ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ የሚፈጸመውን ድብደባ እንዲቆም ያደረጉት ለዲፕሎማሲ ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት መሆኑን
በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር አስታወቁ።
አምባሳደር ማይክ ዋልዝ እሁድ ዕለት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ፕሬዚዳንቱ “ለንግግር የተወሰነ ቦታ ለመስጠት”
ጥቃተ እንዲቆም ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የኢራን ጦር ቃል አቀባይ እሁድ ዕለት ቴህራን በቀጣናው ላይ የምትፈጽመውን “የአጸፋ” ጥቃቶች ማቆሟን ተናግረዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን መካከል በሰኔ ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ከፈረሰ በኋላ የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ
ሳምንቶች በየዕለቱ ኢራን ላይ ድብደባ ሲፈጽም ቆይቷል።
ቴህራንም በምላሹ በጎረቤት አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ ሚሳዔሎችን ስታስወነጭፍ ቆይታለች።
አምባሳደሩ ትራምፕ ጥቃቱ እንዲቆም ያደረጉት ለአጭር ጊዜ ስለመሆኑ kኤንቢሲ ተጠይቀው ሲመልሱ “ለአሁኑ እዚያ ድረስ ሄጄ
መመለስ አልፈልግም። ፕሬዚዳንቱ ሁሉንም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠዋል” ብለዋል።
ኒውዮርክ ታይምስ የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ጥቃቶች እየሰፉ የሚመጡ ከሆነ የአየር መከላከያ ጦር መሣሪያዎች እየሳሱ
ይመጣሉ ማለታቸውን መዘገቡን በተመለከተ ዋልዝ ሲጠየቁ አጣጥለውታል።
“የአሜሪካ ጦር . . . ዘመቻውን በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስፈልጉት ሁሉም ነገሮች አሉት” ብለዋል።
እስከ እሁድ ምሽት ድረስ ትራምፕ ጥቃቱ ስለመቆሙ በይፋ ያሉት ነገር የለም።
ነገር ግን ቀደም ሲል በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች የኢራንን መርከቦች እና የኻርግ ደሴቶችን
ሲደበድቡ የሚያሳይ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተሰራ ምስል አጋርተው ነበር።