ጥቃቶች ውስጥ ተሳትፈዋል" ሲልም ለይቶ ያልጠቀሳቸውን አካላት ከስሷል።
የሰኞ ዕለቱን መግለጫ ተከትሎ ታጣቂ ቡድኑ "ኃላፊነት ወሰደ" የሚል ዘገባ መውጣቱ፣ "ኦነሠ ባልነበረበት የተፈጸሙ ጥቃቶችንና የደረሱ ጉዳቶችን በሙሉ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ላይ ማላከክ ነው" ሲል ተቃውሟል።
አክሎም፣ "በአርሲ የተፈጸሙትን ክስተቶች በሙሉ የሚመለከት ታማኝ፣ ነፃና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ" ጥያቄ አቅርቧል።
ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቅምት 24 ቀን ባወጣው መግለጫ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወደ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ "በአራት አቅጣጫ በመግባት" ጥቃት ማድረሱን በመግለጽ ከስሶ ነበር።
በዕለቱ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት "በአካባቢው በታጠቁ ኢመደበኛ በሆኑ ታጣቂ ግለሰቦች ሰባት ሲቪል ሰዎች የተገደሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል" ብሏል።
ቢቢሲ በወቅቱ ያነጋገራቸው ሁለት ነዋሪዎች ከ40 በላይ ሰዎች ከሞቱበት ጥቃት በኋላ፣ "የእስልምና እምነት ተከታይ" የሆኑ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ፣ 46 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ያነጣጠረው ምዕመኖቿ ላይ መሆኑን ገልጻለች። በሽርካ ዞን ጥቃት ከመፈጸሙ ቀናት አስቀድሞ አጎራባች በሆነው መርቲ ዞን ተጨማሪ 16 ሰዎች መገደላቸውንም አስታውቃለች።