የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በአርሲ ሽርካ ወረዳ "እርምጃ" መውሰዱን አምኖ፣ የተገደሉት "የትርፍ ጊዜ ተዋጊዎች" ናቸው አለ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ዞን ከ40 በላይ ሰዎች በተገደሉበት የጥቅምት ወር ጥቃት ወቅት "እርምጃ" መውሰዱን አረጋገጠ።

ይሁንና፣ በታጣቂው ቡድኑ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት ሲቪሎች ሳይሆኑ በጸጥታ አካላት "የተመለመሉ" እና "መደበኛ ነዋሪ የሆኑ የትርፍ ጊዜ ተዋጊዎች" ናቸው ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ይህንን ያለው በጥቅምት አጋማሽ በቀድሞው አርሲ ዞን ውስጥ በሚገኘው ሽርካ ወረዳ ቦርቢና ጮሌ ቀበሌ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ትናንት ሰኞ ኅዳር 7 ቀን 2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።

በዕለቱ በተፈጸመው ጥቃት "46 ሰዎች" እንደተገደሉ ነዋሪዎች በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከተገደሉት ውስጥ "ቢያንስ አምስቱ ሕጻናት" እንደሆኑም ገልጸዋል። አንድ ነዋሪ "የአምስት፣ ሰባት እና አሥር ዓመት" ሕጻናት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች በበኩሉ በተመሳሳይ ዕለት "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" እና "ኢመደበኛ ታጣቂዎች" በስፍራው በፈጸሟቸው ጥቃቶች 48 ሰዎች መገደላቸውን ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኢሰመኮ መግለጫ እንደሚያስረዳው 41 ያህል ሰዎች የተገደሉት በኦነሠ ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት ነው። ኢሰመኮ "[ታጣቂ ቡድኑ] በፈጸመው ጥቃት 23 በቀበሌ ደረጃ የተደራጁ ጸጥታ አካላት፣ 5 የሚሊሻ አባላት እንዲሁም 13 ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለማረጋገጥ ተችሏል" ብሎ ነበር።

ቀጥሎ ደግሞ "በአካባቢው በታጠቁ ኢመደበኛ በሆኑ ታጣቂ ግለሰቦች" ባደረሱት ጥቃት ሌሎች ሰባት ሰዎች መገደላቸውን በመግለጫው አስፍሯል።

በዕለቱ 46 ሰዎች መገደላቸውን የምትገልጸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ፣ ጥቃቱ ምዕመኖቿ ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ በመግለፅ ከስሳለች።

በሽርካ ወረዳ የተፈጸሙትን ጥቃቶች "በጥንቃቄ እየመረመረ ሳምንታትን" ማሳለፉን በትናንቱ መግለጫው የጠቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ፣ ስለ ክስተቱ የራሱን ገለጻ አስቀምጧል።

እንደ ኦነሠ መግለጫ፣ በስፍራው ከታጣቂ ቡድኑ በተጨማሪ፣ "የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የፀረ ሽምቅ ኃይሎች፣ የክልል ሚሊሻ እና የታጠቁ የአማራ ተወላጅ ሲቪሎች" ይገኛሉ።

"የታጠቁ የአማራ ተወላጅ ሲቪሎች" በሚል የተገለጹት አካላት፣ "መደበኛ የሲቪል ሕይወት የሚመሩ ቢሆንም፣ በሥርዓቱ ኃይሎች ሲጠሩ ወይም ሲታለሉ መሣሪያ የሚያነሱ" ናቸው ብሏል።

የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ክስተት የተጀመረውም እነዚህ የታጠቁ ነዋሪዎች ከጥቃቱ አንድ ሳምንት በፊት ጥቅምት 8 ቀን "ከገበያ ስትመለስ የነበረች አንዲት ኦሮሞ እናትን በጥይት መትተው" ከገደሉ በኋላ መሆኑን በመግለጽ ወንጅሏል።

ይህንንም ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተዋጊዎች በሽርካ ወረዳ ግለሰቦቹ የሚገኙበት አካባቢ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልጿል።

"የኦነሠ ተዋጊዎች፣ እነዚህ የታጠቁ ሲቪሎች በመደበኛው የሥርዓቱ ኃይሎች ትዕዛዝ እንደሚንቀሳቀሱ ስለሚያውቁ በሽርካ ወረዳ፣ ቢርቦፍ ጮሌ የሚገኘው ሰፈራቸው ላይ እርምጃ ወስደዋል" ሲሉ በመግለጫው አስፍሯል።

ታጣቂ ቡድኑ አክሎም፣ "በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በተኩስ ልውውጡ ከመደበኛ ተዋጊዎች በተጨማሪ የሲቪሎች ሞት ተከስቷል" ብሏል። ይሁን እንጂ የተገደሉት ሰዎች "የትርፍ ጊዜ ተዋጊዎች" እንጂ "በተባባሪ ጥይት የተገኙ ሲቪሎች አልነበሩም" ሲል በመግለጫው አስፍሯል።

"የወደቁት ሲቪሎች በመከላከያ ሠራዊት እና በፀረ ሽምቅ ኃይሎች ከግል ሕይወታቸው ተመልምለው የወጡ የትርፍ ጊዜ ተዋጊዎች ነበሩ" በማለት አክሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መግለጫ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ አልጠቀሰም።

ኦነሠ በትናንት መግለጫው፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የአርሲውን ጥቃት በተመለከተ ያወጣውን ሪፖርት አጣጥሏል።

ብሔራዊውን የሰብአዊ መብቶች ተቋም "የአገዛዙ ቅጥያ" በማለት የገለጸው ታጣቂ ቡድኑ፣ ኢሰመኮ ስለ ሽርካ ወረዳው ጥቃት ያወጣው ሪፖርት "እንደ ገለልተኛ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሥራ" መታየት እንደሌለበት በመግለጽ ተከራክሯል።

"የአርሲው ክስተት ተነጥሎ የሚታይ አጋጣሚ" እንዳልሆነ በመግለጽም፣ መንግሥት "በአገዛዙ ላይ የጋራ ግንባር እንዳይፈጠር ለመከላከል የብሔር እና የሃይማኖት ስንጥቃቶችን በመሣሪያነት እየተጠቀመ ነው" ሲል ከስሷል።

በአንድ ሳምንት ልዩነት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመው እና ከ40 በላይ ሰዎች የተገደሉበት የሽርካ ወረዳ ጥቃት መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ጥቃቱን በመኮንን መግለጫ አውጥቷል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ጭምር ባለፉት ሳምንታት ስለ ጥቃቱ የተለያዩ አካላትን ሲያነጋግሩ ነበር። አምባሳደሩ ስለ አርሲው ክስተት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሲያን እና ኢሰመኮ አመራሮች ጋር መነጋገራቸው ተገልጿል።

ጥቃቱ በደረሰበት ሳምንት አጎራባች በሆነው መርቲ ወረዳም 16 ሰዎች መገደላቸው የጠቀሰችው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ፣ በቀናት ልዩነት የተገደሉት ምዕመኖቿ ብዛት 60 እንደሆነ አስታውቃለች።

ከዚህ ክስተት ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ደግሞ የቀድሞው አርሲ ዞን ሌላኛው ወረዳ በሆነው ሮቤ ውስጥ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት የ38 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል 10 ሰዎች ሲቪሎች ሲሆኑ የተቀሩት የእንደቶ ከተማ ሚሊሻዎች እና የፖሊስ አባላት መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል በሽርካም ሆነ በሮቤ ወረዳ ለተፈጸሙት ጥቃቶች ተጠያቂ ያደረገው ፌደራል መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀውን እና "ሸኔ" ሲል የሚጠራውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው።

የክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ስለ ሽርካው ጥቃት በሰጡት መግለጫ ከኦነሠ በተጨማሪ "የፋኖ" አባላትም በአካባቢው እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸው ነበር።

በአዲሱ የኦሮሚያ ክልል አወቃቀር በምሥራቅ ዞን ሥር የተካተተው የቀድሞ አርሲ ዞን ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስተናግዷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም. ባወጣው የምርመራ ሪፖርት በአርሲ ዞን ውስጥ በአራት ዓመታት በተፈጸሙ ጥቃቶች "458 ሰዎች" ሲገደሉ፤ "38 ነዋሪዎች ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም" ብሎ ነበር።