ቬንዙዌላ በርዕደ መሬት ከተመታች ከቀናት በኋላ ሁለት ታዳጊዎችን ጨምሮ 33 ሰዎች ከፍርስራሽ ውስጥ በሕይወት ወጡ

የፎቶው ባለመብት, ungrd_oficial
ቬንዙዌላ በሁለት ከባድ ርዕደ መሬት ከተመታች ከቀናት በኋላ በተደረጉ የነፍስ አድን ጥረቶች ተአምራዊ ታሪኮች እየተሰሙ ነው።
ባሳለፍነው ቅደሜ እና እሁድ 33 ሰዎች ከፍርስራሽ ውስጥ በሕይወት መውጣታቸውን የአገሪቷ ጊዜያዊ ፕሬዚደንት ዴሊሲይ ሮድሪጉዝ ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል ሁለት የ11 ዓመት ታዳጊዎች ይገኙበታል። ታዳጊዎቹ እሁድ ዕለት በሰዓታት ልዩነት ውስጥ በተለያየ ቦታ ከፈረሱ ሕንጻዎች ውስጥ በሕይወት ወጥተዋል።
ሆኖም በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እስካሁን ደብዛቸው እንደጠፉ ሲሆን ሰዓታት በነጎዱ ቁጥር ሌሎች ሰዎችን በሕይወት የማግኘት ተስፋ እየተመናመነ ነው።
የእርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት አደጋው ከተከሰተ ከ48 እስከ 72 ሰዓታት ያሉት ጊዜያት ሰዎችን በሕይወት ለማግኘት ወሳኝ ናቸው።
ሆኖም ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች ቤተሰቦች የሚወዷቸውን ሰዎች የተመለከተ ዜና በመጠባበቅ አምስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል።
እስከ እሁድ ድረስ ቢያንስ 1 ሺህ 450 ሰዎች በአደጋው መሞታቸውን ጊዜያዊ ፕሬዚደንቷ ሮድሪጎዝ ተናግረዋል።
ሮድሪጎዝ እንዳሉት ርዕደ መሬቱ በአገሪቷ ታሪክ ያጋጠመ አስከፊው የተፈጥሮ አደጋ ነው።
ረቡዕ ዕለት በ39 ሴኮንዶች ውስጥ ያጋጠሙት እና በሬክተር ስኬል በ7.2 እና 7.5 የተለኩት ሁለት ተከታታይ ርዕደ መሬቶች 800 የሚጠጉ ሕንፃዎችን ያፈራረሱ ሲሆን በርካታ ሰዎች በፍርስራሹ ውስጥ እንዲቀሩ አድርጓል።
በጭንቀት የተዋጡ ቤተሰቦችም የሚወዷቸውን ሰዎች ለመፈለግ በእጃቸው ሳይቀር ፍርስራሾቹን እየቆፈሩ ነው።
አንዳንዶቹ ከፍርስራሽ ውስጥ የሰዎች ድምጽ እንደሚሰሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ሆኖም ከባባድ የሕንፃዎቹን ፍርስራሾች ማንሳት ስለማይችሉ ማሽኖችን እየተጠባበቁ ነው።
ምንም እንኳን ሰዎችን በሕይወት ለማግኘት ወሳኝ የሆነው 72 ሰዓታት ቢያልፍም የነፍስ አድን ሰራተኞች ከቀናት በኋላም ተስፋ አልቆረጡም። ሰዎች ምግብ እና ውሃ ካገኙ አሁንም በሕይወት ሊገኙ ይችላሉ ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት አስተባባሪ ጊያንሉካ ራምፖላ አሁንም ሰዎችን በሕይወት ማግኘት እንደሚቻል ገልጸው፤ ነገር ግን " ይህ የሚሆንበት ጊዜ እያጠረ ነ ው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጊዜያዊ ፕሬዚደንቷም ቅዳሜ እና እሁድ ከፍርስራሽ ውስጥ በሕይወት የወጡ ሰዎችን ቪዲዮ ጨምሮ ተስፋ ሰጪ የሆኑ መልዕክቶችን በማኅበራዊ ሚዲያ እያጋሩ ነው።
የነፍስ አድን ሰተራኞችም ሞይስስ የተባለ የ11 ዓመት ታዳጊ ከፍርስራሽ ውስጥ ሲወጣ የሚያሳይ ቪዲዮ አጋርተዋል።
የኮሎምቢያ ብሔራዊ የአደጋ አስተዳደር ክፍል እንዳለው ታዳጊው ሞይስስ ሦስት ሜትር ጥልቀት ባለው ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብሮ የነበረ ሲሆን የነፍስ አድን ሰራተኞች ታዳጊውን ለማውጣት ስድስት ሰዓታት ወስዶባቸዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ሰራተኞቹ ታዳጊው በሕይወት ከሌሉ እህቱ እና እናቱ አጠገብ ማግኘታቸውን በዎኪ ቶኪ ሲነጋገሩ ተሰምተዋል።
ከዚያም ከሰዓታት በኋላ ሮድሪጉዝ በካራባሌዳ ከተማ ሌላ የ11 ዓመት ታዳጊ በሕይወት ሲወጣ የሚያሳይ ቪዲዮ በኤክስ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
"በእነዚህ ሰዓታት እያንዳንዱ እስትንፋስ ለቬንዙዌላ ተስፋ ነው" ብለዋል።
በርዕደ መሬቱ ክፉኛ በተጎዳችው ካራባሌዳ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ ቡድን እሁድ እለት አባት እና ታዳጊ ልጁን መታዳግ እንደቻሉ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የነፍስ አድን ሥራው አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን አንዳንዶች የመንግሥት ምላሽ በቂ እና አፋጣኝ አይደለም ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በቅርብ ቀናት ከሜክሲኮ፣ ስፔን ፣ ኳታር፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የነፍስ አድኑን ጥረት ለማገዝ ወደ ሥፍራው ቡድን ልከዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር ቅዳሜ ዕለት ከዓለም የተውጣጡና እያንዳንዱ ከ50 እስከ 100 አባላት ያሉት 39 የፍለጋ እና ነፍስ አድን ሰራተኞች ቡድን መሰማራቱን ተናግረዋል።















