ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በበርሊን የናዚን ምሽግ የማፍረስ ዕቅድ ለምን ተቃውሞ ገጠመው?
በማዕከላዊ በርሊን ከአንድ ምሽግ በስተቀር ከናዚ ዘመን የተረፈ ምንም ነገር አይገኝም።
የአዶልፍ ሂትለር የመጨረሻ ይዞታ የሆነ ምሽግን ለማፍረስ አውሮፕላኖች ተሰማርተዋል።
ይሄንን ከምድር በታች ምሽግ የሚገኝበትን አካባቢ አፍርሶ ሕንጻ የመገንባት ዕቅድ ተይዟል።
ዘ ኒው ሬይክ ቻንስለሪ (The New Reich Chancellery) የተባለው ሕንጻ የተገነባው ሂትለር በሚወደው አርክቴክት አልበርት ስፒር ነበር።
ሕንጻው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማገባደጃ ላይ በሶቪየት ኅብረት ኃይሎች ትዕዛዝ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።
ሕንጻው በአውሮፓውያኑ 1949 ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስበትም አሁን ሙሉ በሙሉ ለማፍረስ ታቅዷል።
ምሽግ የሆነው ሕንጻ ሙሉ በሙሉ ስላልፈረሰ የተወሰነው ክፍል እስከ ዛሬ ድረስ ይታያል።
የበርሊን የቤት ግንባታ ሴናተር ክርስቲያን ጌብለር እንደሚሉት ሕንጻው የሚፈርስበት ወቅት አሁን ነው።
"አንዳንዶች እንደ እምነት መዳረሻ የሚያደርጉት ምሽግ እንዳይፈርስ ብለን አዲስ ቤት እንዳይገነባ ማድረግ አንችልም" ሲሉ ቢዜድ ለተባለው ጋዜጣ ተናግረዋል።
ምሽጉ መፍረስ የለበትም ብለው የሚከራከሩ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
የበርሊን አንደርወርልድስ ማኅበር ኃላፊ ዲሜትር አርኖልድ ምሽጉን ማፍረስ "ፍጹም እብደት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
"የጥቃት ፈጻሚዎቹ ማዕከል ነው። የናዚ ጀርመን ዋነኛ ማዕከልም ነው። ከሂትለር ሕንጻዎች የቀረው ብቸኛው ማሳያ ነው" በማለትም አስረድተዋል።
ከሆሎካስት ሙዚየም ጋር በመሆን ሥፍራውን ወደ ሙዚየምነት እና መታሰቢያ ማዕከልነት መለወጥ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
የጦርነቱ ማክተም ማሳያ እንደሆነም ይገልጻሉ።
"በጀርመን ብዙ ታሪክ ጠፍቷል። የኮምኒስት ታሪክም የናዚ ታሪክም ወድሟል። በዚህ መንገድ መቀጠል የለብንም።"
ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ምሽጉ የሄዱት በአውሮፓውያኑ 2007 ሲሆን፤ ጥሩ ይዞታ ላይ እንደሚገኝ ታዝበዋል።
ሂትለር እና ሚስቱ ኢቫ ብሩዋን ራሳቸውን ያጠፉበት ፍዩረርበንከር ያህል ዝነኛ ቦታ አለመሆኑን ይናገራሉ።
ይህ ሥፍራ ከምሽጉ በ120 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ሕንጻው በአንድ ወቅት ሠራተኞች የነበሩት ሲሆን በጦርነቱ ማብቂያ አካባቢ በውስጡ ሆስፒታል ተዘጋጅቷል።
ዲሜትሪ እንደሚሉት 1,200 ስኩዌር ሜትር የሚሆነው የምሽጉ ክፍል አሁንም ባለበት ሁኔታ ይገኛል። ግድግዳው እና ጣሪያው 1.7 ሜትር ይደርሳል።
ምሽጉን ሳያፈርሱ ከላይ ሕንጻ መገንባት እንደሚቻል ይገልጻሉ።
ባለፈው ዓመት የበርሊን ቅርሶች ካውንስል ምሽጉ "ጉልህ ታሪካዊ ዋጋ" ያለው እንደሆነ በመግለጽ መፍረሱን እንደሚቃወም አስታውቋል።
"ዘ ኒው ሬይክ ቻንስለሪ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ዕቅድ የሚነደፍበት ማዕከል ነበር። የናዚ ሥርዓት መውደቅ ምልክትም ነው" ሲልም መግለጫ አውጥቷል።
ካውንስሉ "ታሪካዊ ዋጋ ያለው ሕንጻ እንደመሆኑ መጠበቅ አለበት፤ ከተማው ጥበቃ ሊያደርግላቸው ከሚገባው ሕንጻዎች ዝርዝር ውስጥም ሊካተት ይገባል" ሲልም አቋሙን ገልጿል።