ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን "አንድም አጀንዳ ላይ ውሳኔ አልተሰጠም" ሲል የሚነሱ አስተያየቶችን አስተባበለ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian National Dialogue Commission
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ በምክክር ሂደቱ "እስካሁን ድረስ አንድም ውሳኔ በአንድም አጀንዳ ላይ አልተሰጠም" ሲሉ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተነስቷል ላሉት "አሉባልታ" ምላሽ ሰጡ።
የምክክሩ ተሳታፊዎች ጉባኤው ላይ የተገኙት "ከየአካባቢያቸው ይዘው የመጡትን ጥያቄ መልሰው ለመሄድ" እንዳልሆነ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ "ኢትዮጵያን ማዕከል" እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ኮሚሽኑ፣ በምክክር ሂደቱ ላይ የሚታዩ "ስሜቶች እንዲረጋጉ" ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከእምነት ተቋማት መሪዎች ጋር ንግግር ማድረጉንም አስታውቀዋል።
ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ይህንን ያሉት፣ አንድ ወር ሊደፍን የቀናት ዕድሜ የቀረው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 4/2018 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
የጉባኤው ተሳታፊዎች 500 አባላት ባሏቸው ስምንት ቡድኖች ተከፋፍለው በኮሚሽኑ የተመረጡት አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ነው።
500 አባላት ያሏቸው ቡድኖች ወደተለያዩ አነስተኛ ቡድኖች በመከፋፈል የተሰጣቸው አጀንዳ ላይ ሲመክሩ ቆይተዋል።
በተለያዩ ደረጃዎች ሲነሱ የነበሩ ሀሳቦች፣ 250 አባላት በሚይዙ ስልታዊ ቡድኖች ምክክር ከተደረገባቸው በኋላ ተመልሰው ወደ ዋናው ባለ 500 አባላት ቡድን እየቀረቡ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን በዛሬው መግለጫ ተናግረዋል።
ሦስት አጀንዳዎችን የያዙ ቡድኖች ዛሬ ሰኞ ምክረ ሀሳቦቻቸውን ይዘው ወደ ዋናው ቡድን መመለስ መቻላቸውን ጠቅሰዋል። "የሚቀሩት ሦስቱ ወይም አራቱ ደግሞ ነገ [ማክሰኞ] ጠዋት አምስት መቶ ላይ ይጀምራሉ" ብለዋል።
"ይህ ሂደት እንደምትገምቱት ቀላል አይደለም" ያሉት ኮሚሽነሩ፣ "ሁሉም አጀንዳዎች እኩል አለመሆናቸው" ቡድኖቹ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ላለመድረሳቸው አንድ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
"አጀንዳዎች ይለያያሉ። አገር ግንባታ እንደምታውቁት በጣም ሰፊ ነው። የተቋማት ግንባታ፣ የመንግሥት አወቃቀር እና የመሳሰሉት በጣም ሰፋፊ ናቸው" ብለዋል። ይህ ግን ሌሎች አጀንዳዎች "ትንንሾች ናቸው ማለት አይደለም" ሲሉም አብራርተዋል።
"እንደ አቀራረቡ፣ እንደ ሰዎቹ ዝግጅት እና እንደ ሰዎቹ ወደ መሃል የመምጣት ፍላጎት አካሄዶቹ ሊለያዩ ይችላሉ። ሁሉም አጀንዳዎች እኩል ባለመሆናቸው ነው ሦስቱ ዛሬ አምስት መቶ ላይ የደረሱት" ሲሉ የሂደት ልዩነት የተፈጠረበትን ምክንያት አንስተዋል።
500 አባላት ወዳሉበት ዋና ቡድን ካልተመለሱ አጀንዳዎች አንዱ የፌደራል ከተሞች በሆኑት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ላይ የሚደረገው ምከክር እንደሆነ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
250 አባላት ባሏቸው ስልታዊ ቡድኖች ላይ እየተወያዩ ያሉት የዚህ አጀንዳ ተመካካሪዎች፣ 500 ቡድኖች ወዳሉት ዋና ቡድን የሚቀርብ ምክረ ሀሳብን በተመለከተ ተቀምጦ በነበረው ቀን ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በተለይም አዲስ አበባ ከተማን በተመለከተ በምክክሩ ተነስተዋል የተባሉ ሀሳቦች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችም አነጋጋሪ ሆነው ሰንብተዋል። የተለያዩ ምልከታዎች የያዙት አካላት አቋሞቻቸውን ሲያንጸባርቁ ታይተዋል።
ዋና ኮሚሽነር መስፍንም በዛሬው መግለጫቸው በአጀንዳዎች ላይ የሚደረግ ምክክርን በተመለከተ ይሰማል ያሉትን "አሉባልታ" አንስተዋል።
"በዚህ ሃሳብ ላይ ሰሞኑን ድምጽ ብልጫ ይሰጥበታል፤ ስለዚህ በጋራ ተመካክረው ከደጅም ከውስጥም ያሉ ሎቢ ተደርገው በዚህ ውሳኔ ላይ እንዲህ ሊያደርጉ ነው" የሚል አስተያየት መነሳቱን ገልጸዋል። አክለውም "የሚባለው ነገር ከአሉባልታ ያለፈ አይደለም። ስለዚህ ይሄ ለሁላችንም ግልጽ ሊሆን ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።
በምክክር ጉባኤው መጨረሻ የሚደረሰው ምክረ ሀሳቦች እንጂ ውሳኔዎች ላይ እንዳልሆነ በአጽንኦት አንስተዋል። "በአሁኑ ሰዓት ውሳኔዎች እየወሰንን አይደለም። እስካሁን ድረስ አንድም ውሳኔ፣ በአንድም አጀንዳ ላይ አልተሰጠም። ምናልባትም ወደፊትም ውሳኔ አይሰጥም" ብለዋል።
"እዚህ የመጣነው ከየመንደራችን፣ ከየአካባቢያችን ይዘን የመጣነውን ጥያቄ እዚህ መልሰን ልንሄድ አይደለም። እዚህ የመጣነው አገራችንን ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገን መሆን አለበት፤ ይሄ በትክክል ሊሰመርበት ይገባል" ሲሉ ተመካካሪዎችን አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ፣ በምክክር ሂደቱ ለሚነሱ ቅሬታዎች ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ያነሱት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ከዚህም ባሻገር "ስሜቶች እንዲረጋጉ" የተለያዩ አካላትን ማነጋገሩን ገልጸዋል።
"እስካሁን ድረስ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በተናጠል አግኝቷል። ኮሚሽኑ የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎችንም ጭምር አግኝቷል። ምክንያቱም ያሉ ስሜቶች እንዲረጋጉ እና ወደፊት እንዲሄዱ ማድረግ እንዲቻል እነሱንም አግኝቶ አነጋግሯል" ብለዋል።
"አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ነገሮች አሉ፤ ግን እስካሁን በውጪ ይሰማል እንደሚባለው 'ይሄ ነገር አያስፈልገኝም' የሚል ነገር አላጋጠመንም" ሲሉም አክለዋል።
ሀገራዊ ምክር ኮሚሽን ላላፉት አራት ዓመታት በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ ሲያሰባስብ ቆይቶ አራት ሺህ ሰዎች በስምንት ዋነኛ አጀንዳዎች ላይ የሚደያርጉት የመጨረሻው ምክክር የተጀመረው ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም. ነው።















