በዓለም በከፍተኛ ደረጃ በፖሊስ ከሚፈለጉ የወንጀል ቡድን መሪዎች አንዱ በዱባይ ተያዘ

ዳንዔል ኪናሀን

የፎቶው ባለመብት, Solarpix

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በመላው ዓለም በከፍተኛ ደረጃ በፀጥታ ኃይሎች ከሚፈለጉ ሰዎች አንዱ የሆነው እና የወንጀል ቡድንን በመምራት የተጠረጠረው ግለሰብ በዱባይ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ዳንዔል ኪናሀን የተባለው ተጠርጣሪ ከዱባይ ለአየርላንድ ተላልፎ ተሰጥቶ በደብሊን ፍርድ ቤት ቀርቧል።

በአውሮፓውያኑ ከጥቅምት 2015 እስከ ግንቦች 2017 ባሉት ዓመታት ለወንጀል ቡድን ትዕዛዝ በመስጠት ክስ ተመሥርቶበታል።

የአየርላንድ መንግሥት ጄት የ49 ዓመቱን ተጠርጣሪ ደብሊን አድርሶ በቁጥጥር ሥር አውሏል።

እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በፖሊስ ይዞታ ሥር ሆኖ ይቆያል ተብሏል።

በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በቁጥጥር ሥር የዋለው መጋቢት ላይ ሲሆን ባለፉት ወራት ለአየርላንድ ተላልፎ እንዳይሰጥ ይግባኝ ቢልም አልተሳካለትም።

ኪናሀን የወንጀል ቡድን ከፍተኛ መጠን ያለው አደንዛዥ ዕፅ እና የጦር መሣሪያ ከመላው ዓለም በማስገባት ተጠያቂ እንደሆነ የአየርላንድ ብሔራዊ የወንጀል ተቋም አስታውቋል።

ከወንጀል ቡድን ግድያዎች ጋር የተያያዘ እንደሆነም ተገልጿል።

የግል ጄት

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ከአየርላንድ በተጨማሪ የአሜሪካ ግምጃ ቤትም በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ይፈልጋል።

የሚመራው የወንጀል ቡድን በዓለም እጅግ የከፉ ከሚባሉት አንዱ እንደሆነም ተገልጿል።

የአሜሪካ መንግሥት በ2022 በግለሰቡ ላይ ማዕቀብ ጥሏል። ኪናሀን እና ቤተሰቦቹ በወንጀል ቡድኑ ውስጥ እጃቸው እንዳለበት ገልጿል።

በወንጀል ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት 18 ሰዎች ከመገደላቸው ጋር በተያያዘ በአየርላንድ ሲፈለግ ነበር።

የአየርላንድ መንግሥት አደገኛ የሚላቸው ሰዎችን የሚያጓጉዝበት ጥይት የማይበሳው መኪና ተዘጋጅቶ፣ በፀጥታ ኃይል ታጅቦ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ኮሚሽንር ጀስቲን ኬሊ እንዳሉት ግለሰቡ መታሰሩ "ድንበር ዘለል የወንጀል ቡድኖችን ዒላማ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኛነት" ያሳያል።

ዳንዔል ኪናሀን

የፎቶው ባለመብት, Mike O'Donnell

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኪናሀን ጥቁር ለብሶ በፍርድ ቤት ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ በጋዜጠኞች ተሞልቶ ነበር።

ዳኞቹ ፓትሪክ ማግራት፣ ሳራ በርክሊ እና ፊዩና ሊዶን ጉዳዩን ተመልክተዋል።

ኪናሀን ጠበቃ ለማቆም ጊዜ እንዳላገኘ አስታውቋል። በዋስ ለመውጣት መጠየቅ ይፈልግ እንደሆነ በዳኞች ሲጠየቅ።

"ዋስትና ብጠይቅ እንደማይሰጠኝ ሁላችንም እናውቃለን፤ ጊዜያችሁን ስለሰጣችሁኝ ግን አመሰግናለሁ" ሲል መልሷል።

የዩኤኢ እና አየርላንድ የፍትሕ ሚኒስትሮች የወንጀል ተጠርጣሪዎችን አሳልፈው የመስጠት ስምምነት በመጥቀስ ኪናሀን ስለመያዙ የሚዘረዝር የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

"በድንበር ተሻጋሪ የተቀናጀ ወንጀል እና የወንጀል ቡድንን በመምራት አየርላንድ በከፍተኛ ደረጃ ስትፈልገው ነበር" ይላል መግለጫው።

የአየርላንድ የፍትሕ ሚኒስትር ጂም ኦካለግሀን "በሁለቱ አገራት መካከል ትልቅ ትብብር የታየበት የፍትሕ ትስስር ነው" ብለዋል።

የዩኤኢ የፍትሕ ሚኒስትር አብዱላህ ቢን ሱልታን ቢል አዋድ አል ኑያሚ "ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን ለመከላከል የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት ለመደደገፍ ቁርጠኛ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።

የኪናሀን የወንጀል ቡድን ወደ 1 ቢሊዮን ፓውንድ እንዳገኘ ይገመታል።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት የወንጀል ቡድኑን ከጣልያኑ 'ካሞራ'፣ ከሜክሲኮው 'ሎስ ዜታስ' እና ከጃፓኑ 'ያኩዛ' የወንጀል ቡድኖች ጋር አነጻጽሯል።

ኪናሀን ወይም አባቱ ክሪስቶፈር አልያም ወንድሙ ክሪስቶፈር ጁንየርን በተመለከተ ጥቆማ ለሚሰጥ ሰው አሜሪካ 5 ሚሊዮን ዶላር ቃል ገብታ ነበር።

በ2022 የቡድኑ የወንጀል ድርጊቶች መሪ ቶማስ ካቫንጋህ ኬሎች ተጠርጣሪዎች ጋር የ21 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

የአየርላንድ ብሔራዊ ወንጀል ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው፤ ወደ 23.4 ዩሮ የሚያወጣ ኮኬይን እና 6.4 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ካናቢስ በማዘዋወር ተጠያቂ ናቸው።

ኪናሀን በ2016 ከግድያ ሙከራ አምልጧል።

ከአየርላንድ ወጥቶ በስፔን እና ከዚያም በዱባይ ኖሯል።

ጠበቃው ከዚህ በፊት ለቢቢሲ ፓናሮማ ምንም የወንጀል ሪከርድ እንደሌለው እንዲሁም ክሶቹም ሐሰተኛ እና ማስረጃ አልባ እንደሆኡ ተናግረዋል።