ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይጄሪያ ራስን የማጥፋት ሙከራን በእስር ከሚያስቀጡ ወንጀሎች ውስጥ ልታስወጣ ነው
የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ቦላ ቲኑቡ ራስን የማጥፋት ሙከራ ከወንጀል ድርጊቶች ውስጥ እንዲወጣ ምክር ቤቱን ጠየቁ።
ፕሬዚደንቱ ራስን ከማጥፋት ሙከራ የተረፉ ግለሰቦች በቅጣት ፋንታ የሕክምና ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ሃሳብ አቅርበዋል።
ቲኑቡ ያቀረቡት እቅድ ናይጄሪያ አሁን ተግባራዊ እያደረገች ያለችውን እና ራስን የማጥፋት ሙከራን እንደ ወንጀል የሚቆጥረውን ሕግ ከወንጀልነት ወደ ሕክምና እና ማገገሚያ ማዕከላት እንዲሸጋገር የሚያደርግ ነው።
የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችም ራስን የማጥፋት ሙከራ የወንጀል ቅጣት ሳይሆን ሕክምና ነው የሚያስፈልገው ሲሉ ለዓመታት ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
እአአ ግንቦት 2024 በፓርላማ በተካሄደው የሕዝብ ችሎት ላይ በወቅቱ የናይጄሪያ የሥነ-አዕምሮ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ታይዎ ኦቢንዶም ሕግ አውጪዎች ራሳቸውን ለመግደል በሚሞክሩ ሰዎች ላይ የሚጣሉ የወንጀል ቅጣቶችን እንዲያስወግዱ አሳስበዋል።
"የታመሙና የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ግለሰቦች ለምን እንቀጣለን?" ሲሉም ጠይቀዋል።
አሁን ተግባራዊ እየሆነ ባለው የናይጄሪያ ሕግ መሠረት ራስን የማጥፋት ሙከራ ወንጀል ሲሆን ድርጊቱን ፈፅመው የተገኙ የአንድ ዓመት እስር፣ የገንዘብ ቅጣት ወይም ሁለቱም ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
ራስን የማጥፋት ሙከራ በፈፀሙ ግለሰቦች የሚተላለፉ ቅጣቶችን በሕክምና ድጋፍ፣ በማገገሚያ እና ሌሎች ድጋፎች እንዲተኩ የሚጠይቅ ለሴኔቱ የቀረበ ሌላ ረቂቅ ሕግም ሁለተኛውን ግምገማ አልፏል ።
ይህን ረቂቅ ሕግ ያቀረቡት የምክር ቤት አባሉ አሱኮ ኤክፕንዮንግ ከራስን ከማጥፋት የተረፉ ግለሰቦችን መቅጣት ራስን የማጥፋት ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦች እርዳታ እንዳይጠይቁ ያደርጋል ብለዋል።
የምክር ቤት አባሉ ጨምረውም ቤተሰቦች ቅጣትን እና ማኅበራዊ መገለልን በመፍራት እንዲህ ዓይነት ክስተቶችን ሊደብቁ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
"ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ ሰዎችም ቅጣቱን በመፍራት ከድርጊታቸው ላይቆጠቡ እና እስከ ሕይወታቸው ህቅታ ሊገፉበት ይችላሉ" ብለዋል።
የረቂቅ ሕጉ ዓላማ ራስን ማጥፋትን ማበረታታት ወይም ሕጋዊ ማድረግ እንዳልሆነ፤ ይልቁኑ ሕይወታቸው የተረፉትን መጠበቅ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው አስረድተዋል።
የፕሬዚደንቱ እቅድም ቀደም ብሎ ራስን ከማጥፋት ሙከራ የተረፉ ሰዎች ወደ እስር ቤት መላክ አለባቸው ሲሉ በነበሩት የምክርቤቱ ፕሬዚደንት ጋድስዊል አክፓባዮም ተቀባይነት አግኝቷል።
አክፓባዮ ከዚህ ቀደም "አሁን ላይ ራስን ማጥፋት ወንጀል ነው። ስለዚህ ከሞከራችሁ ቀጥሉበት። ካልሆነ ወደ እስር ቤት እንልካችኋዋለን" ብለው ነበር።
ሆኖም የፕሬዚደንቱን እቅድ ከተቀበሉ በኋላ የከዚህ ቀደሙን ንግግራቸውን "የአዕምሮ ጤና ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ ተግባራዊ አይሆንም" ግልጽ ለማድረግ ሞክረዋል።
ጨምረውም በአዕምሮ ጤና ችግር ምክንያት ተገፋፍተው ድርጊቱን የሚፈፅሙትን መቅጣት ተገቢ አይሆንም ብለዋል።
አክፓባዮ የተሻሻለውን የፕሬዚደንቱን ረቂቅ ሕግ ለተጨማሪ ግምገማ ለምክር ቤቱ ኮሚቴ መርተዋል።
ናይጄሪያ ራስን የማጥፋት ሙከራ ወንጀል ካደረጉ በርካታ አፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ናት።
ጋና ከሦስት ዓመት በፊት ራስን የማጥፋት ሙከራን ወንጀል የሚያደርገውን ሕግ ያስወጣች ሲሆን የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ባለፈው ዓመት ድርጊቱን ወንጀል የሚያደርገው ሕግ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ብሏል።