በኮሎምቢያ በተከሰተ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ 132 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኮሎምቢያ ውስጥ በተከሰተ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ የ132 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ በርካታ ሕንጻዎች ፈረሱ።
በሕንጻዎች ፍርስራሽ ሥር ሰዎች ተቀብረዋል የሚል ስጋት በመኖሩ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተገልጿል።
ባለፉት ዓመታት ኮሎምቢያ ውስጥ ካጋጠመው ከባድ ተፈጥሯዊ ክስተቶች አንዱ የሆነው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 7.4 ሆኖ ተመዝግቧል።
በኮሎምቢያ ቾኮ ግዛት የታየው የመሬት መንቀጥቀጥ ከመሬት በ103 ኪሎሜትር በታች የተከሰተ እንደሆነ የአገሪቱ የጂኦሎጂካል አገልግሎት አስታውቋል።
ንዝረቱ በምዕራባዊ ኮሎምቢያ በመቶዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ አካባቢዎችም ተሰምቷል። ጎረቤት አገራት ቬንዙዌላ፣ ኢኳዶር እና ፓናማም ንዝረቱ ደርሶባቸዋል።
በርካታ ሞት የተመዘገበው የኮሎምቢያ ቡና አምራች ግዛት ውስጥ በምትገኘው ፔሬራ ከተማ ነው። በዙሪያዋ የሚገኙ ከተሞች እና ቫሌ ዴል ካውካ ግዛትም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ማዕከል ቾኮ ግዛት 'ሳን ሆሴ ዴል ፓልማር' የተባለ መንደር ውስጥ ነው። መንደሩ ውስጥ ግን "ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ" መንገዶች ላይ ከደረሰው ጉዳት ባሻገር የአንድም ሰው ሕይወት እንዳላለፈ እና የአካል ጉዳት እንዳልደረሰ ከንቲባው ሌዮን ፋቢኦ ማሪን ሞንካዳ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በመሬት መንቀጥቀጥ ከ480 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል። ከመሬት መንቀጥቀጥ መነሻ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፒሬራ ከተማ የከፋው ጉዳት ተመዝግቧል።
ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው አንድ ቪዲዮ፣ 'ፕላዛ ቦሊቫር' በተባለው የከተማው ዋና አደባባይ የሚገኝ አንድ ሕንፃ ሲደርመስ አሳይቷል። በርካታ ሰዎች ተሰብስበውበት የነበረ ስፍራ በፍርስራሽ እና አቧራ ሲሞላም ይታያል።
በከተማው 40 ሰዎች መሞታቸውን እና 65 ሕንፃዎች መፍረሳቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል። በ15ቱ ሕንፃዎች ፍርስራሽ ስር ሰዎች ተቀብረው ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል።
ከመሬት መንቀጥቀጡ መነሻ 200 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው ካሊ ከተማ ውስጥ ደግሞ 32 ሕንፃዎች ፈርሰዋል።
በቾኮ እና ቫሌ ዴል ካውካ ግዛቶች በሚገኙት ማኒዛሌስ፣ ኪብዶ እና ሜዴሊን ከተሞችም የሰዎች ሕይወት ማለፉ ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአገሪቱ የአቪዬሽን ባለስልጣን እንደገለጸው፣ በተለያዩ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ አየር መንገዶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ ዛፎች እና የትራፊክ መብራቶች በኃይለኛው ሲወዛወዙ ታይቷል። በመዲናዋ በአደጋው የተሰነጠቁ ሕንጻዎች ቢኖሩም መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ የሚባል ጉዳት አልደረሰም።
የአሁን የተፈጥሮ አደጋ ያጋጠመው በጎረቤት አገር ቬንዙዌላ የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ6,300 በላይ ሰዎችን ከገደለ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።
ኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት አቤላርዶ ደ ላ ኤስፕሪኤላ በጀት ማጽደቅን ጨምሮ፣ ለአደጋው በፍጥነት ምላሽ መስጠት የሚያስችላቸውን ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ይፋ አድርገዋል።
ባለፈው ሳምንት ሥልጣን የተረከቡት አዲሱ ፕሬዚዳንት፣ ገና ከጅማሬው ቆይታቸውን ሊወስን የሚችል ክስተት አጋጥሟቸዋል።















