ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የባሕር ወንበዴዎች በሶማሊያ ባሕር ዳርቻ ሌላ መርከብ አገቱ
የባሕር ላይ ውንብድና እንደሆነ በተጠረጠረ ድርጊት በቀናት ልዩነት ሌላ መርከብ መያዙን ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም ማሪታይም ባለሥልጣናት በሶማሊያ ባሕር ዳርቻ የጠለፋ ስጋት ጨምሯል የሚል ማስጠንቀቂያ አወጡ።
እሁድ ዕለት ከሶማሊያ ባሕር ዳርቻ ስድስት ናውቲካል ማይልስ ርቀት ላይ አንድ መርከብ መታገቱን የዩናይትድ ኪንግደም የማሪታይም ንግድ ሥራዎች መስሪያ ቤት አስታውቋል። ስለ ክስተቱ ተጨማሪ መረጃዎች አልወጡም።
ተቋሙ ባወጣው መግለጫ፤ እሁድ ዕለት "ያልተፈቀደላቸው ሰዎች" መርከቡን ይዘው አቅጣጫውን ሶማሊያ ግዛት ውስጥ ወደ ሚገኘው ውሃ ማስቀየራቸውን ገልጿል። ይህንንም ተከትሎ በአካባቢው ያለው ስጋት "በከፍተኛ መጠን" መጨመሩን አስረድቷል።
ባለፈው ሳምንት ውስጥ ብቻ አሳ ማጥማጃ እና የነዳጅ ጫኞችን ጨምሮ አራት መርከቦች የባሕር ላይ ውንብድና እንደሆነ የተጠረጠረ ድርጊት ዒላማ ሆነዋል።
በአንድ ወቅት እጅግ ተስፋፍቶ የነበረው በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የሚደረግ የመርከቦች ጠለፋ እስካለፈው ሦስት ዓመት ድረስ ጠፍቷል በሚያስብል ሁኔታ ላይ ቢቆይም በድጋሚ መከሰት ጀምሯል።
የዩናይትድ ኪንግደሙ መስሪያ ቤት በመግለጫው "የባሕር ውንብድና ቡድን እንቅስቃሴ ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ መርከቦች በጥንቃቄ እንዲጓዙ ይመከራሉ" ብሏል። በአካባቢው ያለው የአየር ሁኔታ ለትንሽ ጀልባዎች ጉዞ አመቺ መሆኑንም አክሏል።
ተቋሙ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በሰሜናዊ ሶማሊያ ማሬዮ ባሕር ዳርቻ ላይ ሌላ መርከብ በመጠለፉ ማስጠንቀቂያ አውጥቶ ነበር።
በተጨማሪም የባሕር ወንበዴዎች ባለፈው ሳምንት ሐሙስ 17 ሠራተኞችን ይዞ በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ሲቀዝፍ የነበረ 'ሆነር 25' የተሰኘ የነዳጅ ጫኝ መርከብን መጥለፋቸውን በርካታ የደኅንነት ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መርከቡ 10 ፓኪስታናውያን፣ አራት ኢንዶኔዥያውያን እንዲሁም የሕንድ፣ ሲሪላንካ እና ምያንማር ዜጋ የሆኑ ሠራተኞችን ይዞ ነበር። ከሶማሊያ ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በሁለት የአሳ አጥማጆች ከተሞች መካከል እንደቆመ ተገልጿል።
ሐሙስ ዕለት የሶማሊያ ባንዲራን ያነገበ የአሳ ማጥመጃ መርከብ መያዙን የዩናይትድ ኪንግደም የማሪታይም ንግድ ሥራዎች መስሪያ ቤት ገልጿል።
ቢያንስ ሁለት የታጠቁ ሰዎች መርከቡ ላይ ለመውጣት ቢሞክሩም ሠራተኞቹ የማስጠንቀቂያ ተኩስ ካሰሙ በኋላ መሸሻቸውን አስታውቋል።