ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የሕፃናት ፓውደር ምርቱ "ካንሰር ያመጣል" በሚል ለቀረበበት ክስ 5.5 ቢሊዮን ዶላር ሊከፍል ነው

የሕፃናት ፓውደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ከምርቶቹ መካከል አንዱ የሆነው የሕፃናት ፓውደር እንዲሁም ሌሎች በ'ታልክ' የሚሰሩ ምርቶቹ የኦቫሪ ካንሰር አስከትለዋል በሚል በሰሜን አሜሪካ ለቀረቡበት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ክሶች 5.5 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመክፈል ማቀዱን አስታወቀ።

በእቅድ ደረጃ የቀረበው ይህ ታሪካዊ ስምምነት ኩባንያውን ለረዥም ጊዜ ሲያስጨንቁ የቆዩትን የሕግ ክርክሮች ለመዝጋት ያለመ ነው።

የሚከፈለው ገንዘብ ምርቶቹ የጤና ችግር አስከትሎብናል የሚሉ ሰዎችን ለመደገፍ ይውላል ተብሏል።

ተቀማጭነቱን በኒው ጀርሲ ባደረገው ግዙፍ የውበትና ጤና መጠበቂያ ምርቶች አምራች ላይ የቀረቡት ክሶች ባለፉት ዓመታት ኩባንያው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል።

ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ 'ታልክ' የተጨመረባቸው ምርቶቹ ካንሰር ያመጣሉ እንዲሁም በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው የሕፃናት ፓውደር የሚቀምምበትን ቀመር ለውጧል መባሉን አስተባብሏል።

ታልክ ከማግኒዥየም፣ ሲልከን፣ ኦክስጅን እና ሃይድሮጅን የተሰራ ተፈጥሯዊ ማዕድን ሲሆን ብዙ ጊዜ የሕፃናት ፓውደር ለመስራት ጥቅም ላይ ይውላል።

ማዕድኑ 'አስቤስቶስ' ከተባለው ማዕድን ጋር ባለው ንክኪ ሳቢያ ለካንሰር ተዳርገናል በሚል ነበር ተጎጂዎች በኩባንያው ላይ ላይ ክስ ያቀረቡት።

ታልክ ከመሬት ውስጥ የሚወጣ ሲሆን የሚገኘውም አስቤስቶስ በሚባለው እና ካንሰር በማስከተል ከሚታወቀው መርዛማ ማዕድን አጠገብ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተቋሙ ምክትል ፕሬዚደንት ኤሪክ ሃስ ክሶቹ "በእውቀት ላይ ያልተመሠረቱ" መሆናቸውን ገልጸው፣ ኩባንያው ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ያቀረበው ገንዘብ 69 ሺህ ኬዞችን የሚሸፍን እንደሆነ ገልጿል። ከታልክ ጋር የተያያዙ ክሶችም የክፍያው አካል ናቸው።

በዚህም መሠረት ተቋሙ በሚቀጥለው ዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ የሚያቀርብ ሲሆን ከ2028 ወዲህ ግን ሌላ ተጨማሪ ክፍያ አይጠየቅም።

ሆኖም ዕቅዱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በፌደራል እና የግዛት ፍርድ ቤቶች ከኦቫሪ ካንሰር ጋር የተያያዘ ክስ ያቀረቡ 95 በመቶ ከሳሾችን በወከሉ የሕግ ተቋማት ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል ብሏል።

ሃስ በመግለጫቸው ድርጅቱ ለመክፈል ያቀደው ገንዘብ የቀረቡበትን ሕጋዊ ጥያቄዎች ይቋጫል ብሎ እንደሚተማመን ገልጸዋል።

ጨምረውም የቀረበው የመፍትሔ ሃሳብ ድርጅቱ ጉዳዩን ወደ ኋላ ትቶ ሕይወት አድን የሆኑ መድኃኒቶችን እና የሕክምና መሣሪያዎችን የማምረት ተልዕኮዎቹ ላይ ማተኮር እንደሚያስችለው ገልጸዋል።

በደንበኞች ጤና ንግድ ላይ የተሰማራው የቀድሞው የድርጅቱ አካል 'ኬንቪው' የተባለ ኩባንያ፣ ጆንሰን የሚያመርተውን የሕፃናት ፓውደር ከሰሜን አሜሪካ ውጭ መሸጥ አቁሟል።

ባንድ ኤድ፣ ሊስተሪን እና ካልፖልን ጨምሮ ታዋቂ ምርቶች ባለቤት የሆነው ኬንቪው እአአ በ2022 ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ጋር መለያየቱን አስታውቋል።

በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ላይ ታልክ የተባለው ማዕድን ካለው የሕፃናት ፓውደር ጋር በተያያዘ ክስ መቅረብ የጀመረው በ2009 መጀመሪያ ላይ ነበር።

ሐምሌ ወር ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ክስ ያቀረቡት ግለሰቦች ታልክ ከኦቫሪ ካንሰር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ማሳየት አልቻሉም በሚል ለድርጅቱ ወስኖለት ነበር።

ጆንሰን ኤንድ ጆንሰንም በተደጋጋሚ የቀረቡበትን ክሶች ውድቅ አድርጓል።

አሁን ላይ ባወጣው መግለጫም ታልክ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስቤስቶስ እንዳልያዘ እንዲሁም ካንሰር እንደማያስከትል ገልጿል።

ሆኖም እአአ በ2022 ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በታልክ የተሰሩ የሕፃናትፓውደሮችን ማምረት እና በዓለም ላይ መሸጥ እንደሚያቆም ገልጾ ነበር።

ይህን ያለው ምርቶቹን በአሜሪካ ውስጥ ሸጦ ካጠናቀቀ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው።

" በዓለም ላይ በተደረገ ግምገማ ፣ በኮርንስታርች ወደሚሰሩ የሕፃናት ፓውደር ለመሸጋገር የንግድ ውሳኔ አሳልፈናል" ብሎ ነበር በወቅቱ።