በዕድሜ ከሮናልዶ እና ከሜሲ የሚበልጠው አፍሪካዊ የዓለም ዋንጫ ግብ አስቆጣሪ ማነው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ምናልባት ክርስቲያኖ ሮናልዶ በስድስት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ግቦችን አስቆጥሮ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እርሱም ሆነ 39ኛ ዓመቱን የደፈነው ሊዮኔል ሜሲ ያልደረሱበት አንድ ታሪካዊ ክብረ ወሰን አለ።

ፖርቹጋል ከኡዝፔክስታን ጋር ባደረገችው ሁለተኛ የምድብ ጨዋታዋ ላይ ሮናልዶ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው በ41 ዓመት ከ138 ቀናት ዕድሜው ነው። ይህቺ ግብ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ሁለተኛው በዕድሜ ትልቁ ግብ አስቆጣሪ አድርጋዋለች።

ይህም ቢሆን ግን የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ እና የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ክብረ ወሰኑን ካሜሮናዊውን ሮጀር ሚላን በመብለጥ መንጠቅ አልቻለም።

ሚላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የተሳተፈው ውድድሩ በአውሮፓውያኑ በ1982 ስፔን ውስጥ በተካሄደበት ጊዜ ነው።

ዓለም አቀፍ ዝና ያገኘው ግን ጣልያን ውስጥ በ1990 ጣልያን ውስጥ የዓለም ዋንጫ ሲካሄድ በ38 ዓመቱ አራት ግቦችን በማስቆጠር ካሜሮንን ወደ ሩብ ፍጻሜ ሲያደርስ ነው።

የሚላ ግቦች 'አይበገሬዎቹ አናብስቶች' ተብለው የሚታወቀው የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን አባላት ለመጀመሪያ ጊዜ አገራቸውን ለሩብ ፍጻሜ የደረሰች አፍሪካዊት አገር አደርገዋታል። ግብ ካስቆጠረ በኋላ የማዕዘን ባንዲራ አጠገብ ያሳየው ዳንስ ደግሞ መለያ ምልክቱ ሆኖለታል።

ከአራት ዓመት በኋላ በ1994 አሜሪካ ውስጥ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድርም የተሳተፈው ሚላ፤ ከ7.3 ሜትር ርቀት ላይ ኳስን ከመረብ በማገናኘት ሩሲያ ላይ ግብ አስቆጥሯል።

በዚህ ጊዜም መለያው የሆነችውን ውዝዋዜ ቢያሳይም፤ ካሜሮን 6 ለ 1 በመሸነፍ ከምድብ ከመውረድ አልተረፈችም።

አርጀንቲናው አጥቂ ሜሲ አገሩ ኦስትሪያን ባሸነፉበት ጨዋታ ግብ ያስቆጠረው በ38 ዓመት ከ363 ቀናት ዕድሜው ነበር።

በማግሥቱ ፖርቹጋል እና ኡዝቤኪስታን ባደረጉት ጨዋታ ላይ ግን ሮናልዶ ከመረብ ያሳረፋት ግብ፤ በዕድሜ ትልቁ ግብ አስቆጣሪ ሰንጠረዥ ላይ በሦስተኛነት ተቀምጦ የነበረውን ሜሲን ወደ አራተኛነት ዝቅ አድርጋዋለች።

ከዚህም ባሻገር ግን በ40ኛ ዓመታቸው ላይ የሚገኙት የቦስኒያ ሄርዜጎቪናው አጥቂ ኤዲን ዜኮ ወይም የክሮሺያው ሉካ ሞድሪች ግብ የሚያስቆጥሩ ከሆነ ሜሲን ይበልጥ ወደታችኛው የሰንዠረዡ ደረጃ ያወርዱታል።

ከአርጀንቲናዊው ገናና ተጫዋች በዕድሜ ዘጠኝ ወራትን የሚበልጠው የጃፓኑ መካከለኛ ተከላካይ ዩቶ ናጋሞቶም ሌላኛው ግብ አስቆጣሪ ሊሆን ይችላል።

አንጋፋ ግብ ጠባቂዎችን ባልተጠበቀ ሁኔታ ግብ አስቆጣሪ ሆነው እናያቸው ይሆን? የጀርመኑን ማኑኤል ኖየር፣ የኬፕ ቨርዴው ቮዚኛ እና የኡራጓዩ ፈርናንዶ ሙስሌራን ጨምሮ በዕድሜ ከሜሲ የሚበልጡ ስድስት ግብ ጠባቂዎች አሉ።

ይሁን እንጂ ከአውሮፓውያኑ 1930 ጀምሮ በተካሄዱት 22 የዓለም ዋንጫዎች ውስጥ አንድም ግብ ጠባቂ ኳስ ከመረብ አገናኝቶ አያውቅም።

የ37 ዓመቱ ኦስትሪያዊው ተጫዋች ማርኮ አርናውቶቪች አገሩ ጆርዳንን ባሸነፈችበት ጨዋታ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ግብ በማስቆጠር በሰንጠረዡ ከሚገኙት ቀዳሚዎቹ 10 ተጫዋቾች አንዱ ሆኗል።

ሮናልዶ ወይም ሜሲ በ2030 ፖርቹጋል እና አርጀንቲና በጋራ በሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ላይ እስካልተሳተፉ ድረስ ካሜሮናዊው ሚላ ክብረ ወሰኑን ይዞ የሚቀጥል ይመስላል።

መቼም፤ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአገሩ መሬት ላይ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር የመሳተፍ ፍላጎት አይኖረውም ብለው አይደመድሙም አይደል?

በዓለም ዋንጫ ታሪክ በዕድሜ አንጋፋዎቹ 10 ግብ አስቆጣሪዎች እነማን ናቸው?

  • ሮጀር ሚላ - ካሜሩን ከ ሩሲያ (ሰኔ 28/1994) - 42 ዓመት ከ39 ቀናት
  • ክርስቲያኖ ሮናልዶ - ፖርቱጋል ከ ኡዝቤኪስታን (ሰኔ 23/2026) - 41 ዓመት ከ138 ቀናት
  • ፔፔ - ፖርቱጋል ከ ስዊዘርላንድ (ታኅሣሥ 6/2022) - 39 ዓመት ከ283 ቀናት
  • ሊዮኔል ሜሲ - አርጀንቲና ከ ኦስትሪያ (ሰኔ 22/2026) - 38 ዓመት ከ363 ቀናት
  • ጉናር ግሬን - ስዊድን ከ ጀርመን (ሰኔ 24/1958) - 37 ዓመት ከ236 ቀናት
  • ኩዋውቴሞክ ብላንኮ - ሜክሲኮ ከ ፈረንሳይ (ሰኔ 17/2010) - 37 ዓመት ከ151 ቀናት
  • ፌሊፔ ባሎይ - ፓናማ ከ እንግሊዝ (ሰኔ 24/2018) - 37 ዓመት ከ120 ቀናት
  • ማርኮ አርናውቶቪች - ኦስትሪያ ከ ዮርዳኖስ (ሰኔ 17/2026) - 37 ዓመት ከ58 ቀናት
  • ኦብዱሊዮ ቫሬላ - ኡራጓይ ከ እንግሊዝ (ሰኔ 26/1954) - 36 ዓመት ከ279 ቀናት
  • ማርቲን ፓሌርሞ - አርጀንቲና ከ ግሪክ (ሰኔ 22/2010) - 36 ዓመት ከ227 ቀናት