ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የሕፃናት ፓውደር ምርቱ "ካንሰር ያመጣል" በሚል ለቀረበበት ክስ 5.5 ቢሊዮን ዶላር ሊከፍል ነው
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ከምርቶቹ መካከል አንዱ የሆነው የሕፃናት ፓውደር እንዲሁም ሌሎች በ'ታልክ' የሚሰሩ ምርቶቹ የኦቫሪ ካንሰር አስከትለዋል በሚል በሰሜን አሜሪካ ለቀረቡበት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ክሶች 5.5 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመክፈል ማቀዱን አስታወቀ።
በእቅድ ደረጃ የቀረበው ይህ ታሪካዊ ስምምነት ኩባንያውን ለረዥም ጊዜ ሲያስጨንቁ የቆዩትን የሕግ ክርክሮች ለመዝጋት ያለመ ነው።
የሚከፈለው ገንዘብ ምርቶቹ የጤና ችግር አስከትሎብናል የሚሉ ሰዎችን ለመደገፍ ይውላል ተብሏል።
ተቀማጭነቱን በኒው ጀርሲ ባደረገው ግዙፍ የውበትና ጤና መጠበቂያ ምርቶች አምራች ላይ የቀረቡት ክሶች ባለፉት ዓመታት ኩባንያው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል።
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ 'ታልክ' የተጨመረባቸው ምርቶቹ ካንሰር ያመጣሉ እንዲሁም በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው የሕፃናት ፓውደር የሚቀምምበትን ቀመር ለውጧል መባሉን አስተባብሏል።
ታልክ ከማግኒዥየም፣ ሲልከን፣ ኦክስጅን እና ሃይድሮጅን የተሰራ ተፈጥሯዊ ሚኒራል ሲሆን ብዙ ጊዜ የሕፃናት ፓውደር ለመስራት ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላል።
የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ታልክ የተጨመረበት ምርት 'አስቤስቶስ' ከተባለው ማዕድን ጋር ባለው ንክኪ ሳቢያ ለካንሰር እንደዳረጋቸው በገለጹ ተጎጂዎች ክስ ቀርቦበታል።
ታልክ ከመሬት ውስጥ የሚወጣ ሲሆን የሚገኘውም አስቤስቶስ በሚባለው እና ካንሰር በማስከተል ከሚታወቀው ቁስ አጠገብ ነው።
የተቋሙ ምክትል ፕሬዚደንት ኤሪክ ሃስ ክሶቹ "እውቀት ላይ ያልተመሠረቱ" መሆናቸውን ገልጸው፣ ኩባንያው ግን ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።
ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ያቀረበው ገንዘብ 69 ሺህ ኬዞችን የሚሸፍን እንደሆነ ገልጿል። ከታልክ ጋር የተያያዙ ክሶችም የክፍያው አካል ናቸው።
በዚህም መሠረት ተቋሙ በሚቀጥለው ዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ የሚያቀርብ ሲሆን ከ2028 ወዲህ ግን ሌላ ተጨማሪ ክፍያ አይጠየቅም።
ሆኖም ዕቅዱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በፌደራል እና የግዛት ፍርድ ቤቶች ከኦቫሪያን ካንሰር ጋር የተያያዘ ክስ ያቀረቡ 95 በመቶ ከሳሾችን በወከሉ የሕግ ተቋማት ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል ብሏል።
ሃስ በመግለጫቸው ድርጅቱ ለመክፈል ያቀደው ገንዘብ የቀረቡበትን ሕጋዊ ጥያቄዎች ይቋጫል ብሎ እንደሚተማመን ገልጸዋል።
ጨምረውም የቀረበው የመፍትሔ ሃሳብ ድርጅቱ ጉዳዩን ወደ ኋላ ትቶ ሕይወት አድን የሆኑ መድኃኒቶችን እና የሕክምና መሣሪያዎችን የማምረት ተልዕኮዎቹ ላይ ማተኮር እንደሚያስችለው ገልጸዋል።
በጤና ንግድ ላይ የተሰማራው የቀድሞው የድርጅቱ ደንበኛ 'ኬንቪው' የተባለ ኩባንያ፣ ጆንሰን የሚያመርተው የሕፃናት ፓውደር ከሰሜን አሜሪካ ውጭ እንዳይሸጥ አግዷል።
ባንድ ኤድ፣ ሊስተሪን እና ካልፖልን ጨምሮ ታዋቂ ምርቶች የያዘው ኬንቪው እአአ በ2022 ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጦ ነበር።
ታልክ የተባለው ሚኒራል ካለው የሕፃናት ፓውደር ጋር በተያያዘ በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ላይ ክስ መቅረብ የጀመረው በ2009 መጀመሪያ ላይ ነበር።
ሐምሌ ወር ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ያቀረቡት ግለሰቦች ታልክ ከኦቫሪ ካንሰር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ማሳየት አልቻሉም በሚል ለድርጅቱ ወስኖለት ነበር።
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በተደጋጋሚ የቀረቡበትን ክሶች ውድቅ አድርጓል።
አሁን ላይ ባወጣው መግለጫም ታልክ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስቤስቶስ እንዳልያዘ እንዲሁም ካንሰር እንደማያስከትል ገልጿል።
እአአ በ2022 ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በታልክ የተሰሩ የሕፃናትፓውደሮችን መሥራት እና በዓለም ላይ መሸጥ እንደሚያቆም ገልጾ ነበር።
ይህን ያለው ምርቶቹን በአሜሪካ ውስጥ ሸጦ ካጠናቀቀ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው።
" በዓለም ላይ በተደረገ ግምገማ ፣ በኮርንስታርች ወደሚሰሩ የሕፃናት ፓውደር ለመሸጋገር የንግድ ውሳኔ አሳልፈናል" ብሎ ነበር በወቅቱ።